አፍሪካ ከ150 በላይ የባህር ትራንስፖርት አካዳሚዎች ቢኖሯትም፣ በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍ የመርከበኞች የሰው ኃይል ውስጥ ያላት ተሳትፎ ከ1.9 ሚሊዮን ከሚሆነው የዓለም የባህር ሰራተኛ አጠቃላይ ቁጥር ውስጥ 4% ብቻ መሆኑ ተገለፀ።
ይህን አነስተኛ ተሳትፎ ተከትሎ፣ አህጉሪቱ ዘመናዊ፣ ተወዳዳሪና ሁሉን ያካተተ የባሕር ላይ የሰው ኃይል ለመገንባት በጋራ ጥረት የምታደርግበት ትልቅ ምዕራፍ የሆነው “ዘ አፍሪካ ማሪታይም ኮንፈረንስ 2025” በአዲስ አበባ ሊካሄድ መታቀዱ ታውቋል።
የአፍሪካ የባሕር ላይ ጉባኤ ሰብሳቢና የዋይ ሲ ኤፍ ማኒኒግ ሊሚትድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ፍራንስ ጆበርት ” ይህ ጉባኤ እምቅ አቅምን ወደ ዕድል በመቀየር አፍሪካውያን መርከበኞች በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ በልበ ሙሉነት እና በተወዳዳሪነት እንዲሳተፉ የሚያስችሉ ሥርዓቶችን በመገንባት ላይ ያተኮረ ነው” ብለዋል።
ኮንፈረንሱ የሚካሄደው በ”አፍሪካ- ቀጣይ የአለም አቀፍ የመርከበኞች ግንባር” በሚል መሪ ቃል ሲሆን፣ የመላው አፍሪካ መሪዎችን እና በአለም አቀፍ የባህር ላይ ጭነት ማጓጓዣ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ቁልፍ ባለድርሻ አካላትን ያሳትፋል ተብሏል።
ዝግጅቱ በዋይ ሲ ኤፍ ማኒንግ ሊሚትድ ከኢትዮጵያ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ጋር በአጋርነት የሚዘጋጅ የሶስት ቀናት ጉባኤ መሆኑ ነዉ የተገለጸው።
CapitalNews