“…ከአገሬው የኪን ፍልስፍና ተነስቶ፥ በ40ዎቹ አርመናውያን አመጣጥ ጎዳና ተምሞ፥ ማርሽ ኢትዮጵያ እና ማርሽ ተፈሪን ተዝቶ፥ የኬቦርክ ናልባንዲያን እና የየኔታ ዮፍታሄ ንጉሴን ፍጥጫ አውስቶ፥ በፋቼታ ኔራ ኩርባ ታጥፎ፥ መሰንቆ እንደ ጦር መሣሪያ የተቆጠረበትን አውድ አውግቶን ይነጉዳል። የሀገር ፍቅር ማኅበርን ከአመሠራረቱ ጀምሮ የነበረውን ታሪክ ለመሰነድ የሄደበት ርቀት እሚደንቅ ነው። የቀብር ቀኑን በገዛ ሙዚቃው ከታጀበለት አሰፋ አባተ፥ እስከ ሙዚቃ የዋጠው ፖለቲካ (አሊ ቢራ)፥ ከሜሪ አርምዴ ታሪክ የአበበ ፍቅር እስካናወዛት አስናቀች ወርቁ ድረስ ያሉ የሕይወት ታሪክ መድብል ብዙ የተለፋበት ሥራ መሆኑን ያሳብቃል። የተለያዩ የሙዚቃ ባንድ ታሪኮችን ማካተቱ ሲገርመን፥ ዓይነስውራን ሙዚቀኞችን ማውሳቱ ደግሞ እጅግ አስደንቆኛል። የ700 ሙዚቃዎች “ካታሎግ” ደግሞ ሌላ ታሪክ ነው።”
ይነገር ጌታቸው፣ ጠመንጃና ሙዚቃ
ይህን ያውቁ ኖሯል
በቅሎ ወለደች!
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ባኮ ቲቤ ወረዳ አንዲት በቅሎ መውለዷ ተነግሯል፡፡ የበቅሎዋ ባለቤት አቶ ብርሃኑ ተምትሜ በ2014 በቅሎዋን እንደገዟት እና ለማጓጓዣ አገልግሎት ሲጠቀሙባት መቆየታቸውን ተናግረዋል። ነገር ግን የበቅሎዋ ሆድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን እንዳአስተዋሉ እና ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 5፡30 ላይ እንደወለደች አረጋግጠዋል፡፡ የበቅሎዋ መውለድ ክስተት እንዳስገረማቸው አንስተው ውርንጭላው አሁን ላይ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ በባኮ ቲቤ ወረዳ ግብርና ጽ/ ቤት የእንስሳት ሐኪም የሆኑት ዶክተር ለማ አያላ÷በቅሎ ሲወልድ አይተው እንደማያውቁ እና ክስተቱ እንግዳ እንደሆነባቸው ገልፀዋል፡፡ ባለሙያው በቅሎ አትወልድም የሚለው እሳቤ በሳይንስ እና በባህላዊ መንገድ የታመነበት ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ ከአንድ ሚሊየን በቅሎዎች አንዳቸው ሊወልዱ እንደሚችሉ መግለጻቸውን የወረዳው ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ሥነ-ግጥም
ፊደል
ሀ ፡ ብቴ ሀብትሽ ይሁን ብዬ
ለ ፡ መኖሬ እስትንፋሴን ከአንቺ ደስታ አስከትዬ
ሐ ፡ ኪሜ ሆነሽ ለሕይወቴ መድሀኒቴ
መ ፡ መኪያዬ ፍቅር ዓለም አለኝታዬ
ሠ ፡ ፊ ልቤ ውስጥ አኖርኩሽ ከሌላው ዓለም ነጥዬ፤
ረ ፡ ጅሙን ፍቅር ታሪክ ፣ የድሮውን ፊት ነስተሽው
ሰ ፡ ው ያለውን ፣ የሀሜቱን ፣ የወሬውን አድምጠሽው
ሸ ፡ ሸሽ ፍቅሬን ፣ መሀይም ብለሽ ንቀሽው
ቀ ፡ ንም ያልፋል ፣ መሀይምም ፊደል ያውቃል
በ ፡ ተናቀው አንጿበቴ ልቤ ዛሬ እንዲህ ይልሻል…
ተ ፡ ስፋ አልቆርጥም እኔ ፣ ውስጤ አሁንም ይወድሻል
ቸ ፡ ሩ ጌታ ሰርቶብሽ ግን ብትመለሽ ይሻልሻል፣
ኀ ፡ ይሌ አልቆ ብከፋብሽ ኋላ አንቺኑ ይጎዳሻል
ነ ፡ 7 ፍቅር ከእኔ ጠፍቶ ፊጿል ሁሉ ይሰድብሻል፡፡፡፡
የግጥም ጥም፣ ሳልሳዊ አስፋው ከበደ
አማርኛ አባባሎች
- ጥጃ ቢፈነጭ በሜዳ ውሀ ቢሄድ በጎድጓዳ፤
- ከጠጅ ወዲያ አስካሪ ከባለቤት ወዲያ መስካሪ፤
- ያልታደለ በረዶ ከድንጋይ ላይ ያርፋል፤
- የለመነ ያገኛል የነገደ ያተርፋል፤
- ያልፋል እስኪያልፍ ያለፋል፤
- ለብልህ አይነግሩ ለድመት አያበሩ፤
- ያለ ሴት ምን ያደርጋል ቤት፤
- ያባይ ምልክቱ አንደበቱ የገዳይ ምልክቱ ሽልማቱ፤
- ማሽላ እየፈካ ያራል፤
- ድሪያ የዝሙት ዋዜማ፤
አማርኛ አባባል
ጠቅላላ እውቀት
በዓለም ላይ በየስድስት ሰከንዱ አንድ ሰው፣ በየዓመቱ ደግሞ ከ8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መንስኤቸው የትንባሆ ምርትና የትንባሆ ጭስ በሚያስከትላቸው የካንሰርና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምክንያት ሕይወታቸውን ያጣሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከ8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ወደ 17 ሺሕ የሚጠጉ ሰዎች መንስኤቸው የትንባሆ ምርትና የትንባሆ ጭስ በሆኑ የካንሰርና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምክንያት ሕይታቸው ያጣሉ፡፡ የትንባሆ ሱስ ባስከተለባቸው ሕመም ምክንያት በቋሚ ደዌ ተይዘው በየቤታቸውና ተቋማት የአልጋ ቁራኛ የሆኑ ሰዎች እጅግ በርካታ ናቸው። ይህንን ታሳቢ በማድግና የጉዳዩ ስርጭትና አሳሳቢነት የሚመጥን ግብረ መልስ ለመስጠት፤ በከተማ ደረጃ ራሱን የቻለ የሦሶት ዓመት የተቀናጀ የትምባሆ ቁጥጥር ስትራቴጂ ተቀርጿል። ስትራቴጂውን በላቀ ደረጃ ለማስፀም እንዲቻልም፤ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላትን ያካተተና በከተማው ከንቲባ የሚመራ የትምባሆ ቁጥጥር ትግበራ አስተባባሪ ግብረ ሃይል እንዲደራጅ ተደርጎ አዲስ አበባን ከትምባሆ ጭስ ነፃ ለማድርግ በዘንድሮ ዓመት ሥራው ተጀምሯል። በየዓመቱ ግንቦት 23 ቀን ዓለም አቀፍ ትንባሆ የማይጨስበት ቀን ሆኖ የሚከበር ሲኾን፤ ዘንድሮ በ2015 ዓ.ም በዓለም ለ36ኛ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ31ኛ ጊዜ “ምግብ እንጂ ትምባሆ አንፈልግም” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ የመድኃኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን