በኢትዮጵያ የስም ሕግ እንዴት ነው?

Date:

በኢትዮጵያ የስም አሰያየምን በተመለከተ የሚደነግገው ሕግ የፍትሐ ብሔር ሕግ ሲሆን በሕጉም ከአንቀጽ 32 ጀምሮ ተደንግጓል፡፡ በሕጉ እንደተቀመጠው እያንዳንዱ ሰው አንድ የቤተ ዘመድ ስምና አንድ ወይም ብዙ የግል ስሞችና የአባት ስም እንደሚኖረው ያስቀምጣል፡፡

ይህም ማለት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሆነ ዜጋ እነዚህ ሦስት ስሞች ሊኖሩት ይገባል ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም እነዚህ ስሞች የሚጻፉት እንደተፈለገ ሳይሆን የአጻጻፍ ሥርዓት ወይም ቅደም ተከተል አላቸው፡፡ ይኸውም በማንኛውም በአስተዳደር ክፍል ሰነድ ወይም ጽሑፎች ላይ የአንድ ሰው ስም በሚጻፍበት ወቅት በመጀመሪያ የሚጻፈው የቤተ ዘመድ ስም ሲሆን ቀጥሎ የግል ስም በመጨረሻም የአባት ስም ነው፡፡ ይሁንና ከቅደም ተከተሉ ተዛብቶ ተጽፎ ቢገኝ የግለሰቡን ትክክለኛ ማንነትን አይገልጽም ማለት ነው፡፡

ይህ የሕጉ ድንጋጌ እስካሁን በሀገራችን ላይ ከተለመደው የአሰያየም ዘዴ ለየት ያለ አዲስ ሥርዓት የሚዘረጋ ሲሆን፣ እስካሁን ባለው ሥርዓት የቤተ ዘመድ ስም የሚባለው በሥራ ላይ ውሎ አናየውም፡፡ የግል ስምና የአባት ስምን በተመለከተ ቀደም ሲል ከፍትሐ ብሔር ሕጉ መረቀቅ በፊት በልማድ ሲጠቀሙበት የነበረው እንዳለ የተቀመጠ ሲሆን ከፍትሐ ብሔር ሕጉ መረቀቅ በኋላ አዲስ ነገር የተጨመረው የቤተ ዘመድ ስምን በተመለከተ ብቻ ነው፡፡

የስም አሰጣጥ

በሕጉ በስም አሰጣጥ ወቅት የልጁ የቤተ ዘመድ ስም የአባቱ የቤተ ዘመድ ስም እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ነገር ግን የልጁ አባት ማንነት ያልታወቀ ሲሆን ወይም ልጁ የተካደ በሚሆን ጊዜ የልጁ የቤተ ዘመድ ስም የእናቱ የቤተ ዘመድ ስም እንደሚሆን የፍትሐ ብሔር ሕጉ ይደነግጋል፡፡     

የፍትሐ ብሔር ሕጋችን ስለ እያንዳንዱ የስም አይነቶች ወይም ክፍሎች የሚደነግገውን ስንመለከት የፍትሐ ብሔር ሕጉ የግል ስም በማለት የሚገልጸው ለአንድ ሰው በግሉ የሚወጣለት ከሌላ የቤተሰቡ አባላት ጋር የማይጋራው ስምን ነው፡፡ ስለሆነም የዚህ ስም ዋና ጠቀሜታው አንድን የቤተሰብ አባል ከሌላው የቤተሰብ አባል ለመለየት ነው፡፡

የግል ስም በማን እንደሚወጣና ለአንድ ልጅም ምን ያህል ስም ሊሰጠው እንደሚችል የሚደነግገው የፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀጽ 34 ሲሆን ይህ ድንጋጌ መሠረቱን ሲያስቀምጥ የአንድ ልጅን ስም የሚመርጠው አባቱ ወይም አባቱ በሌለ ጊዜ የእናቱ ቤተ ዘመዶች እንደሆኑ ይገልጻል፡፡ 

እንዲሁም ለልጁ ሁለተኛ የግል ስም እናቱ ወይም እርሷ ከሌለች የእናቱ ቤተ ዘመዶች መርጠው ሊሰጡት እንደሚችሉ ይገልጻል፡፡

የልጁ አባት ባልታወቀ ጊዜ ወይም የልጁ የአባቱ ወገን የሆኑ ቤተ ዘመዶች የሌሉት እንደሆነ የልጁ እናት ወይም እርሷ ባትኖር የእናቱ ቤተ ዘመዶች ሁለት የግል ስሞች ሊሰጡት ይችላሉ ማለት ነው፡፡

ከዚህም አንቀጽ የምንገነዘበው የአንድ ልጅ የመጀመሪያ ስም የሚያወጣለት አባቱ ነው ወይም አባት ለልጁ የመጀመሪያ ስም የማውጣት ቅድሚያ መብት አለው ለማለት ይቻላል፡፡ እንዲሁም የልጁ እናት አስፈላጊ ሆኖ ካገኘችው ለልጁ ሁለተኛ የመጀመሪያ ስም ልትሰጠው ትችላለች፡፡

አባት በሌለ ወይም እናት በሌለች ጊዜ እንደ ሁኔታው በምትካቸው ሆነው ለልጁ ስም የሚያወጡለት የአባት ወይም የእናት ቤተ ዘመዶች ናቸው፡፡ በዚህም ጊዜ ቤተ ዘመዱን በመወከል ልጁን የሚሰይመው ከአያቱ ከቅድመ አያቱ …ወዘተ መካከል በሕይወት ያለው ነው፡፡

እነዚህ በሌሉ ጊዜ ደግሞ ወደጎን ከሚቆጠሩት ዘመዶች መካከል በዝምድና አቆጣጠር ለልጁ የቀረበ ዝምድና ያለው ዘመዱ ነው፡፡ የዝምድና ደረጃው እኩል በሚሆንበት ወቅት ደግሞ በእድሜ አንጋፋ የሆነው ቅድሚያ ይኖረዋል፡፡

የልጁን አባት ወይም እናት ለማወቅ ያልተቻለ በሚሆንበት ጊዜ በአንቀጽ 39 መሠረት ልጁን ለመሰየም ኃላፊነት የተጣለው የክብር መዝገብ ሹሙ ላይ ነው፡፡ በዚህም ወቅት የክብር መዝገብ ሹሙ ለልጁ ሁለት የግል ስሞችና የቤተ ዘመድ ስም ሊሰጠው እንደሚገባ ሲደነግግ ስሞቹን ሊመርጥለት የሚገባው በተወለደበት አካባቢ ከሚገኝ ልማዳዊ የቤተ ዘመድ ስምና የግል ስም መካከል ሊሆን እንደሚገባ ይደነግጋል፡፡

እንዲሁም በዚህ አንቀጽ ንኡስ ቁጥር (1) መጨረሻ ላይ የአባቱ ቤተ ዘመድ ማለት ሲገባው የእናቱ ቤተ ዘመድ በማለት ያስቀመጠው ግልጽ ስህተት መሆኑ የማያጠራጥር ነው፡፡ ምክንያቱም ንኡስ ቁጥር (2) ስለ እናቱና ስለ እናቱ ቤተ ዘመዶች መብት የሚደነግግ በመሆኑ ንኡስ ቁጥር(1) በተመሳሳይ ስለ አባቱና የአባቱ ቤተ ዘመዶች መብት የሚደነግግ ነው መሆን ያለበት፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕጉ የእንግሊዝኛ ቅጂም የአባት ቤተ ዘመድ በማለት ነው የሚያስቀምጠው፡፡ ስለሆነም ይኸው ታርሞ የአባት ቤተ ዘመዶች በሚል ሊነበብ ይገባዋል፡፡  

ስምን ስለመለወጥ

የፍትሐ ብሔር ሕጉ ስም ሊለወጥ የሚችልባቸውን ሁኔታዎች ሲያስቀምጥ የመጀመሪያው በራስ አነሳሽነት ግለሰቡ ስሙ እንዲለወጥ ፍርድ ቤት በማመልከት የሚደረግ ሲሆን ሁለተኛው በሕግ ትእዛዝ የሚፈጸም እንደሆነ ይገልጻል፡፡

በራስ አነሳሽነት የሚደረግ የስም ለውጥ

1.            የቤተ ዘመድ ስምን ስለመለወጥ የሚደነግገው አንቀጽ 42 የቤተ ዘመድ ስምን ለመለወጥ መሟላት ያለባቸውን ሁኔታዎችን ያስቀምጣል፡፡ እነዚህም፡- 

2.            ለመለወጥ የሚፈልገው ሰው ለፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረብ አለበት፡፡ ይህም ማለት የስምን መለወጥ ጥያቄ ሊያቀርብ የሚችለው ራሱ ሰውዬው ብቻ እንጂ ሌሎች ሰዎች ይህን አይነት ጥያቄ ሊያቀርቡ አይችሉም ማለት ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ አባቱ ዘግይቶ ቢታወቅ በእንደዚህ ያለ ሁኔታ ደግሞ ስም እንዲቀየር ሕጉ ስለሚፈቅድ የስም ለውጥ ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የስም ለውጡን ማመልከቻ ማን ነው የሚያቀርበው የሚለውን ስንመለከት እንደ ልጁ ለአካለ መጠን ያልደረሰ መሆን እናትና አባቱ ማመልከት ይችላሉ ቢያስብልም የንኡስ አንቀጹ ቀጥተኛ ትርጉም ግን ይሄንን የሚፈቅድ አይመስልም፡፡ 

3.            ጥያቄው በፍርድ ቤት የሚፈቀደው በቂ ምክንያት ሲቀርብ ብቻ መሆኑን፤ ይህም ማለት የቤተ ዘመድ ስምን ለማስለወጥ አቤቱታን ማቅረብ ብቻ በቂ እንዳልሆነ ያሳያል፡፡ አቤቱታውን በበቂ ምክንያት ማስደገፍ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በቂ ምክንያት ሲባል ምን አይነት ምክንያቶች ናቸው በቂ ምክንያት ሆነው የሚቆጠሩት የሚል ጥያቄ ሊያስነሱ ይችላሉ፡፡ በሕጋችንም ይህን መለየት ለዳኞች ህሊና የተተወ ነው፡፡ በመሆኑም ዳኞች የጉዳዩን ጠቅላላ ሁኔታ በመገንዘብ የአንድን ምክንያት ስምን ለማስለወጥ በቂ ነው አይደለም የሚለውን ለመወሰን ይችላሉ፡፡

4.            ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን በሚመረምርበት ወቅት የስሙ መለወጥ የሦስተኛ ወገኖችን ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ያስቀምጣል፡፡ ፍርድ ቤቱ ከሚያደርገው የጥንቃቄ እርምጃ አንዱ ማወጅ ሲሆን ይህም ከግለሰቡ ጋር የንግድም ሆነ ተመሳሳይ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ሁኔታውን አውቀው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አልፎ ተርፎም ስሙ መለወጥ ይጎዳኛል የሚሉ ሰዎች ፍርድ ቤት በመቅረብ ተቃውሞአቸውን እንዲያቀርቡ ይረዳል፡፡

የመጀመሪያ ስምን ስለመቀየር

እንደ ቤተ ዘመድ ስም ሁሉ የመጀመሪያ ስሞችንም ለመቀየር የፍርድ ቤት ፈቃድ አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን በቂ ምክንያት ማቅረብ አያስፈልግም፡፡ አቤቱታ ማቅረብ ብቻ በቂ ይሆናል፡፡ አቤቱታውን ማወጁም እንዲሁ አስፈላጊ አይደለም፡፡

የአባትን ስም ስለመለወጥ

የአባት ስምን መለወጥን አስመልክቶ ሕጋችን ምንም የሚለው ነገር የለም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት የግል ስም በመሆኑ መለወጥም ካለበት መለወጥ የሚችለው አባት ራሱ ስለሆነ ነው፡፡ በልጅ ጠያቂነት ሊለወጥ አይችልም፡፡ ስለዚህም በሕጋችን መሠረት በልጅ አመልካችነት ሌሎቹን ስሞች መለወጥ የሚቻል ሲሆን መለወጥ የማይቻለው የአባትን ስም ብቻ ነው፡፡ 

በሕግ ትዕዛዝ ስምን ስለመለወጥ

በሕግ ትዕዛዝ ስም ሊለወጥባቸው የሚችሉት ሁኔታዎች ሁለት ብቻ ሲሆኑ እነሱም ጋብቻና ጉዲፈቻ ናቸው፡፡

በሕጉ አንቀጽ 41 ላይ እንደተቀመጠው የጉዲፈቻ ልጅ የጉዲፈቻ አድራጊው የቤተ ዘመድ ስም የሚኖረው ሲሆን፤ በጉዲፈቻ ውሉም መሠረት አንድ አዲስ የግል ስም ሊሰጠውና የጉዲፈቻ አድራጊው መደበኛ የግል ስም እንደ አባት ስም ሊሆነው ይችላል፡፡ ይሁንና የመጀመሪያ ስሞችንና የአባት ስምን በተመለከተ ልጁ ከጉዲፈቻ በፊት የነበረውን ይዞ ሊቆይ ይችላል ወይም ደግሞ አዲስ የመጀመሪያ ስም ሊወጣለትና የጉዲፈቻ አድራጊው መደበኛ ስም የአባቱ ስም እንዲሆን ሊደረግ ይችላል ማለት ነው፡፡ እንደ ጉዲፈቻ ሁሉ ጋብቻም በሕግ ትዕዛዝ የስም ለውጥ ያስከትላል፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀጽ 40 ድንጋጌ መሠረት አንዲት ያገባች ሴት ማናቸውም የፍትሐ ብሔርም ሆነ ንግድ ነክ ተግባራት በምትፈጽምበት ጊዜ በራሷ የቤተ ዘመድ ስምም ሆነ በባሏ የቤተ ዘመድ ስም ለመጠቀም ትችላለች ማለት ነው፡፡ ሚስት በባሏ ስም የመጠቀም መብት የሚኖራት ጋብቻው ጸንቶ እስከቆየበት ጊዜ ድረስ ነው፡፡ ጋብቻው የፈረሰው በፍቺ ወይም እንደገና ሌላ ባል በማግባቷ ምክንያት ከሆነ በስሙ የመጠራት መብቷም አብሮ ቀሪ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን አንቀጽ 40(3) ስንመለከት ጋብቻው የፈረሰው ከፍቺ ውጪ በሆነ ምክንያት ለምሳሌ፡- በባል ሞት ምክንያት እንደሆነ ሚስት ይሄንኑ መብት እንደያዘች ትቆያለች የሚል ሃሳብ ያለው ይመስላል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የህዳሴ ግድቡ ውዝግብ በፖለቲካዊ ሳይሆን በቴክኒካዊ መንገድ መፈታት አለበት

በአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ፣ እና የመካከለኛው ምስራቅ...

የ7 የጋራ መኖሪያ ቤቶች የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ አለመከናወኑ ተገለጸ

በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የሚተዳደሩ 7 የጋራ መኖሪያ...

የቀድሞው የኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

የቀድሞው የኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ በ80 ዓመታቸው ከዚህ...