አምራቾች ለሚገጥማቸው የገበያ ተደራሽነት ክፍተት ይሸፍናል የተባለው”ኑግዙ” የተሰኘ የኦንላይን የገበያ መድረክ ተመረቀ። ይህ የገበያ ስርዓት ስማርት ሊንክ ፕሮፐርቲስ ሃላፊነቱ የተወሰነ በግል ማህበር አማካኝነት ነው የተዘጋጀው።
የስማርት ሊንክ ስራ አስፈፃሚ አቶ ዮናስ በየነ፤የዚህ የ”ኑግዙ ” የተሰኘ የኦንላይን የገበያ መድረክ ዋና አላማ በኢትዮጵያ የዲጂታል ንግድን በማስፋፋት የዜጎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ ማቅለል ነው ብለዋል።
አቶ ዮናስ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሰፊ የገበያ እድል መፍጠር፣ ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋና በቀላል መንገድ ለሸማቹ እንዲቀርብ ማስቻል ነው ሲሉም ገልፀዋል።
የሸማቾችንና የነጋዴዎችን የአሰራር ዘዴ ያዘምናል የተባለም ሲሆን ይህ የኦንላይን የገበያ መድረክ እንደ አማዞን፣አሊባባ እና ሌሎች አለም አቀፍ ግዙፍ የኦላይን የገበያ መድረኮች የሚሰጧቸውን አገልግሎት በኢትዮጵያም ተደራሽ ለማድረግ ታስቦ መዘጋጀቱ ስራ አስፈፃሚው ጠቁመዋል።
ነግዙ ለተጠቃሚዎቹ ሰፊ የምርት አማራጮች፣ ለበርካታ ሻጮች ክፍት የሆነ መድረከ፣ ቀላልና ምቹ የፍለጋና የአጠቃቀም ሥርዓት፣ ዝርዝር የምርት መረጃና የተጠቃሚ አስተያየቶች መቀበያ ዘዴ ስለ መዘጋጀቱም ተገልጿል።
ስርዓቱ ከሚያዝያ 29 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት መስጠት ይጀመራል ተብሏል።