ከምድራችን ፍጡራንም ሆነ ማሽኖች ድንቅና ውስብስብ የሆነው አእምሯችን፣ በተወሳሰበ ማህበራዊ ኑሮ ውስጥ መኖር እንድንችልና እንዲስማማን ራሱን ከለውጥ ጋር ማስኬድ ይችላል፡፡ ወደዚህች አለም ስንመጣ አእምሯችን ተግባራችንን እንዲመራ ተደርጎ የተፈጠረ የአካላችን ዋና ክፍል ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኒውሮሳይንስ ከጤናው ዘርፍ ባሻገር አዲስ ዐይነት የፍልስፍና ዘርፍ ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡ ሕዝብን የሚከፋፍልና ወጅብ የበዛው ፖለቲካ በሚታይበት በዚህ ወቅት፣ በአእምሮ አሠራር ላይ የሚካሄዱ ጥናቶች የበለጠ ራሳችንንና ማህበረሰባችን እንድናውቅ አዲስ በር የከፈቱ ናቸው፡፡ አሁን አሁን የሰውን ስሜት፣ የውሳኔ አሰጣጥን፣ ስነምግባርን፣ ድንጋጤንና የስልጣን ጥማትን የመሳሰሉ ባህሪዎቻችንን የበለጠ ለመረዳት እየቻልን ነው፡፡ ከህዋሶቻችን ጀምሮ ኒውሮ ኬሚስትሪያችንን የኒውሮኖችን (የአእምሮ ሴሎችን) የትስስር እንዲሁም የአእምሮ ቅርጻዊ ለውጦችን በአእምሯችን ውስጥ በማጥናት ስለሁኔታው የበለጠ ማወቅ ተችሏል፡፡
ማህበራዊ ኒውሮ ሳይንስ በመባል የሚታወቀው ዘርፍ አዲስ የተጀመረ የጥናት ጽንሰ ሀሳብ ሲሆን፣ የማህበረሰብ ተግባር ወይም እውቀት በምን አይነት የአእምሮ ሴሎች ትስስር ሂደት እንደሚከወን የሚያጠና ነው፡፡ ዘርፏ የሰው ምግባር በምን አይነት የአእምሮ ክፍል ላይ በሚፈጠሩ ኬሚካሎች ሳቢያ እንደሚከሰት ከማጥናት በተጨማሪ፣ ማህበረሰባዊ ተግባሮች ከአእምሮ ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚያጠና ነው፡፡ የሁለቱ ማህበረሰባዊ ተግባሮች ከአእምሮ ጋር ያላቸውን ግንኑነት የሚያጠና ነው፡፡ የሁለቱ ግንኙነት ተገለባባጭ ነው፡፡ አእምሮ ማህበረሰባዊ ዕውቀትም ሆነ ተግባር ላይ ተጽእኖ የሚያመጣውን ያህል ማህበረሰባዊ ምግባሮችም አእምሮ ላይ ተጽእኖ ያሳድራሉ፡፡ እርስ በርስ ተጽእኖ ማሳደራቸው የታወቀ ቢሆንም፣ ምን ያህል ነው ተጽእኖዋቸው? የሚለው ግን ትልቁ ጥያቄ ነው፡፡
በMIT የአስተሳሰብ ኒውሮ ሳይንቲስት የሆነው ኢሚሊ ብሩኖ ስለነገሮች ያለንን አግባብ ያልሆነ ፍረጃ እንዴት እንደሚከሰትና ተግባራዊ እንደሚደረግ እንዲሁም ርህራሄ እንዴት እንደሚፈጠር በማጥናት የተሻለ ዕውቀት በማስጨበጥ እነዚህ አይነት ነገሮችን በመጠቀም እንዴት ሰላምን ማስረፅ እንደሚቻል በተለያዩ ወቅቶች በተካሄዱ ጉባኤዎች ላይ ጥናትን ሲያቀርብ ቆይታል፡፡
አእምሯችን በጣም ውስብስብ የሆነ ሰርዓት ያለው አካላችን ነው፡፡ እስካሁን በተደረጉ ጥናቶች በፊት ይገመት እንደነበረው አእምሯችን በተሰጠው መረጃ ላይ ብቻ ተመስርቶ በእዝ መልክ ከሆነ ማዕከል በሚተላለፍ ትዕዛዝ መሠረት ብቻ የሚሠራ አይደለም፡፡ በተቀራኒው፣ ከሁሉም ቦታ ወደ ሁሉም የአእምሮ ክፍል ትይዩ በሆኑ ኔትወርኮች እንደሚሠራ ተረጋግጧል፡፡ ተግባር የአእምሮ ውጤት እንደመሆኑ በተፈጥሮ የሚገኙ የአካባቢያዊ ሁኔታዎች ተጽእኖ ጭምር የሚካሄድ ውስብስብ ድርጊት ነው፡፡
በኒውሮ ሳይንስ ጥናት መስክ አእምሮን የበለጠ በማወቅ የሚገኙ አዳዲስ እውቀቶች በህይወታችን ላይ ትልቅና ዘላቂ ለውጥ ማምጣታቸው አይቀርም፡፡ በዘርፏ የሚገኙ አዳዲስ ግኝቶች አለም አቀፍና የእርስ በርስ ግጭቶችን እንዴት እንደምንረዳ፣ ክስተቱን በምን መልክ መያዝ እንዳለብንና ችግሩን እንዴት እንደምንፈታቸው ያለንን እውቀት በማጎልበት መፍትሄ ለማግኘት ተስፋ ይሰጣል፡፡ በኒውሮ ሳይንስ ዘርፍ የአእምሮን ተግባር ለማወቅ ትልቅ ለውጥ ያመጣው ሰው ሰራሽ መሣሪያ ፈንክሽናል ማግኔቲክ ሪዞናንስ ኢሜጂንግ (FMRI) የተሰኘው ሲሆን፣ አእምሮ የሚያነሳቸው ርዕሶች በኒውሮ ኬሚካልና ኒውሮ አናቶሚካል መንገድ የትኛው የአእምሮ ክፍል ጋር እንደሚገናኙ ማወቅ ያስችላል፡፡ ይህ ማለት ለእያንዳንዱ የሰው ልጅ ጭፍን ጥላቻ ኒውሮሎጂካል መነሻ አለው በማለት፣ እያንዳንዱ ሰው ለተግባሩ መንስዔ የሆነ ስር የሰደደ ምክንያት እንዳለው በነባራዊ መንገድ ራሱ እንዲያውቅ ያደርገዋል፡፡
ሠላምን ማምጣት የሚፈልጉ አካላት አሁን ባለው ተለዋዋጭ ማህበረሰብ ውስጥ ምን አይነት ዘመናዊ መንገድን መከተል እንዳለባቸው ኒውሮ ሳይንስ መንገዱን ይመራቸዋል፡፡ ሰዎች ምን እያሰቡ እንደሆነ ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደሚያስቡም ማወቃቸው የበለጠ ይጠቅማል፡፡ የተለመደው በጎ አመለካከት ብቻ ይህን ለማወቅ በቂ እንደማይሆን በMIT የዘርፉ ባለሙያ የሆኑት ይናገራሉ፡፡
እንደ ኢሚሊ ጥናት ከሆነ ለግጭቶች መነሻ ከሆኑ ምክንያቶችና አስተሳሰቦች ውስጥ አእምሯችን ውስጥ ስር የሰደደ በጎ ያልሆነ አመለካከት፣ ትርክትና ጥላቻ የሚጠቅስ ሲሆን፣ እንዲህ አይነት ስሜትም ሆነ ግንዛቤ እንዳለን እንኳን ላናቀው እንችላለን፡፡ ስካን በማድረግና በኒውሮ ኢሜጂንግ አማካኝነት ኮንሺየስና ሰብኮንሺየስ ውሳኔያችንን በግጭት ወቅት ማን እንደሚያዘው ማወቅ ይቻላል፡፡ የኒውሮ ባዮሎጂካል ስርዓቱንም በማወቅ ፀረ-አመፅ የሆኑ ውጤታማ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ማድረግ ያስችላል፡፡ ይህን መንገድ በተገቢ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ አለማችንን በተሻለ ከአመጽ የፀዳች ማድረግ ይቻላል፡፡
በካምብሪጅ መቀመጫውን ያደረገ ግብረ ሰናይ ተቋም በኒውሮ ሳይንስና በግጭት አፈታት መካከል ግንኙነት እንዳለ አረጋግጧል፡፡ ከMIT ጋር በጋራ በሚያካሂዱት ጥናት ከግጭት አኳያ ያለውን ግንኙነት በመለየት ሌሎች እንዲያውቁት እየተሞከረ ነው፡፡ ይህ መንገድ ይበልጥ ሲታወቅ ግጭቶችን እንዴት ማየት እንዳለብን ሠፋ ያለ ምልከታ ይሰጠናል፡፡
በዚህ ዙሪያ “ቢዮንድ ኮንፍሊክት” የተሰኘ ተቋም በፈረንጆቹ 1992 ዓ.ም ከተመሠረተ ጀምሮ በአለማችን ላይ የተከሰቱ ግጭቶች ለማብረድና መፍትሄ ለማግኘት ሲሞክር ቆይቷል፡፡ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች በአካል በመገኘት ሁኔታዎችን ለማጥናት የሞከሩ የዘርፏ ባለሙያዎች፣ ከሰሜን አየር ላንድ ግጭት ጀምሮ በምዕራብ አውሮፓ ያለውን፣ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት የነበሩ ግጭቶችን ሲያጠኑ መፍትሄም ሲያፈላልጉ ኖረዋል፡፡ ድርጅቱ ለ22 ዓመታት ሰላም ለማምጣት ሲጥር ከቆየ በኋላ፣ “በስራችን ላይ ምን የጎደለበን ነገር አለ” ብሎ ለማሰብ ተገዷል፡፡ በዚህ ወቅት ኒውሮ ሳይንስ ጥቅም ላይ መዋል እንዳለበት መታወቁን የድርጅቱ የጋራ መስራች የሆኑት ቲሞቲ ፈሊፕስ ይናገራሉ፡፡ ኒውሮ ሳይንቲስቶች ስለ ግጭት የነበረንን አስተሳሰብ ስር ነቀል በሆነ መንገድ እየለወጡልን ይገኛሉ ብለዋል፡፡ ሰው መሆን ምን ማለት እንደሆነ እንድናውቅ በማድረግ የሰዎች ደርጊት በምን ምክንያት እንደሚከሰት በማጥናት ጠለቅ ያለ እውቀት እንዲኖረን አስችለዋል፡፡ ሰዎች ከግጭት እንዲርቁም ሆነ ወደ ግጭት እንዲያመሩ የሚያደርጋቸውን ምክንያት ዘርፏ እንድናውቅ አስችሎናል፡፡ ማወቅ በራሱ ትልቅ ብቃት ይፈጥርልናል፡፡
ለሰው ልጆች ተግባራት ምክንያት ከሚሆኑት መካከል ባህል፣ ዘርና ብሄርን የመሳሰሉት መገለጫዎች ብቻ አያደሉም፡፡ ስለ እነዚህ ነገሮች ያለን አመለካከት በአንድነት በአንጎላችን ላይ በሚቀመጡት ጊዜ በሁላችንም ዘንድ ተመሳሳይ የሆነ ውጤት ያመጣል ሲሉ የኩባንያው ሀላፊ ይናገራሉ፡፡ ማህበራዊና ፖለቲካል ሳይንስ ዘርፎች ሰው ምክንያታዊ ነው ብለው ቢያስተምሩም፣ ሰው ግን በይበልጥ ስሜታዊ ነው፡፡ በአብዛኛው ተግባራችንን ከሚወስነው ምክንያት ዋናው ስሜታችን ሲሆን፣ ተጽእኖ የሚያሳድርብንን ይህን የአስተሳሰብ ክፍላችንን በተገቢው መንገድ ማወቅና ማስተካከል እንኳን አልቻልንም፡፡
የኒውሮ ሳይንስ ጥናትን ተግባራዊ ለማድረግ የታቀደው፣ ዘርፏ ጭፍን ጥላቻን የሚያስከትሉ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ኃይማኖታዊ ሀይሎችን በማቀናጀት የሚፈጥረውን ከባድ ተጽእኖ ለማወቅና ለሌሎች ለማስተማር ነው፡፡ ስለ አንጎላችን የተጠኑ በርካታ ጥናቶች ሙሉ በሙሉ እንደሚያሳዩት አዕምሯችን መለወጥ እንደሚችል ነው፡፡ ጥናቶቹ የጅምላ ፍረጃ እና ፍርሃት ከልጅነታችን ጀምሮ ከቤተሰብም ሆነ ከጓደኞች የሚገኝና ውስጣችን የሚሰርፁ መሆናቸው የታወቀባቸው ናቸው ፡፡ ማወቁ እነዚህን መሠል አላስፈላጊና ግጭት ፈጣሪ ነገሮችን ከራሳችን ላይ ለማላቀቅ ጠቃሚ የሚሆኑ አዳዲስ ዘዴዎች ተግባራዊ ይደርጋሉ ብለን ስለ ወደፊቱም ተስፋ እንድናደርግ ያግዘናል፡፡
ስለ እራሳችን ታሪክ የበለጠ ማወቅ በቻልን መጠን በተግባር ምን ያህል የጠለቀ ተጽእኖ ማሳደር እንደሚችሉም ስለምናውቅ፣ ኒውሮ ሳይንስና ሶሻል ሳይኮሎጂ እውነተኛ ጥቅም ሊሰጡን እንደሚችሉ ማመን እንጀምራለን፡፡ ዋና አላማው ስለ ግጭት በተለያዩ የዕውቀት ዘርፎች እስካሁን የሚታወቀውን በማቀናጀት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻል ነው፡፡ ግጭትን የሚያስከትሉና ለአመፅ አቅጣጫ የሚያሲዙ ክስተቶችን በመለየት የተገኙ ሀሳቦችን ለተጠቃሚዎች በመቀየር መሪዎችና ፓሊሲ አውጪዎች ጥቅም ላይ እንዲያውሉት፣ እንዲሁም ወደፊት ለሚካሄዱ ጥናቶች በግብአትነት እንዲያገለግሉ ነው፡፡ በብሔር በዘርና በሃይማኖት መንስኤ የተነሱ ግጭቶችን ለማብረድ የሚሰሩ ግለሰቦች ከኒውሮ ሳይንቲስቶች ጋር በማበር ለሰው ልጆች ግጭት መንስኤ የሚሆኑ ጭፍን ጥላቻዎች፣ ፍርሃትና ማስጠላቶችን የመሳሰሉ ስሜቶች እንዴት እንደሚመነጩ ለማወቅ እየጣሩ ነው፡፡ አጥኚዎች በጥናታቸው ያወቁትን ግኝት በመጠቀም ብዛት ያላቸው ስትራቴጂዎችን ለመንደፍ ገና ብዙ ቢቀራቸውም፣ ጅምራቸው ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ሠላምን ለመገንባት የሚያስፈልግ ሂደት ውስጥ አንጎላችን እንዴት እንደሚሠራ ማወቁ በራሱ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ሰዎች ላለባቸው ጭፍን ጥላቻ መንስኤ የሆነ ኒውሮሎጂካል(የአእምሮ ሴል) መነሻ እንዳለ ማስተማሩ በራሱ ነገሮችን እንዲያስተውሉ በማድረጉ ብቻ ጥቅም ይሰጣል፡፡