ኢትዮጵያ ከግል የቦንድ ባለቤቶች ጋር ደርሳው የነበረው በመርህ ደረጃ ላይ የተመሰረተ ስምምነት (AIP) በዋና አበዳሪ ሀገራት (OCC) ውድቅ ተደርጓል።
ቻይና እና ፈረንሳይ የሚመሩት የሁለትዮሽ አበዳሪዎች ኮሚቴ (OCC) ስምምነቱን ከመረመረ በኋላ ውድቅ ማድረጉ ነው የተገለጸው። ይህ ውሳኔ ሀገሪቱን የአንድ ቢሊዮን ዶላር የዩሮ ቦንድ ዕዳ ለመክፈል እያደረገች ያለችውን ጥረት ወደ ኋላ የሚመልስ ነው።
ለዚህም በምክንያት የተቀመጠው አበዳሪ ሀገራቱ ኢትዮጵያ ከከግል የቦንድ ባለቤቶች ጋር ያደረገችው በመርህ ደረጃ ላይ የተመሰረተ ስምምነት (AIP) “ከእኛ ጋር ሲነፃፀር ፍትሃዊ ያልሆነና የግል ባለሀብቶቹን የጠቀመ ነው” በማለታቸው መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ኮሚቴው ለገንዘብ ሚኒስቴር በላከውና በሚኒስቴሩ በኩል ይፋ በሆነው ደብዳቤ ላይ እንደሰፈረው ስምምነቱ፥ የአበዳሪዎች ኮሚቴ (OCC) እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የሚከተሉትን የአበዳሪዎች እኩልነት መርህ እንዳልተከተለ ይጠቅሳል።
አክሎም፥ “አሁን ባለው ተስፋ ሰጪ የኢኮኖሚ ሁኔታ አንጻር ሲታይ፣ የግል ባለሀብቶቹ ያደረጉት የዕዳ ማሻሻያ ጥረት በጣም አነስተኛ ነው” ሲል ነው የገለጸው።
በተጨማሪም፥ በስምምነቱ ውስጥ የተካተተውና ኢትዮጵያ ወደፊት ኢኮኖሚዋ ሲያድግ ለባለሀብቶቹ ተጨማሪ ክፍያ እንድትፈጽም የሚጠቅሰውንም ክፍል “የዕዳ ሽግሽጉን ሂደት ውስብስብ ከማድረጉም በላይ፣ በአበዳሪዎች መካከል ከፍተኛ የሆነ የጥቅም ልዩነት እንዲፈጠር ያደርጋል ሲል አንስቷል።
የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫም ሂደቱ ወደ ኋላ መመለሱ የሚያስቆጭ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ግን አሁንም ለሰላማዊና ለፍትሃዊ ድርድር ዝግጁ ነች ሲል ገልጿል።
ኢትዮጵያ ይህንን የ1 ቢሊዮን ዶላር የዩሮ ቦንድ ብድር የወሰደችው እ.ኤ.አ. በ2014 ሲሆን፣ ብድሩ ለ10 ዓመታት የሚቆይና በየዓመቱ 6.625 በመቶ ወለድ የሚከፈልበት ነበር።
|@tikvahethmagazine
