ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ አራተኛ ስብሰባውን መስከረም 15 ቀን 2018 ዓ.ም አካሂዷል።
በተሻሻለው የባንኩ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1359/2025፣ አንቀጽ 23፣ በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሠረት የተቋቋመው የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ከባንኩ ዋጋን ከማረጋጋት ቀዳሚ ዓላማ ጋር የተጣጣሙ የገንዘብ ፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን ለባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ እያቀረበ ያስጸድቃል።
በዚህ ረገድ፣ ኮሚቴው የኢትዮጵያን የዋጋ ግሽበት፣ የፊስካል፣ የውጭ ኢኮኖሚ፣ የገንዘብ አቅርቦትና የፋይናንስ ዘርፍ አዝማሚያዎችን፣ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አመልካቾችን እንዲሁም በሀገር ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ አንደምታ ያላቸው ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ይገመግማል። ከእነዚህ የማክሮ ኢኮኖሚያዊ ግምገማዎችና የቅርብ ጊዜ የወደፊት ትንበያዎች በመነሣትም በቀጣይ ተግባራዊ የሚደረጉ የፖሊሲ ምክረ-ሐሳቦችን ያቀርባል።
በዚሁ መሠረት፤ ኮሚቴው በውይይቱ ያካተታቸው ዐበይት ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፡-
የዋጋ ግሽበት፡- ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት በተከታታይ እየቀነሰ በመምጣት ነሐሴ ወር 2017 ዓ.ም መጨረሻ 13.6 በመቶ ደርሷል። በኮሚቴው ግምገማ መሠረት ለዋጋ ግሽበት መቀነስ ዐበይት ምክንያቶች ብሔራዊ ባንክ ተግባራዊ እያደረገ ያለው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ፣ የግብርና ምርታማነት መሻሻል እና መንግሥት ዋጋን ለማረጋጋት እየወሰዳቸው ያሉ አስተዳደራዊ እርምጃዎች ናቸው፡ የዋጋ ግሽበትን ከፋፍለን ስናይ፤ ምግብ-ነክ የዋጋ ግሽበት ነሐሴ ወር 2017 ዓ.ም መጨረሻ 127 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ከነበረው የ18.8 በመቶ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ቅናሽ አሳይቷል። በአንጻሩ፣ ምግብ-ነክ ያልሆነ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ ጭማሪ በማሳየት 15.1 በመቶ ሆኗል።
ለዚህም በቅርቡ የተካሄደው የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥ ጫና በተወሰነ መልኩ አስተዋጽኦ አድርጓል። በተመሳሳይ መልኩ፣ ነሐሴ ወር 2017 ዓ.ም መጨረሻ ወርሃዊ የዋጋ ግሽበት ወደ 11 በመቶ ዝቅ ማለቱ የዋጋ ግሽበቱ በኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ እየቀለለ መሄዱን ያመላክታል።
የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና ዕድገት፡- ኮሚቴው የሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ ዕድገት ተጠናክሮ መቀጠሉን ተገንዝቧል። የብሔራዊ ባንክ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አመላካቾች (Composite |ndex of Economic Activities) የተጠናከረ የኢኮኖሚ ዕድገት መኖሩን ያሳያሉ።
ለዚህም በግብርናው ዘርፍ የሚታየው ምርትና ምርታማነት መጨመር፣ ከውጭ ምንዛሪ ለውጡ ጋር ተያይዞ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ምርት ማደግ፤ እንዲሁም የወጪ ሸቀጦች ንግድ በተለይም ወደ ውጭ የሚላከው ቡና እና ወርቅ ከፍተኛ እመርታ ማሳየት ለኢኮኖሚ ዕድገቱ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አድርገዋል ። በአንጻሩ፣ ወደ ሃገር ውስጥ በሚገቡ ሸቀጦች ማለትም በከፊል ያለቀላቸው እቃዎች እና የፍጆታ ሸቀጦች ላይ መቀዛቀዝ ታይቷል።
የገንዘብ ሁኔታ፡- በገንዘብ ዝውውር አመልካቾች ረገድ ፈጣን ዕድገት ተስተውሏል። ለዚህም የብድር ዕድገት ገደቡ ላላ መደረጉ እንዲሁም የፊስካል እና የውጭ ዘርፍ ዕድገት ማሳየታቸው አስተዋጽኦ አድርገዋል።
በመሆኑም፣ ነሐሴ ወር 2017 ዓ.ም መጨረሻ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚዘዋወረው የጠቅላላ ገንዘብ አቅርቦት (broad money supply) 23.1 በመቶ፣ መሠረታዊ ገንዘብ (base money) 70.7 በመቶ፤ የሀገር ውስጥ ብድር 14 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት አሳይተዋል። ከዚህ ሌላ፣ አጠቃላይ የባንኮች የብድር ክምችት ከሰኔ ወር 2017 ጋር ሲነጻጸር 5.4 በመቶ ጨምሯል ።
ለመሠረታዊ ገንዘብ ከፍተኛ ዕድገት ዋናው ምክንያት ከወርቅ ግዢ ጋር በተያያዘ የብሔራዊ ባንክ የውጪ ምንዛሪ ክምችት በመጨመሩ እና ከዚህም የተነሣ ወደ ባንኮች የገባው የብር ፍሰት መጠን ከፍ በማለቱ ነው። ይሁን እንጂ፣ የብድር ዕድገት ገደብ ፖሊሲ መኖሩ የጠቅላላ ገንዘብ ዕድገቱ የተለጠጠ እንዳይሆን አድርጎታል።
የወለድ ተመን ሁኔታ፡- የዕድገት አዝማሚያ ከፖሊሲ የወለድ ተመን ጋር የተቀራረበ መሆኑን፣ እንዲሁም የዋጋ ግሽበትን ታሳቢ ካደረገው የወለድ ተመን ጋር ሲነጻጸር ከዜሮ በላይ ሆኖ መቀጠሉን ኮሚቴዉ ተገንዝቧል። ይህም አዝማሚያ ለገንዘብ ገበያ መነቃቃት አስተዋጽኦ እንዳለው መረዳት ተችሏል።
ለምሳሌ፣ የ91-ቀን የመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ አማካይ የወለድ ተመን ሰኔ ወር 2017 ከነበረበት 17.6 በመቶ በነሐሴ ወር 2017 መጨረሻ ወደ 15.0 ዝቅ ብሏል። በተመሳሳይ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን የገንዘብ ዋጋ የሚያመላክተው የ7-ቀን የባንክ ለባንክ ግብይት አማካኝ የወለድ ተመን በሚፈለገው የወለድ ተመን ክልል (nterest Rate Corridor) ውስጥ እንዲቆይ ብሔራዊ ባንክ ከባንኮች ጋር የገንዘብ ግብይት (Open Market Operations) እያደረገ ይገኛል።
በመሆኑም፣ በነሐሴ ወር 2017 መጨረሻ የ7-ቀን የባንክ ለባንክ ግብይት አማካኝ የወለድ ተመን ወደ 13.7 በመቶ ዝቅ ያለ ሲሆን፣ ይህም ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው የወለድ ተመን ክልል ውስጥ መሆኑ ታውቋል። ጥቅምት 2017 ዓ.ም የተጀመረው በባንኮች መካከል የሚደረግ የገንዘብ ግብይት ከፍተኛ ዕድገት በማሳየት በነሐሴ ወር 2017 መጨረሻ ብር 945.1 ቢሊዮን ደርሷል።
የፋይናንስ ዘርፍ መረጋጋት፡- የባንክ ዘርፍ ዝቅተኛ የተበላሸ ብድር እና በቂ ካፒታል ያስመዘገበ በመሆኑ ጤናማና የተረጋጋ መሆኑን፣ ነገር ግን፣ በአንዳንድ ባንኮች ዘንድ በተወሰነ መልኩ የጥሬ ገንዘብ አከል (liquidity) እጥረት መኖሩን ኮሚቴው አስተውሏል። ይህም የሆነዉ በባንኮች ዘንድ በሚታየው ከፍተኛ የብድርና የተቀማጭ ሂሳብ (loan to deposit ratio) ጥምርታ ምክንያት ቢሆንም አሁን ላይ ችግሩ በባንክ ለባንክ የገንዘብ ገበያ (nterbank Money Market) እና በብሔራዊ ባንክ ዕለታዊ የብድር አገልግሎት መፍትሔ እያገኘ ነው።
የፊስካል ሁኔታ፡- የፊስካል ፖሊሲ ጥንቃቄ የተሞላበትና ከብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ጋር የተጣጣመ መሆኑን ኮሚቴው ተገንዝቧል። ልክ እንደባለፈዉ በጀት ዓመት ሁሉ በተያዘው የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ሁለት ወራትም መንግሥት ለበጀት ጉድለት ማሟያ ከብሔራዊ ባንክ ምንም ብድር አለመውሰዱ የብሔራዊ ባንክን የገንዘብ ፖሊሲ አቋም በእጅጉ የሚደግፍ ክስተት ሆኖ ቀጥሏል።
የውጭ ኢኮኖሚ ዘርፍ፡- በሐምሌ ወር 2016 ከተወሰደው ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ የውጭ ኢኮኖሚ ዘርፉ በበርካታ መመዘኛዎች ትልቅ እምርታ እያሳየ መሄዱን ኮሚቴው ተገንዝቧል። ለምሳሌ፣ በወጪ ንግድ በተለይም በወርቅና በቡና ንግድ፣ በግለሰብ ሐዋላ እንዲሁም በተጣራ የአገልግሎት ንግድ ከፍተኛ ዕድገት ታይቷል። በመሆኑም፣ የከረንት አካውንት ጉድለት ተሸሽሏል እንዲሁም አጠቃላይ የክፍያ ሚዛን ትርፍ አሳይተዋል።