የአረጋውያን መብት ጥበቃ፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ በዝግጅት ላይ መሆኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ ይህን ረቂቅ አዋጅ በፍጥነት ወደ ተግባር ለማስገባት የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሰራሁ ነው ብሏል፡፡
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአረጋውያንና ቤተሰብ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ሮበሌ፤ ለአዋጁ ግብዓት የሚሆኑ ሐሳቦች ከተለያዩ ባለሙያዎች ተሰብስበዋል ።
የተነሱት ሐሳቦች እስከ ጥቅምት 15 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ ለፍትሕ ሚኒስቴር እንዲቀርቡ ለማድረግ እና ረቂቅ አዋጁ በአፋጣኝ ወደ ተግባር እንዲገባ ለማድረግ ሁኔታዎች እየተመቻቹ እንደሆነ ተናግረዋል።
መሪ ሥራ አስፈጻሚው እንዳሉት፤ አረጋውያን በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑና የመብት ጥሰት እንዳይደርስባቸው የሚያስችል አስገዳጅ ሕግ በተደጋጋሚ ሲጠየቅ የነበረ ጉዳይ ነው።
በኢትዮጵያ ከ7 ሚሊዮን በላይ አረጋውያን የሚገኙ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከልም 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚሆኑት ለተለያዩ ችግሮችና ለመብት ጥሰት እንደሚጋለጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
“በአረጋዊያን ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመፍታት የአስገዳጅ የሕግ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልግ በማመን በሂደት ላይ የሚገኘው ረቂቅ አዋጅ በአፋጣኝ ወደ ተግባራዊ እንዲደረግ እየተሰራ ነው” ሲሉም አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል።
አክለውም ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ አረጋውያን ለተለያዩ ችግሮችና ለመብት ጥሰት እየተጋለጡ በመሆኑ ምክንያት፤ በሁሉም ዘርፍ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ ተደራጅተው እንዲሰሩና የሚደርስባቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመከላከል የሚያስችለው ሕግ በፍጥነት ተግባራዊ መደረጉ በርካቶችን ይታደጋል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
(አሐዱ ሬዲዮ)