“ጠየቀ ወዳጄ፤ “የUN ሰላም አስከባሪ – የሚጠበቅ ሰላም በሌለበት ሀገር እንደሚሰማራው ማለት ነው” አልኩት።
ኢትዮጵያ ሀሳብን በነፃ የመግለፅና በፕሬስ ነፃነት ወደ 145ኛ አቆልቁላሉች። እናም ይህ ዘርፍ ስለሚሻሻልበት በግልፅ መምከር የግዳችን ነው፤ ሁኔታዎች ለጋራ ሀገራዊ ሕልውና እንዲበጁን ስንል።
ኤርትራ ውራ ሆና 180ኛ በሆነችበትና ዩጋንዳ 143ኛ እንዲሁም ሩዋንዳ 146ኛ በሆኑበት ‘Reporters Without Borders’ ያወጣው አመታዊ ማናፀሪያ Index ያመለክታል።
ይዘቱን ለመለወጥ ያተኮረ ሳይሆን እንደው ቀኑን ለስሙ ያህል ለማክበር ብቻ የሚካሄድ ሁነት ሲሆን አንድ አጋጣሚን ያስታውሰኛል።
ያም የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ኃይል ሰላሟ ታውኮ ስትታመስ ወደነበረችው ኮንጎ ኪንሻሳ ተልዕኮ ተሰጥቶት ይሰማራ ነበር።
ይህንን የሚዘግበው የBBE World Service ዘጋቢ እንዲህ ሲል ነበር ሪፖርቱን የጀመረው:- “The Peace Keeping Force moving to Congo DRC where there is no peace to keep”።
(የሰላም አስጠባቂው ኃይል የተሰማራባት ኮንጎ አለኝ የምትለው የሚጠበቅ ሰላምም የላት’) በሚል ነበር ዘገባውን የጀመረው።
እናም አመታዊ የዓለም ፕሬስ ነፃነት ቀንን ለማክበር ስገኝ Paradox (ተገላቢጦሽ) የሚሆንብኝ የሌለውን ነፃነት ለማሰብ ነው ያስብለኛል።
ስለዚህም የተሸረሸረው ሀሳብን በነፃ የመግለፅ መብትና የፕሬስ ነፃነትን እንዴት እናሻሽል ላይ ነው ማተኮር ያለበት ያስብለኛል።
ለነገሩ ሚዲያው ኤችአይቪንም ተከበረ ነው የሚለው፤ የሚዳለጠው ይዘት ብዛቱን ሂሰኛ ይቁጠረውና፤ ይህ ሁነት በአዲስ አበባም ሆነ በሃዋሳ ከመከበር ይልቅ ሲታሰብ ወይ ሲዘከር ብዬዋለሁ።
አንዱ ሁነት የአዲስ አበባው “ሰው ሰራሽ አስተውሎት እያሳረፈ ያለው ጫና” ላይ ሲያተኩር፥ የሃዋሳው ዩኒቨርስቲ ያስተባበረው ደግሞ ቀኑን ‘ከመገናኛ ብዙኀኑ ሞያተኝነትና ዘርፉ ለሰላም ካለው አበርክቶ’ ለማያያዝ ሞክረዋል።
ይህ ቀን ከመገናኛ ብዙኀኑ ነፃነት በላቀ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ከተርታው ዜጋ እስከ ፖርላማውና ዓለም አቀፉ አካል ድረስ የሚሻገር በጋራ ያገባናል ሊባል የሚገባ ታላቅ አጀንዳ ነው፤ የነእከሌ ተብሎ ለአንድ ቡድን ተትቶ የራሳቸው ጉዳይ የምንለው አይደለም።
መገናኛ ብዙኀኑ ከጎጇችን ቤተሰብ ጀምሮ እስከ መንግስቱ መናኸሪያ ፓርላማ ድረስ እየነዋወጠን እያሳረፈ ያለውን ሕመም ያህል እንዴት ትኩረት ሊሰጠው አልቻለም በሚል ራሴን ጠይቄ ምላሽ ያጣሁለት የከረመ ጭንቀቴ ነው።
ይህ ጉዳይ ለምን የመንግስታዊ አስተዳደሩ ትኩረት ሊሆን እንዳልቻለ ግራ ይገባኛል፤ የሕገ መንግስቱ አንኳር ጉዳይ እኮ ነው።
በአብዛኛው ይህ ሃሳብን በነፃ የመግለፅ እና የፕሬስ ነፃነት ሲታሰብ ወሳኝ የመንግስት አካላት ሲገኙ አላይም።
በግልፅ ለዘርፉ ከተሰጠው አነስተኛ ግምት ይሆን እላለሁ፤ በሌላ በኩል ደግሞ እነኚሁ አካላት በፖርላማ ጭምር “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” ብለው ተረት ይጠቅሳሉ የዘርፉን ከፍ ያለ አጀንዳነት ሲያሳስቡ።
በሌላ በኩል በዓለም ለእንደዚህ ጊዜ፥ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ _ ኛ ጊዜ ተብሎ ለይስሙላ ከሚዘከር ምናለ በደንብ ታስቦበት የዘርፉን ሁሉን ደረስ ሕመምና መፍትሔዎችን ያካተተ ጥናት፥ ምርምር፥ ዳሰሳና ቅኝት ሰነድ ቀርቦ ለችግሮች መላ ሊያስገኝ በሚችል የፕሮጀክት አቅም ደረጃ ታስቦበት ቢከናወን እላለሁ በቁጭት።
“በቦሃ ላይ ቆረቆር” እንዲሉ መደበኛ መገናኛ ብዙኀኑ የሚራመዱበትን ሁኔታ በቅጡ የሞያ ሀዲዱን ጠብቀው መጓዝን ሳይፀኑበት ዘርፉ በውጭ እና በውስጥ ተፅዕኖ ከአደጋ ሊወጣ አዳግቶታል።
ቴክኖሎጂው በብርሃን ፍጥነት እየተጓዘ ዲጂታል በዜጋ ጋዜጠኝነቱ መስፋፋት ማህበራዊ ሚዲያው ተቃንቶ መጓዝ አቅቶት ሲንገዳገድ ሳለ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ጭራሽ የDeep feck ቴክኖሎጂ አማራጭን ከች አድርጎ እውነተኛውን ከአሳሳቹ መለየት የተቸገርንበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።
መንግስት ዛሬም የመረጃ ልጓም ይዞ የበላይ ተቆጣጣሪ መሆኑን እንዳጣ ለመቀበር አንገራጋሪነት ይታይበታል። የታፈነ መረጃ ተባራሪ ወሬ ሆኖ ወይ በመላ ምትነት የመውጣቱን መራር ሀቅነት ለመረዳት መቸገር የለብንም።
ባለሶስትዮሽ ማዕዘኑ ለውጥ (Trianguar Shifts) ሚዲያውን ግራ አጋብተውት በማዕበሉ መልዕቁ አጥቷል።
1ኛው ጫፍ – የታዳሚ ባህሪ እጅግ መለወጥ (Audience behavior shift) ነው፤ ዓለም እጅግ በቴክኖሎጂ ተሳስራ ሰው በየዕለቱ በፈጣን እንቅስቃሴ ውስጥ ነውና ለሚዲያ ሰአት ጠብቆ የሚከታተልበት ዘመን ተለውጧል።
2ኛው ጫፍ – የቴክኖሎጂ በተለይም የዲጂታሉ ፈጣን ተለዋዋጭነት – (the fast changing digital technology) – ይህ ደግሞ በቤትና ቢሮ ዙሪያ የነበረ በሬዲዮና ቴሌቪዥን አማካይ የመረጃ ልውውጥን ወደ እንቅስቃሴ ፈጣኑ በእጅ ስልክ አማካይ ተክቶታል፤ የሰዎች በአካል መገናኘትን ቀይሮት ቨርቹዋል አድርጎታል።
3ኛው የትሪያንግሉ ጫፍ – የገበያ ፉክክሩ ፈተናና የተመራጭነት ትኩረት መቀየሩ ነው – (Market competitiveness – shift to alternative new media) – ከፍጥነት፥ ከጥራት፥ ከዋጋ፥ ከተገማችነት፥ ከተደራሽነትና ውጤታማነት አንፃር ለክትትል አመቺ ካልሆነው መደበኛ ሚዲያው ይልቅ ዲጂታሎቹ ተሽለው የመገኘታቸው ጉዳይ ገበያውን እያሸፈተው ነው።
ዛሬ ላይ ማስታወቂያ አስነጋሪ የአምራችና የአገልግሎት ኢንዱስትሪዎቹ ጭምር በቀጥታ ራሳቸው ባበጁት የግል የዌብሳይት፥ ማህበራዊ ሚዲያ ትስስሮች ጭምር በራሳቸው የዲጂታል ሚዲያ አማራጮቻቸው መመካት ስለጀመሩም መደበኛ ሚዲያውን የሚፈልጉበት አጋጣሚ እየመነመነ ነው።
አሁን ጭራሽ ከAI generated የይዘት ቅንብር አንስቶ እስከ ጥናትና ምርምር ድረስ በዚህ እየተሸፈነ ሞያተኛ በአርተፊሺያል ድጋፎች እየተተካ ከስራው የሚፈናቀሉ ሞያተኞች እንደሚበዙ ይጠበቃል።
እነኚህ ፈተናዎች ተደማምረው ሕብረተሰብ የተለያዩ አማራጭ ሀሳቦች በመድብለ ሚዲያዎች ቀርበውለት መረጃ ላይ ተወስኖ ውሳኔ እንዲያሳልፍ (community taking an informed decision based on diverse ideas via plural multi media services) አገልግሎት መስጠት የሚጠበቅባቸውን መገናኛ ብዙኀን ዛሬም ፋይዳ ያላቸውና በገቢም ዘላቂ (Relevant and Viable) የሚሆኑበትን ድባብ እንዴት እንፍጠርላቸው የሚለው ጥያቄ አንገብጋቢ አጀንዳ ነው።
የሀገሪቱ ሰላም እና ዲሞክራሲ ጤና ዋነኛ ማመላከቻ የሆነው የመገናኛ ብዙኀኑ ሕመም የዘርፈ ብዙው ሀገራዊ ሕመም ነፀብራቅ ነውና የፕሬስ ነፃነትን ችግር ሚዲያው ጋ በመዞር ብቻ የሚፈታ አይደለም፤ ይልቁንም የጥቅል ስርአትና መዋቅሩ ችግር መገለጫ ነው።
እናም ለሕመም ምልክቱ ማስታገሻ ክኒን በመስጠት ብቻ ደዌው አይፈወስም።
እንደ 4ኛ የመንግስት ክንፍ ለሚቆጠረው በእውቀትና ምግባር ለሚመራው ፕሬስ – ነፃነቱ እንዲጎመራ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ባለድርሻዎች ሁሉ በጋራ በፅኑ ሊቆሙ ግድ ይሆናል።
ከእሸቱ ገለቱ