ወንድሜ እንዳለጌታ ሰላም ይሁንልህ፤

Date:

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

በመጽሐፍት ዙሪያ በምታዘጋጀው ዝግጅትህ ከ60ዎቹ ትውልድ ጋር የምታደርገው ወግህን እከታተላለሁኝ። በዚህ ሳምንትም የኢሕአፓ አባል ከሆኑት ከወ/ሮ ነጻነት መንግሥቱ ጋር ያደርግኸው ውይይት እጅግ ቀልቤን ሳበውና በኢሕአፓ ታጋዮች ዙሪያ አንድ ገጠመኜን ላካፍልህ ወደድኹ። 

መቼም ያ ትውልድ ታሪኩና ገድሉ ትንግርት ነው… በገሃዱ ዓለም፤ በእናት ምድር- በኢትዮጵያችን መሆኑን፤ መከሰቱን እስክንጠረጥር ድረስ ይሄ እንዴት ሊሆን ይችላል የሚያስብሉ በርካታ የታሪክ ሰበዞች ያለው እንቆቅልሽ የሆነ ትውልድ ነው፤ ለወጌ ፈር ማስያዣ ይሆነኝ ዘንድ ከዛ ትውልድ ጋር የተያያዘ አንድ ገጠመኜን ላንሳ።

ከጥቂት ዓመታት በፊት በመቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን ማእከል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አስተባባሪ ሆኜ አገልግል ነበር። ታዲያ አንድ ቅዳሜ ማለዳ ዕድሜያቸው በ70ዎቹ መጀመሪያ የሆኑ ሰው ወደ ቢሮአችን መጥተው ነበር። የመጡበት ዓላማ ደግሞ ቤታቸውን ለመቄዶንያ አውርሰው ቀሪ ዘመናቸውን በማእከሉ እያነበቡና እየጻፉ ለመኖር እንዲችሉ ዶ/ር ብንያምን ለማነጋገር ነበር። 

እኚህ አባት በኮተቤ የትምህርት ኮሌጅ ተመርቀው በወለጋ የቋንቋና የኅብረተሰብ አስተማሪ ሆነው ሠርተዋል። በመምህርነት ዘመናቸውም የቀድሞ የአገራችን ፕ/ት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ አንዱ ተማሪያቸው ነበሩ።

ከአስተማሪነት ሥራቸው ላይ ሆነው ነበር ኢሕአፓን የተቀላቀሉት። የኢሕአፓ መሪ አባል፤ በጎንደር እንፍራዝ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ሰራዊት/ኢሕአሰ ጦር አመራር የነበሩ ናቸው።

ኢሕአፓ ለትጥቅ ትግል ወደ በረሃ ሲገባም የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ሰራዊት/ኢሕአሰ የጦር አባልና አመራር ሆነው ከወለጋ ወደ ጎንደር/እንፍራዝ ተጓዙ። በደርግ መንግሥት ተይዘው ወደ ወኅኒ እስኪገቡ ድረስም የኢሕአሰ ታጋይና አመራር ነበሩ።

ከእስር ቤት ከወጡ በኋላም አስተማሪ፤ የቤተመጻሕፍት ኃላፊ፤ ነገረ-ፈጅ፤ ለአጭር ጊዜ ደግሞ ፍሪላንሰር ሆነው ሠርተዋል። በኋላኛው ዘመናቸውም በሁመራ በጥጥና በሰሊጥ ግብርና ሥራ ላይ ተሰማርተው ነበር።

ግና እኚህ ሰው የግብርና ኢንቨስተር ለመሆን ገና መንገዱን እንደጀመሩ በ2ኛው ዓመት ላይ ወደ ሱዳን ለመላክ በጎተራ የተከማቸ የጥጥና የሰሊጥ ምርታቸው ላይ እሳት ተለቆበት እንዳለ ወደመባቸው። አዛውንቱ አባት እንዳጫወቱኝ ይሄ ክስተት ፖለቲካዊ ሤራ የነበረበት ነው። ዝርዝሩን ለሌላ ጊዜ ላቆየው። አሊያም ወደፊት በመጽሐፋቸው ያስነብቡን ይሆናል።

እኚህን አባት ይህ ያልጠበቁት ክስተት ለከፋ የጤና መታወክ አጋለጣቸው። በሂደትም ቤተሰባቸው እንዲበተን፤ ለዚህ ሥራ ለብድር ማስያዣነት ያዋሉት የታላቅ ወንድማቸው ቤት በሃራጅ እንዲሸጥ ሆነ… የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር የሆኑ ወንድማቸውም ከቤተሰባቸው ጋር ለስደት እንዲዳረጉ ሆኑ። ከዚህ በኋላ የገጠማቸው የኑሮ ምስቅልቅልና ጭንቀት ነበር ወደ መቄዶንያ ያመጣቸው።

ወጌን ላሳጥረውና ከእኚህ አባት ጋር በነበረን ቆይታ በታሪክ የማውቃቸውን የእርሳቸውን ትውልድ እያነሳን ብዙ ተጨዋወትን። በጨዋታችን መካከል ያሉኝ ነገር ዛሬም ድረስ በአእምሮዬ ታትሞ ቀርቷል።

“ወጣትነታችንን የገበርንለት ትግል ዓላማው አንድ ነው፤ ሕዝባችንን ከጭቆና ከድኅነት አውጥተን ዲሞክራሲና ፍትሕ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ!!

ግና የሄድንበት መንገድ ጦር ያማዘዘን፤ ሳንጃ ለሳንጃ የተሞሸላለቅንበት… ምድሪቱ በደም አበላ የተመታችበት፤ ኢትዮጵያችን አኬልዳማ/የደም ምድር የሆነችበት ነበር።

“ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም!!” እየተባለ የተፎከረበት የለውጥ ርምጃ/አብዮትም- አብዮት የገዛ ልጆቿን ሳይቀር ትበላለች ወደሚል አስፈሪ ፃእረ-ሞትነት ተቀየረ… ሞት በኢትዮጵያ ምድር ነገሠ…፤”

እንደ መውጫ ያለ ሐሳብ፤

ከሳምንት በኋላ ከእኚህ አዛውንት አባት ጋር ስንገናኝ በወቅቱ ከገበያ ላይ ጠፍቶ እስከ 3 እና 4 ሺሕ ዋጋ ይጠራበት የነበረውን የሕይወት ተፈራን፤ Tower in the Sky/ማማ በሰማይ መጽሐፍ በስጦታ ይዘውልኝ መጡ።

ይህን መጽሐፍ አንብበው… ኢትዮጵያችን ትፈወስ ዘንድ የጸጸት፤ የይቅርታና የምሕረት ልብ ያስፈልገናል!! 

አዛውንቱ መምህር፣ የሕግ ሰው፣ የኢሕአፓ አባል… መጽሐፋቸው የሕትመት ብርሃን አይቶ ለማንበብ ያበቃን ዘንድ በመመኘት ወጌን ልቋጭ።

ሰላም 🕊

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ኢትዮጵያ የ1 ቢሊዮን ዶላር የቦንድ ዕዳዋን ለማዋቀር ስታደርግ የነበረዉ ድርድር ያለ ስምምነት ተቋረጠ

የኢትዮጵያ መንግሥት በ2024 ዓ.ም. ዋናው ዕዳ የሚከፈልበት የአንድ ቢሊዮን...

የትግራይ ኃይል አባላት ሰልፍ ዛሬም በሌላ አቅጣጫ ቀጥለዋል

በመቐለና ዙሪያዋ የሚገኙ የትግራይ ኃይል አባላይ ትናንት ሰኞ ጥቅምት...

የምርመራ ኬዝ ስለሆነ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል

ተማሪ ሊዛ ደሳለ የተባለች ወጣት ሰሞኑን በደሴ ከተማ “...

ስቲሊ አር.ኤም.አይ ላለፉት አራት ዓመታት የፕላቲኒየም ሸልማት ተሸላሚው

የ2017 በጀት ዓመት 7ኛው የታማኝ ግብር ከፋዮች ዕውቅና እና...