እናት ባንክ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች የማብቃት ሥራ ላይ ከተሰማሩ የተለያዩ ድርጅቶች ጋር አጋርነትን በመፍጠር ያለምንም ማስታወቂያና ውድድር የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ባንኩ በትናንትናው ዕለት ለ2ኛ ጊዜ ባዘጋጀውና የተለያዩ ታዋቂ ሰዎችና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በተገኙበት “ለእናቴ” እና “የዓመቱ ድንቅ እናት” በሚል የጽሑፍ ውድድር አዘጋጅቷል።
በዚህም “ለእናቴ” በተሰኘው የጽሑፍ ውድድር ከ1ኛ እስከ 5ኛ ደረጃ ላገኙ ተወዳዳሪዎች እንደየደረጃቸው ከ150 ሺሕ ብር እስከ 50 ሺሕ ብር የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል።
“በዓመቱ ድንቅ እናት” ዘርፍ ደግሞ አሸናፊ የሆኑት እናት የ200 ሺሕ ብር እንዲሁም አሸናፊዋን እናት ላቀረበው ሰው የ100 ሺሕ ብር ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን፤ ተጨማሪ 10 ለሚደርሱ ሰዎችና ጽሑፎቻቸው “ለእናቴ” በተሰኘው የእናት ባንክ መጽሔት ላይ ለወጣላቸው የ15 ሺሕ ብር ሽልማት አድርጓል።
በፕሮግራሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የባንኩ ኮርፖሬት አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ገነት ሐጎስ፤ እናት ባንክ በዋናነት የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማሳደግ ራዕይ ያለው ትርፋማና የባለአክስዮኖችን እሴት እያሳደገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አክለውም ባንኩ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች የማብቃት ሥራ ላይ ከተሰማሩ የተለያዩ ድርጅቶች ጋር አጋርነቱን በመፍጠር ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ያለምንም ማስታወቂያና ውድድር የሥራ እድል እንዲያገኙ ማድረግ ስለመቻሉ አስታውቀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የትምህርት ሂደታቸውን ያሻሻሉ ሴቶችን በስልጠናቸው መሠረት አግባብነት ባለው የሥራ መደብ ላይ እንዲመደቡ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
እናት ባንክ የተሟላ አገልግሎትን ለመስጠት በ11 ባለራዕይ ሴቶች የተቋቋመ እንደሆነ የገለጹት የኮርፖሬት አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንቷ፤ “እነዚህ ባለራዕይ ሴቶችም የአገልግሎት ክፍያቸውን ጭምር በመተው የባንኩን ጥቅም በማስቀደም ተምሳሌት መሆን ችለዋል” ብለዋል።
በተጨማሪም ባንኩ የሴቶችን አቅም የማሳደግ ኃላፊነትን መዋቅራዊ በማድረግና አላማውን ለማሳካት፣ ኢኮኖሚያዊ ጫናቸውን ለመቅረፍ እንዲሁም በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል የበኩል አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የፕሮጀክቱን የረዥም ጊዜ ስኬት ለማረጋገጥ በቴክኒክ ስልጠና፣ በገበያ ትስስር እና በዘላቂ የአመራር ዘዴዎች ሃይንከን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል፡፡