በግብጽ የመገናኛ ብዙኃን እየተፈጸሙ ያሉ የጥላቻ ቅስቀሳዎች በሙስጠፋ ሓሚድ ዩሱፍ

Date:

የመንግሥትና የግል የግብጽ መገናኛ ብዙኃን ከሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጀመር በፊት በዓባይ ወንዝ ዙሪያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ አቧራ ማስነሳታቸውና ኢትዮጵያ ምንግዜም ከድህነት አረንቋ ፈጽሞ እንዳትወጣ የመፈለግ ስራዎችን ከመስራት ወደኋላ ብለው አያውቁም፡፡ በዐረቡ አለም የኢትዮጵያ ገጽታ አንዲጠለሽና ኢትዮጵያ ዐረቦች ዘንድ በታሪክ የነበራት ዝና እንዲጠፋ ማድረግ ከጀመሩ ዘመናት አልፈዋል፡፡ “ዓባይ ለግብጽ፣ ግብጽ ደግሞ ለግብጻዊያን የተሰጡ ስጦታዎች ናቸው፡፡” የሚለው መርሕ በግብጽ ሕዝቦች ልቦና ውስጥ ዘልቆ እንዲሰርጽ የግብጽ የመገናኛ ብዙኃን የተጫወቱት ሚና ቀላል ፈጽሞ ቀላል አይደለም፡፡ ለዐረቡ አለም ስለዓባይ ወንዝና ስለሕዳሴ ግድብ  የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን የሰሯቸው ስራዎች ከግብጻዊኑ የመገናኛ ብዙኃን አንጻር ሲታይ ምንም ስራና እንቅስቀሴ የለም፡፡ ከዚህ አንጻር  የግብጽ የመገናኛ ብዙኃን ከግብጽ መንግሰት ይበልጥ ስለዓባይ ወንዝና ስለሕዳሴ ግድብ በርካታ ሥራዎችን ሰርተዋል፡፡

ዐረቦች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከእሥራኤል ጋር ፍቅር ከመጀመሪያ በፊት እሥራኤል በዐረቦች ዘንድ የዲያቢሎስ ቁራጭ ተደርጋ ትወሰድ ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ የዐረብ መንግስታት በእሥራኤል ላይ ከነበራቸው ሃይለኛ የጥላቻ መንፈስ በመነሳት በዜግነት መታወቂያቸው (ፓስፖርታቸው) ላይ “ከእሥራኤል በስተቀር ለሁሉም የዓለም ሐገራት የተፈቀደ” የሚል ጽሑፍ አስፍረው የነበሩ ከመሆናቸው ባሻገር የእሥራኤልን ምድር የረገጠን ዜጋቸውን ዜግነት ከመንጠቅ አልፈው ከሐገር ያባሩ ነበር፡፡ ዐረብ ሐገራት ዜግነትን ከመንጠቅ በተጨማሪ የእሥራኤልን ምድር የረገጠ የየትኛውም ሐገር ዜጋ ፈጽሞ ወደሐገራቸው እንዲገባ አይፈቅዱም ነበር፡፡ የፍልስጥኤም መሬት እ.ኤ.አ ከ1947 ጀምሮ በእሥራኤል በግፍ የመያዙና በዓለም አቀፉ ተቋማት ፍልስጥኤም እንደሐገር እውቅና እንዳታገኝ በእሥራኤል እና በአጋሮቿ የሚደረገው ጫና ዐረቦች እሥራኤልን ክፉኛ እንዲጠሉ ካደረጓቸው ምክንያቶች አንዱ ሲሆን እ.ኤ.አ በ1967 ግብጽ ትመራው በነበራው የዐረቦች ጥምር ጦር ላይ እሥራኤል በሰባት ቀናት ውስጥ የተቀዳችው ድል ደግሞ ሌላኛው የጥላቻ ምክንያት ነው፡፡ ከዚህ ጀምሮ ግብጽ የበቀል ብትሯ በእሥራኤል ላይ ፍጹም መበርታት ጀመረ፡፡ በተለይ በነዳጅ ተፈጥሯዊ ሐብት የሐብት ደረጃ ላይ የደረሱትና በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ሐብታም ሐገራት በእሥራኤል ላይ ከፍተኛ ጥላቻ እንዲያድርባቸው  የግብጽ የመገናኛ ብዙኃን የጎላ ሚና ተጫውተዋል፡፡

የግብጽ የመገናኛ ብዙኃን በእሥራኤል ላይ ይነዟቸው ከነበሩ የጥላቻ መንገዶች አንዱ እሥራኤል በግፍ የወረረችውን የፍልስጥኤም መሬት ዐረባዊ ስሜትን በማቀንቀን ዐረቦች በእሥራኤል ላይ ጥላቻ እንዲያድርባቸው ማድረግ ሲሆን ይህም በዐረቦች ዘንድ ተቀባይነትን በማግኘቱ እሥራኤል በዐረቦች ክፉኛ እንድትጠላና ጥርስ እንዲከስባት አድርጓል፡፡ በዚህ የግብጽ የመገናኛ ብዙኃን የመጀመሪያ አንቅስቃሴ ግብጽ በዐረቦች ልብ ውስጥ ቦታ እንድታገኝና ተሰሚነት እንዲኖራት አደረገ፡፡ ግብጽ በዐረቡ ዓለም ከፍተኛ ተቀባይነትንና ተሰሚነትን ከመቼውም ይበልጥ ለማግኘት ከስሟ አስከትላ ዐረባዊነትን የሚያቀነቅን ተለጣፊ የዐረብ መገለጫን በመጨመር ስሟን ‹‹ጁምሁሪየቲ ሚስሬ-ልዐረቢያህ” /የግብጽ ዐረብ ሪፐብሊክ/ በማለት ሰየመች፡፡ ግብጽ በዚህ ብቻ ሳትወሰን በዐረቦች ላይ የራሷን የጎላ ጫና ለመፍጠርና በዐረባዊ ዜማ የራሷን ፖለቲካዊ ስትራቴጂ በዐረቦች ላይ ለመቀዳጀት የዐረብ ሊግን በሐገሯ ላይ ከመመስረቷ በተጨማሪ የሊጉ ዋና ጽሐፊ የእሷ ዜጋ ብቻ እንዲሆንና የሊጉ መቀመጫም ዋና ከተማዋ ካይሮ እንዲሆን አድርጋለች፡፡ በዚህም ረገድ ግብጽ በዐረባዊነት መንፈስ  ሽፋን በፈለገችውና በምትፈልገው አጀንዳ ላይ የዐረቦችን ድጋፍ ለማግኘት የዐረብ ሊጉን እንደመሳሪያ እየተጠቀመችበት ትገኛለች፡፡ ለዚህም በቅርቡ በሕዳሴ ግድቡ ዙሪያ በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያ ላይ የሚፈጥረው ራሱን የቻለ የጎላ ጫና ባይኖረውም የዐረብ ሊጉ የግብጽን አቋም በመደገፍ ያስተላለፈውን ውሳኔ እንደአንድ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል፡፡     

የግብጽ መንግሥትና የመገናኛ ብዙኃን የዐረቡን ዓለም ድጋፍ፣ እገዛና ትኩረት ለማግኘት ከፍልስጥኤም ጉዳይ ይልቅ በዓባይ ወንዝና በሕዳሴ ግድብ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡ ግብጽ በዓባይ ወንዝ ላይ አለኝ የምትለውን ፍትሐዊ ያልሆነና ከጅማሮው ጀምሮ የራስ ወዳድ መንፈስ ለማጠናከር እንዲሁም የሕዳሴውን ግድብ በመገንባት ኢትዮጵያ ልታገኝ የምትችለውን ከውሃ የሚገኝ የኤሌክትሪክ ሃይል እንዳታገኝ ለማድረግ የግብጽ መንግሥትና የግብጽ መገናኘ ብዝሃን የማይፈጥሩት እንቅፋት የለም፡፡ ግድቡ እንዳይሰራና ኢትዮጵያም ከግድቡ የምታስበውን የኤሌክትሪክ ሃይል እንዳታገኝ በማሰብ የግብጽ የመገናኛ ብዙኃንና የግብጽ መንግሥት፤ “እሥራኤል ከጥንት ጀምሮ የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ሐገራትን ለመቆጠጠር ካላት ፍላጎት የሕዳሴውን ግድብ ከኢትዮጵያ ጋር አብራ እየገነባች ትገኛለች፡፡” በማለት በሚነዙት የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ኢትዮጵያ ጥቁር አይሁዳዊትና ጽዮናዊት ሐገር ተብላ በመወሰድ በዐረቦች ዘንድ እንድትጠላ አድርጓታል፡፡ የግብጽ የመገናኛ ብዙኃን እንደሚያናፍሱት የሐሰት የጥላቻ ዘገባ ከሆነ የዓባይ ወንዝን ምንጭ የሆነቸውን ኢትዮጵያንና የዓባይ ተፋሰስ ሐገራት የሆኑትን ሐገረ- ሱዳንና ግብጽ ለመቆጣጠር እሥራኤል የነደፈችው ስትራቴጂያዊ እቅድ የተጠነሰሰው ጽየናዊቷን እሥራኤል ሐገር የመመስረቱን ሐሳብ በመጀመሪያ ያመጣው ግለሰብ ሚስተር ቲዮድሮ ሔዝትለር  እ.ኤ.አ 1902 ላይ ግብጽን ከጎበኘበት ጊዜ አንስቶ ነው፡፡ ቲዮድሮ ሔዝትለር ግብጽን በጎበኘበት ጊዜ በወቅቱ በግብጽ የእንግሊዝ ቅኝ ገዢ መሪ የነበረው ሎርድ ክሩመርና በወቅቱ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቡጥሩስ ጋሊ በጋራ የሚወያዩበትንና ስምምነት ላይ የሚደርሱበትን የውሃ አጠቃቀም ስትራቴጂ ፕሮጀከት አቅርቦ ነበር፡፡ የዚህ ፕሮጀክት ዋና ዓላማ በግብጽ ሲናይ ግዛት ወደአንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ስድተኛ አይሁዳዊንን ለማስፈር የታቀደ ነበር፡፡ ፕሮጀክቱ የቀረበለትን የቅኝ ገዢዋ የእንግሊዝ መንግሥት ለማሳመን ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡ ግብጻዊያኑ ይህን የሚሰተር  ቲዮድሮ ሔዝትለር  ሃሳብ በግብጽ የዓባይን ወንዝ የውሃ መጠን ለመቆጣጠር ከኢትዮጵያ መንግሰት ጋር በድብቅ የተደረገ አሻጥር ነበር በማለት አሁንም ድረስ የጥላቻ ፕሮፖጋንዳቸውን በኢትዮጵያ ላይ ያሰራጫሉ፡፡ ከታሪክ ድርሳናት ማስረጃ ጋር ሲታይ ይህ ለቅኝ ገዢዋ የእንግሊዝ መንግሥት እና ለሞግዚታዊው የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የቀረበው የሚስተር ቲዮድሮ ሔዝትለር የውሃ አጠቃቀም ስትራቴጂ ፕሮጀከት ስደተኛ አይሁዳዊንን በግብጽ ሲናይ ግዛት ላይ ለማስፈር ታቅዶ የተዘጋጀ የጽዮናዊ አይሁድ የሰፈራ እቅድ እንጂ ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚገናኝ ስትራቴጂያዊ እቅድ አልነበረም፡፡ ለዚህም በኢትዮጵያዊንና በአውሮፓዊያን የተጻፉ የታሪክ ድርሳናት አብይ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ወሰላም!!

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የህዳሴ ግድቡ ውዝግብ በፖለቲካዊ ሳይሆን በቴክኒካዊ መንገድ መፈታት አለበት

በአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ፣ እና የመካከለኛው ምስራቅ...

የ7 የጋራ መኖሪያ ቤቶች የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ አለመከናወኑ ተገለጸ

በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የሚተዳደሩ 7 የጋራ መኖሪያ...

የቀድሞው የኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

የቀድሞው የኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ በ80 ዓመታቸው ከዚህ...