ትዝታ ሁኖ የቀረዉ የልጆች አምባ ሲታወስ !

Date:





‎ቆይ ! ቆይ ! ይህን ፅሁፍ ለማንበብ ከመጀመራችሁ በፊት አንድ ነገር ላስቸግራችሁ ስልካችሁ ላይ “ፀሐዬ ደመቀች” መዝሙር ክፋቱት ።

‎አሁን እንቀጥል …

‎ጥቂት አመታት ወደኋላ ወቅቱ 1973 ዓ.ም ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ የተፈተነችበት ወዲህ አለም ላይ አዳዲስ አስተሳሰብ የፓለቲካ አሰላለፍ የሚፋተግበት ወቅት ።
‎ሀገሪቱም በብሄር የተደራጁ ቡድኖች አሜሪካ እስከ አፍንጫቸው ያስታጠቀቻቸዉ ጉልቤዎች ከተለያዩ አቅጣጫ የውስጥና የውጪ ኃይሎች ጋር ጦርነት ውስጥ የገባችበት ጊዜ ነው፡፡

‎ያኔ ነበር ወታደራዊ መንግስት ደርግ በአራቱም አቅጣጫ የተነሱትን ጠ,ላቶ.ች ለመታገል ሀገርን እናድን ሲል ጥሪ ያቀረበው ።

‎ጥሪዉን የተቀበሉ በርካታ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ልጆቻቸውን ያለ አሳዳጊ ጥለው በየጦር ሜዳው ተመሙ ጥለዉ ወደቁ ፡፡

‎ወላጆቻቸው ለሀገር ሲዋደቁ እንደወጡ ቀርተዉ አሳዳጊና ተንከባካቢ ያጡት ህፃናት በየጎዳናው መውደቃቸው ያሳሰበው የደርግ መንግስት፤ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በነበሩት መንግስቱ ኃይለማርያም ልዩ ትዕዛዝ የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ህፃናት አምባ ተቋቋመ፡፡

‎በቀድሞ አጠራር በሸዋ ክፍለ ሃገር ሀይቆችና ቡታጅራ አውራጃ፣ በአላባ ቁሊቶ ወረዳ፣ አላጌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢዎችም ፤ “ሰብለ አብዮት”፣ “መስከረም ሁለት ኦጋዴን”፣ “ዘርዓይ ደረስ” እና “መንግስቱ ኃ/ማርያም” በተባሉ 5 መንደሮች የተከፋፈሉ ወላጆቻቸውን በጦርነትና በሌሎችም ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች ያጡ ህፃናትን ተቀብሎ እንደ ወላጅ የሚድጉበት ወላጆቻቸዉን ያጡ ህፃናት መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ትምህርትና በሥነ ምግባር አንፆ ኮትኩቶ የማሳደግን ዓላማ አንግቦ አንባዉ አገልግሎት መስጠት ጀመረ ፡፡

‎አምባው ገና ከተወለዱ ህፃናት ጀምሮ በተለያዩ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ህፃናትን ተቀብሎ እያሳደገ ያስተምርና ዕድሜያቸው 18 ዓመት ሲሞላ (የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ) ከማሳደጊያው ይሰናበታሉ፡፡ ህፃናቱ አምባውን ለቀው በሚወጡ ጊዜ በስነ ምግባር የታነፁ እንዲሆኑና በማህበራዊ ህይወታቸውም የመገለል ስሜት እንዳያድርባቸው ልዩ የምክር አገልግሎት ይሰጣቸው እንደነበር የቀድሞው የአምባው ልጆች ያስታውሳሉ፡፡

‎በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ያገኙ ተማሪዎች አንድም ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይገባሉ አሊያም ወደ ውጪ አገር (በአብዛኛው ኩባና ራሺያ) እየሄዱ ይማሩ ነበር፡፡

‎የአምባው ህፃናት ከትምህርት ባሻገር በኢትዮጵያ ኪነጥበብ ላይ አሻራ ጥለዋል መሳጭና መልእክት አዘል በሆኑት ህብረ ዝማሬዎቻቸው በእጅጉ ይታወቃሉ፡፡

‎በታዋቂዋ ገጣሚ አለምፀሐይ ወዳጆ ክትትልና የጥበብ ስልጠና ይደረግላቸው የነበሩት የአምባው ልጆች፤ “የጀግና ፍሬ” በተሰኘ የኪነት ቡድን ታቅፈው በየጊዜው ለታዳሚዎች የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶችን ያቀርቡ ነበር፡፡ በዚህ ቡድን ተዘጋጅተው ለአድማጭ ጆሮ ከበቁትና ተወዳጅነትን ካገኙት ስራዎቻቸው መካከል “ፀሐዬ”፣ “የጀግና ልጅ ጀግና” እና “እርግቢቱ ሂጂ””የገቢ ምንጫችን ሰሊጥ ሰሊጥ ” የሚሉት ዛሬም ድረስ እንደተወደዱ ዘልቀዋል ።

‎እነዚህን በቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በተደጋጋሚ የሚለቀቁ መዝሙሮች በ1970ዎቹ መገባደጂያና በሰማንያዎቹ መጀመሪያ ላይ የነበሩ ታዳጊ እኒህን መዝሙሮች ከህዝብ መዝሙር ባልተናነሰ ያውቃቸው ነበር፡፡

‎ኮረኔል መንግስቱ ለ አምባው ህፃናት የነበራቸው ፍቅር እጅግ እንደሚለይ በርካቶች ይመሰክራሉ ። ከሚደረግላቸው እንክብካቤ ባሻገር መንግስቱ ሀይለማርያም ድንገት በአንባዎቹ እየተገኙ ከታዳጊዎቹ ጋር ጊዜያቸዉን በማሳለፍ ቤተሰባዊ ፍቅርን በመለገስ የጎደለባቸዉን ከህፃናቱ አንደበት ይጠይቁ ነበር ። ከዚህም አልፎ ችሎታቸውን እንዲያሳዩ ደብዳቤ እንዲፅፉ ያደርጉ ስለነበር አባታችን ይሏቸው ነዉ ።

‎በ1989 ዓ.ም ግን ያልተጠበቀዉ ሆነ ልጆቹ የክረምቱን የእረፍት ጊዜ ከቤተሰቦቻቸውና ከየጓደኞቻቸው ጋር ለማሳለፍ አምባውን ለቀው በወጡበት ወቅት ያ በሽዎች መጠለያ መጠጊያ የሆነዉ የኢትዮጵያ ህፃናት አምባ በአዋጅ እንዲፈርስ ስምምነት ተደረሰ ።

‎የአምባው ታዳጊዎች ትዝታቸዉን እንዲህ ይገልፁታል ።
‎አምባው፤አንድ ሰው በህይወት ዘመኑ ማግኘት ያለበትን ደስታና ፍቅር አግኝተን ያለፍንበትና ለህይወታችን መሰረት የሆነን ዕውቀት የቀሰምንበት ቦታ ነው፡፡ ራሳችንን በአግባቡ መግለፅ የምንችል፣ በራሳችን የምንተማመን ልጆች ሆነን እንድናድግ ያደረገን አምባው ነው፡፡ የምግብ፣ መጠጥና አልባሳት ጭንቀት ሳይኖርብን፣ የሚያስፈልገን ነገር ሁሉ ተሟልቶልን ነው ያደግነው፡፡ ከዚሁ ሁሉ በላይ ደግሞ አሳዳጊዎቻችን ተገቢውን የቤተሰብ ፍቅርና እንክብካቤ እየሰጡ አሳድገውናል፡፡ ይህ ቀረብን የምንለው ነገር ፈፅሞ የለም፡፡
‎የወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃ/ማርያም፤ ህፃናቱ አስፈላጊው ነገር ሁሉ እየተሟላላቸው እንደሆነ ለማየት የቅርብ ክትትልና ድንገተኛ ጉብኝትም ያደርጉ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት የአምባው ህፃናት ከምግብ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ቅሬታ አንስተው “አባታችን ይጠራልን” በማለታቸው ፕሬዚዳንቱ ወደ አምባው ሄደው ልጆቹን አነጋግረው ተመልሰዋል፡፡

‎አምባው እንዴት ፈረሰ? የኢትዮጵያ ህፃናት አምባ በአዋጅ እንዲፈርስ የተደረገው በ1989 ዓ.ም ነበር፡፡ ልጆቹ የክረምቱን የእረፍት ጊዜ ከቤተሰቦቻቸውና ከየጓደኞቻቸው ጋር ለማሳለፍ አምባውን ለቀው የወጡበት ወቅት ነው፡፡

ምንም ቤተሰብና ጠያቂ የሌላቸው በርካታ ልጆችም በአምባው ውስጥ ክረምቱን እያሳለፉ ነበር፡፡ አምባው እንደሚዘጋና ልጆቹ እዚያ ባሉበት ቦታ ሆነው ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪፖርት እንዲያደርጉ የሚያሳስብ መልእክት በሬዲዮ ተላለፈ፡፡ ይህ መልእክት የበርካታ የአምባው ልጆችንና ሕፃናትን የወደፊት ህይወት ያጨለመ እንደነበር ልጆቹ ይናገራሉ፡፡

‎የትላንት ታሪክን ማወቁ አይከፋም ብለዉ እስከዚህ ድረስ ስለተከተሉን እናመሰግናለን አንባዉ ታሪከ ብዙ ነዉና በአንድ ክፍል መጣጥፍ ዘርዝረን ለመጨረስ ቸግሮናል ። አንባቢ እንዳይሰለችና እንዳይታክትም ከደርግ ውድቀት በኋላስ? የህፃናት አምባ ልጆች ትዝታና ቁጭት . ፕሬዚዳንቱ ከአገር ሲወጡ … አሁንስ የሚለዉን በቀጣይ ክፍል ነገ በተመሳሳይ ሰአት ለማቅረብ ቃል እየገባን ለዛሬው በዚህ እንቋጭ ። ሀሳብ አስተያየታችሁን እንጠብቃለን ።

በየኔታ ቲዩብ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያን ከ500 በላይ ላመጡ ተማሪዎች ማበረታቻና እውቅና ተሰጠ

በ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከ500 በላይ...

በኖኖ ጃዊ ቀበሌ የሚኖሩ 14 ኦርቶዶክሳውያን በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ

በአርሲ ሀገረ ስብከት ጉና ወረዳ በሚገኘ ኖኖ ጃዊ ቀበሌ...

ትራምፕ ከጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በንግድ እና ወሳኝ ማዕድናት ላይ ንግግር አደረጉ

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማክሰኞ እለት የጃፓን የመጀመሪያዋ...

ኢንፊኒክስ ኢትዮጵያ እና ተግባረ-ዕድ አብሮ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

በትራንስሽን ማኑፋክቸሪንግ ኃ.የተ.የግ.ማ ባለቤትነት የተያዘው ኢንፊኒክስ እና የአዲስ አበባ...