‹‹አንዳንዴ በኢትዮጵያዊ ድክመታችን እቆጫለሁ››
‹‹ንጉሠ ነገሥቱ ‹ያ ጽጌ ቢኖር ኖሮ› እያሉ ያዝኑ እንደነበር ሰምተናል››
ውድ አንባቢያን፣ ባሳለፍነው ዕትም ከአቶ አታመንታ ጽጌ ዲቡ ጋር ባደረግነው ቆይታ፣ ከአያቶቻቸው ጀምሮ ሲወርድ ሲወራረድ ስለመጣው የአርበኝነት መንፈስ፣ አባታቸው ብርጋዴር ጄነራል ጽጌ ዲቡን አስመልክቶ ለረጅም ዓመታት የደከሙበትን መጽሐፍ ያሰናዱበትን አግባብ በተመለከተ ሰፋ ያሉ ሐሳቦች ማንሳታችን ይታወሳል፡፡ በሁለተኛው እና በመጨረሻው ክፍል ዕትማችን ደግሞ ከአባታቸው የአሟሟት ሁኔታ አንስቶ፣ ከእርሳቸው አሰቃቂ ሕልፈት በኋላ ሕይወት በምን መልኩ እንደቀጠለ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ የሚከተለውን ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ!
ግዮን፡- የጀነራል ጽጌ ዲቡ አሟሟት እንዴት ነው?
አታመንታ፡- ጀነራል ጽጌ በዚያ በንቅናቄዉ ወቅት ገና ከጅምሩ ከሚያዙት ከፖሊስ ሠራዊቱ በታች ዕዝ ተቆርጠው እንዲወጡ ተደርገው ነበር፡፡ የሚገርመው እና እስካሁን ሰው የማይጠይቀው ግን ለምን ንቅናቄው ሲጀመር ጀነራል መንግሥቱ ከክቡር ዘበኛ መምሪያ ወደ 10 የሚጠጉ ወታደሮች ብቻ ይዘው ወደ እቴጌ ቪላ ሄደው ጦር ሠራዊቱ አምጿል በማለት ለድርድር መያዣ ቢታሰቡ እና ቢታሰሩ እንኳን ይኽንን ያህል ለወቅቱ ለተጀመረዉ ንቅናቄ ስኬት የሚያስፈልጉትን ዋኖቹን ትተዉ የማያስፈልጉትን ባለሥልጣናት ማሠር መጀመራቸውን ነው፡፡ እቴጌ መነንም ትንሽ ቀድም ብለዉ ከእራት በኋላ ወደ ቤታቸዉ ከሄዱት ከልዑል ሣሕለ ሥላሴ በቀር እዚያዉ ከቆዩት ከልዕልተ ተናኘወርቅ ኃይለሥላሴ፣ ከልዕልት ሣራ ግዛዉ፣ ከአባ ሃና ጂማ፣ ከራስ አንዳርጋቸዉ መሳይ እና ከሌሎችም ጋር እራት ከተነሳ በኋላ አብረው ፊልም ለማየት ተቀምጠዉ ነበር፡፡ በዚያን ሰዓት ላይ ለቤተ መንግሥቱ፣ ለእቴጌ ቪላ እና ለክብር ዘብ መምሪያ በጣም በቅርብ ከሚገኘዉ የአልጋ ወራሽ ግቢ ልዕልት መድፈሪያሽ ወርቅ የአልጋ ወራሽ ባለቤት፣ ደጃዝማች ከበደ ተሰማ፣ ደጃዝማች አሥራተ ካሣ፣ ባምባራስ ማሕተመ ሥላሴ፣ ፊታውራሪ ወርቅነህ ወልደአማኑኤል እና ካፕቴን ኃይሉ የመሳሰሉት በሙሉ ተሰብስበዉ ነበር፡፡ ጀነራል መንግሥቱ ይህን ሲያካሂዱ መጀመሪያ መያዝና ማሠር ያለባቸው ንጉሡን ባለቤት፣ ልጆቹን፣ ዋና ዋናዎቹን የጦር መሪዎች ነበር፡፡ እሳቸው ግን እነዚህን በሙሉ አንዳቸውንም አልያዙም፡፡ ለምን? ስለዚህ መፈንቅለ መንግሥቱ በጥቅሉ ንጉሠ ነገሥቱን ለመገልበጥና አሁን ድረስ በብዙ በተቃዋሚ ድርጅቶች እንደሚታየዉ ሀገሪቱን በማይሆን የፖለቲካ እሳቤ አፈራርሶ ሌላ ለማቆም ሳይኾን ኋላቀር እና እንቅፋት የሚሏቸዉን ባለስልጣናት በሰላም አስወግደዉ፣ የነበረውን መንግሥት በሕግ በተወሰነ ሞናርኪ ሥርዓት አስቀምጠው ሀገሪቱ በፓርላሜንት ሥርዓት እንድትተዳደር ነበር፡፡ የሀገሪቱ ሁኔታ እና አቅም በጊዜዉ የሚፈቅደዉም ይኸዉ ነበር።
ያ እንዳይሳካ እና እንዳይኾን እንቅፋቱ ማነው? እነማን ናቸዉ? የሚለው ግን ዋናው መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ አማጽያኖቹ የንጉሣዉያኑን ቤተሰቦች ትተዉ እና አስጠብቀዉ እዚያዉ እቴጌ ቪላ የታገቱትን መኳንንቶች ይዘዉ ክብር ዘብ መመሪያ ሄዱ። እዚያም ቆይተዉ በነጋታዉ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የንቅናቄዉን መመሪያ አዙረዉ የሚወስዷቸዉን እርምጃዎች ማካሄድና መቆጣጠር ጀመሩ። ገንዘብ ሚኒስቴር ደርሰው ወደ ገነተ ልዑል ቤተ-መንግሥት የሄዱት በከተማዉ መብራት ስለተቋረጠ መብራት ያለው እዚያ ስለኾነ ነው እንጂ እዚያ የመሄድ እቅድ አልነበራቸውም፡፡ ከተማ ውስጥ መብራት ሲጠፋ ቤተ መንግሥት ግን ጄኔረተር ስለነበር ነዉ፡፡ ለዚያ ነው እዚያ የገቡት፡፡ ድርድር የተጀመረው ከዚያ በኋላ ነው፡፡ እነ ጀነራል መርዕድ መንገሻ ተሰብስበው አራተኛ ክፍለ ጦር ኾነዋል፡፡ የጦርን እና ሲቪል ለዉጥ ተቃዋሚዎቹ ሁሉቱም ቡድኖች አንድ ላይ ኾነው በአንድ ጊዜ በጥቂት ሰዓታት ዉስጥ ተስማምቷል፡፡ ይህ ሁሉ መረጃ በአንድ ጊዜ እንዴት ጥርት ብሎ ሊታያቸዉ ቻለ? ሰዎቹ በአብዛኛው ተዘጋጅተው ይጠብቁ ነበር፡፡ የክብር ዘበኛ አባላት መረጃውን ያውቃሉ፡፡ ንቀናቄዉ ከተጀመረ በኋላ ከዕረቡ ምሽት ጀምሮ ብዙዎቹም የክብር ዘበኞች ግዳጃቸዉን እየጣሉ ሄደዋል፡፡ ገና ከጅምሩ ፖሊስ ሠራዊትና ጦር ሠራዊት በአንድ ቆመዋል፡፡ ጦርነቱ ሃሙስ ታሕሳስ 6 ቀን 1953 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ስምንት ሰዓት ላይ ተጀመረ። ይኽ ከመሆኑ በፊት የጦር ሠርዊቱ ኃይል ወደ አዲስ አበባ ከተማ በተለያየ አካባቢ እየገባ ነበር፡፡ አማጽያኖቹ ላይ የተካሄደዉ ድብደባውም በእግረኛና በአየር ኃይል የተጠናከረ ነበር፡፡ የአሜሪካ አምባሳደርም በየመሐሉ ከቤተ መንግሥት ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር ይመላለስ ነበር፡፡ በነጋታዉ እንዲሁ ቀጥሎ ዉሎ በዚህ መሃል እነ ጀነራል መንግሥቱ ነዋይ ‹‹ሁሉም ነገር ከቁጥጥር ውጪ ኾኗል፤ የሚያዘልቅ አይደለም፤ መውጫ ካገኘን ሰዎቹን ለቀን እንወጣለን፤ ለአስር ለምንሆነዉ መውጫ መንገድ ክፈቱልን›› ብለው ለእነ ጀነራል መርዕድ መንገሻ መልዕክት ይልካሉ፡፡ ያገኙት መልስ ግን “ለሰራችሁት ሥራ ለፍርድ ትቀርባላችሁ፣ መዉጫ መንገድም አይከፈትላችሁም፣ እስረኞቹንም ፈትታችሁ አስረክቡ እጃችሁን መስጠት ብቻ ነዉ ያላችሁ ምርጫ” የሚል ድፍን መልስ ነበር። ማንም እንደሚያዉቀዉ እንኳና በዚያ መልኩ የተካሄደ ጉዳይ ይቅርና ተራ ወንጀለኛ አንድን ሰዉ እንኳን ቢያግት ሰዉየዉን ለማስለቀቅ መጀመሪያ በድርድር እና በንግግር ለመስማማት ተሞክሮ የመጨረሻዉ ምርጫ አደገኛ እየሆነ ከመጣ ብቻ ነዉ የመጨረሻዉ እርምጃ የሚወሰደዉ። እነ ጄኔራል መርዕድ መንገሻ ግን አልጋወራሹ፣ ራስ እምሩ፣ ራስ ስዩም ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ ወዘተ… በሙሉ ታግተዉ ቤተመንግሥቱን ለአንድ ሀገር ለማጥቃት በሚያስችል ጦር ያለምንም ማስጠንቀቂያ በአሜሪካን ወታደር ኃይል ታግዘዉ በአውሮፕላን፣ በታንክ በመድፍ እና በእግረኛ ጦር መደብደባቸዉ፣ ሁሉንም አንድ ላይ ለመጨረስ የወጠኑት እርምጃ ነበር። ድብቅ አጀንዳቸዉ ይኸዉ ነበር። ይኽ ሁሉ አላስፈላጊ ኃይል እና እርምጃ የተወሰደባቸዉ በዚህን ወቅት ከጠባቂዎቻቸው ጭምር በገነተ ልዑል ቤተመንግሥት የነበሩት በቁጥር ከ20 አይበልጡም ነበር። ሲጀመርም በቅጡ ለሚያዉቃቸዉ ለእነሱም እጅ የሚሰጡ አልነበሩም።
የአሜሪካኑ አምባሳደር 4ኛ ከ/ጦር ሄዶ ለጥያቄያቸዉ መልስ ይዞ ሲመለስ የጦር አውሮፕላን መጥቶ የጥይት ናዳ ያርከፈክፍባቸዋል፡፡ የአሜሪካው አምባሳደርም በጀርባ በኩል በአቶ ከተማ ይፍሩ ቢሮ በመስኮት ዘሎ አምልጦ ወጣ፡፡ እነ ኮ/ል ወርቅነህም በዚያው አምልጠው ሄዱ፡፡ ጦርነቱ አንድ ሰዓት በላይ ከተካሄደ በኋላ በኋላ ጀነራል መንግሥቱ ቃል በቃል ለእነ ሻለቃ ያሬድ ቢተው እና አብረዋቸዉ ለነበሩት፤ ‹‹እዚህ ዝም ብለን ከምናልቅ እንውጣ›› ብለው ተናገሩ፡፡ ያኔ የእኛ አባትም ‹‹እኔ የትም አልሄድም፤ የምትሄዱ ሂዱ፣ መጀመሪያዉኑ መደረግ የነበረበትን ነግሬያችሁ ነበር፤›› አሏቸው አሉ፡፡ ቀደም ብሎ ሐሙስ የጦር መምሪያዉን ወደ ገነት ልዑል ቤተመንግሥት ከማዛወራቸዉ በፊት ገንዘብ ሚኒስቴር እንደተቀመጡ አንድ ሻለቃ ጦር አዲስ አበባ ኬላው ላይ ተያዘ፡፡ ያን ጊዜ ጀነራል መንግሥቱ ነዋይ፣ ኮ/ል ወርቅነህ ገበየሁ እና ሌሎችም አንድ ላይ ኾነው የታገተዉን ጦር ለማነጋገር ሲሄዱ የእኛ አባት ከወንድማማቾቹ ከአቶ ገርማሜ ወንዳፍራሽ እና ከአቶ አምዴ ወንዳፍራሽ ጋር አንድ ክፍል ውስጥ ነበሩ፡፡ ያን ጊዜ አባታችን ለእነአቶ አምዴ ወንዳፍራሽ ‹‹እነ ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይን፣ ኮሎኔል ወቅነህ ገበየሁን እና አቶ ገርማሜ ነዋይን ይሄ ነገር የሚቋጨው ተቃዋሚዎቻችን በቁጥጥር ስር ሲውሉ፤ ወይም እነርሱ ወደ እኛ ሲመጡ ብቻ ነው፡፡ እነርሱ ወደ እኛ እንደማይመጡ አስታውቀዋል፡፡ ስለዚህ እርምጃ አሁኑኑ መውሰድ ይኖርብናል ብላቸዉ እነጀነራል መንግሥቱ አልጋ ወራሹ እና ሌሎቹም ደም መፋሰስ ይኾናል ብለው እምቢ አሉ›› ብለዉ እንደነገሯቸዉ ይህንን ቃላቸዉን በቪዲዮ ሰጥተዉናል። ይኼን ጄኔራል ወልደሥላሴ እና የጦር ሠራዊቱ ዋና አዣዦችም በመገናኛ በመጥለፍ መረጃውን ይሰሙ ነበር፡፡ ጄኔራል ወልደ ሥላሴ በረካ እንድሚሉት ‹‹እናንተ አባታችሁን በፍጹም አታዉቁትም፣ አንዴ ላመነበት እና ለቆረጠበት ለእናንተ እንኳን ቢሆን አይመለስም። እሱ እንዳሳስባቸዉ ቢሆን ኖር፣ እጅ መስጠት፣ መሮጥ ወይም እዚያዉ ማለቅ ብቻ ነበር የነበረን ምርጫ›› ብለዉናል። አባታችን ለአመኑበት ነገር እንደማይመለሱ አስቀድሞ የታወቀ ነበር፡፡ እሳቸዉ የመከሩትን እነመንግሥቱ ነዋይ ባይቃወሙ ኖሮ ነገሮች በአጭር ጊዜ ደም ሳይፈስ ወድያዉኑ ይቋጩ ነበር፡፡ ስለዚህ የእኛ አባት ከእነ ጀነራል መንግሥቱ ሐሳብ የተለዩት ያኔዉኑ ከጅምሩ ማክሰኞ ማታዉኑ ነበር፡፡ ከመፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎቹ ተለዩ፡፡ ሥራቸውን እንደ ልጆች ጨዋታ ቆጠሩት፡፡ እዚያ ያሉትም እንደ ነገሩን አባታችን እነመንግሥቱ ከገነተ ልዑል ቤተመንግሥት ለቀዉ ሲወጡ እኔ አልወጣም ብለው መሳሪያቸውን ይዘው በመስኮት በኩል ከ2 ሰዓታት በላይ ለብቻቸዉ ከጦር ሰራዊቱ ጋር ተዋግተዋል፡፡ ከጦር ሠራዊቱ ጋር ብቻ ለብቻ ነበር የሚታኮሱት፡፡ አባታችን ሲበዛ አልሞ ተኳሽ ናቸው፡፡ እሳቸው ብቻ ሳይኾኑ ታላቅ ወንድማችን ቴዎድሮስ ጽጌም አልሞ ተኳሽ ነበር፡፡ ፈጥኖ ደራሽ ግቢ የተኩስ ዉድድር ሲኖር እሱም እዚያዉ ካለ ሁለቱ አንድ ቡድን አይመደቡም ነበር፡፡ የኾነው ኾኖ ሁለት ሰዓት በላይ ሲታኮሱ ቆይተው መጨረሻ ላይ ጥይት ሲጨርሱ ራሳቸውን ገደሉ፡፡ ከዚያ እነ ኮሎኔል ጃገማ ኬሎ፣ ጀነራል ወ/ሥላሴ በረካ ኾነው ሄደው እንዳዩት ‹‹ጽጌ የሞተው በሙሉ ጥይቱን ጨርሶ መትረየሱን ደረቱ ላይ አድርጎ ነበር የተገኘዉ። እሱ የሞተበት አካባቢው በሙሉ በባዶ ቀለሃ ሞልቶ ነበር ያገኘነዉ፡፡ እሱ እራሱን ነው የገደለው የምንለው ለዚያ ነዉ›› ብለዋል። በተጨማሪ ከቤተመንግሥቱ ውስጥ ወደ ዉጭ የሚተኮሰዉ ጥይት ከቆመ ከብዙ ጊዜው በኋላ በጣም በጥንቃቄ ወደፊት እየሰለሉ የሚያስሱት የጦር ሠራዊት ወታደሮች ወደ ቤቱ ሲጠጉ ከሞት የተረፉት ራስ አንዳርጋቸዉ መሳይ አግኝተዋቸዉ ሁሉም እንደ ሄዱ እና ማንም እንደ ሌለ ነገሯቸዉ። ይኽ በጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ ፍርድ ላይ ቃል የሰጡት ነዉ። እነ መንግሥቱ ነዋይ ግን ከሁለት ሰዓት በፊት ቤቱ እና ግቢዉን ለቀዉ ሄደዉ ነበር። ጄኔራል ጽጌ ክሁለት ሰዓት በላይ ጦር ሠራዊቱን ገትረዉ ባያቆሙት ኖሮ እነጄኔራል መንግሥቱ እሩቅ ሳይሄዱ ይያዙ ነበር። የጦር ሰራዊቱ ሁሉም መሪዎች እዚያዉ የነበሩ መስሏቸዉ ነበር። ሌሎች የዙፋኑ ተቀናቃኞች በህቡዕ የተደራጁ የራሳቸዉን የቆየ ሴራ አመቺ ጊዜ በመጠበቅ ለመተግበር ሲዘጋጁበት የነበረዉን እቅድ በዚህ ክስተት በተደራቢ ደረጃ አካሂደዉ ስላልተሳካ ብዙዎች አልቀዉ ባሰቡት መንገድ ዉጥን ግባቸዉ ስለተሰናከለ እንዳይጋለጡ ወዲያዉኑ ለአልጋዉ ታማኝ በመሰል ዋና ተበቃይ ሆነዉ ቀረቡ።
ግዮን፡- እሳቸው ካረፉ በኋላ ሁኔታዎች ምን ይመስሉ ነበር?
አታመንታ፡- ጦር ሠራዊቱ ቤተ መንግሥቱ ውስጥ ከገባ በኋላ የወደቁትን አንስተው የእኛን አባት አስክሬን ደግሞ በመኪና አስረው በማርቆስ በር በኩል እየጎተቱ ይዘዋቸው ወጡ፣ ወስደውም ድልድይ ውስጥ ጣሏቸው፡፡ ከዚያ በማንሳት እንደገና ጊዮርጊስ አደባባይ ወሰዷቸው፡፡ ይህም ሳይበቃ በቆሻሻ መኪና አንስተው ኢትዮጵያ ሆቴል እና መከላከያ ሚኒስቴር አካባቢ ወስደው ታንክ ላይ አስተኟቸው። በመቀጠልም አስከሬናቸዉ በዘልማዱ መሿለኪያ ድልድይ ከላይ በሚያልፈዉ ብረት ሃዲድ ላይ ገመድ ወጥረዉ አስረዉ አስከሬናቸዉን ሰቀሉ። በዚህን ጊዜ በድን ሰዉነታቸዉ ላይ በተፈጽማባቸዉ አስክፊ እና አጸያፊ እንግልት ለመስቀልም ዳግቷቸዉ ነበር፣ ቀጥለውም ከዚያም በማንሳት አራተኛ ክፍለ ጦር ፊት ለፊት ለሕዝብ እንዲታዩ የባቡር ሀዲዱ ላይ ወስደው ዘረሯቸው፡፡ ይህን ያደረጉት ቀኑም እየመሸ ስለነበር ባቡር ጨፍልቋቸው እንዲያልፍ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሲኾን ሰው አስክሬናቸውን በድንጋይ እየደበደበና እየተሳበደ ነው፡፡ ሁኔታውን የተከታተሉት አንድ ሰው በቅርቡ እንደነገሩን ‹‹ሁኔታውን ስናይ ሀዲዱ ላይ ዘርግተዋቸዉ አየን፡፡ እየመሸም ስለነበር ከሩቅ የባቡር ድምጽ ሰለሰማን ለምን ከዚህ አይነሱም ብንል የከበቡትን ወታደሮች ስንጠይቅ ባቡር እንዲጨፈልቃቸዉ ነዉ አሉን። እኛም ይኽ የክርስቲያን ሥራ አይደለም ብለን የቀን ሠራተኞች በማስተባበር በእንጨት ተሸክመን ወደ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን ወስደን እንደ ነገሩ አፈር አበስ አበስ አድርገን ቀበርናቸው›› ብለዋል፡፡ የእኝህ ትልቅ ሰዉ እማኝ ምስክርነት በቪዲዮ ተቀርጿል፡፡ ቪዲዮው በቅርቡ ይለቀቃል፡፡
ግዮን፡- ይፋዊ የቀብር ሥርዓታቸው የት ኾነ?
አታመንታ፡- ምንም ይፋዊ የቀብር ሥርዓት አልተካሄደም፡፡ ቤተሰብም ምንም የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ እኔም በየጊዜው ቄርቆስ ቤተክርስቲያን እሄዳለሁ፤ ግን ምንም ነገር የለም፡፡ ወንድሜም እህቴም በተደጋጋሚ ለማየት ሞክረው ነበር፤ ምንም ማግኘት አልተቻለም፡፡ ይህ በመኾኑም ለአባታችን ማስታወሻ ይኾን ዘንድ በእናታችን መቃብር ላይ የአባታችንንም ምስል ለማስታወሻ አካተነዋል፡፡ የእናታችን መቃብር መጀመሪያ እስጢፋኖስ ነበር፡፡ በኋላ ግን ቤተክርስቲያኑ ሲታደስ በአንዳንድ ተቃዋሚዎች የእናታችን አጽምም እንዲወጣ ተደርጎ አሁን ያሉበት ኮተቤ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ተቀበረ፡፡
ግዮን፡- ከአባታችሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የአባታችሁ ቤተሰቦች የተለየ ጥቃት ደርሶባቸዋል?
አታመንታ፡- የአባታችን ዘመዶች አብዛኞቹ በጣሊያን ጊዜ አልቀዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ከታኅሣሱ ግርግር ወዲህ ሙሉ በሙሉ ከእኛ ተነጠሉ፡፡ ምክንያቱም እኛ በዚያ ወቅት እንደመንግሥት ጠላት ስለምንታይ የእነርሱ ከእኛ ጋር መታየት አደጋ አለው ብለዉ አስበዉ ይሆናል፡፡ ከኛ ጋር የዘለቁት በጣም ጥቂት ናቸዉ፡፡ የተቀሩት ግን እነማን እንደሆኑ አናዉቃቸዉም። ጥቅምም የለዉም። በዚያ ፈታኛ ጊዜ አብሮ ካልቆመዉ ብዙዉ ዘመድ ይልቅ ባይተዋሩ ትልቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእኛ ቆመልን።
ግዮን፡- መጽሐፉ ለንባብ ከበቃ በኋላ የአንባቢው አስተያየት ምን ይመስላል?
አታመንታ፡- በመጀመሪያ መጽሐፉ ለሕትመት በቅቶ ለአንባቢያን እንዲደርስ የተፈለገው ለ60ኛ ዓመት የታኅሣሱ ኩዴታ ለማስታወስ ነበር፡፡ ነገር ግን እኛ በርብርብ ጨርሰን ለአሳታሚዎች አዲስ አበባ ብንልክም እነርሱ የእኛን ከማተም ይልቅ አዘገዩት፡፡ አልፎም ከላክልናቸው ውጪ ያልታረመዉን አትመው አወጡት፡፡ እንደ ደንቡ ማንኛዉም አሳታሚ ድርጅት ለጸሐፊዉ አካል ለግምገማ እና ለጥራት ፍተሻ የታዘዘዉ ለስርጭት ከመታተሙ በፊት አንድ መጽሃፍ ማቅረብ ግዴታም ደንብም ነዉ። ይህንን አስታሚዉ ድርጅት አላደረገም። ከሚያስፈልገዉ ጊዜ እጅግ በላይ ወስደዉ የታዘዘዉን ያህል አምጥተዉ ሰጡን። በጊዜዉም ለሕትመት ከፍ ያለ ገንዘብ ከፍለን ነበር፤ ጥራቱ ግን በክፍያው ልክ አይደለም፡፡ ከወረቀቱ አይረቤነትም በላይ ፎቶግራፎቹ በደንብ አይታዩም፡፡ ለኤዲተርም ቢኾን ከፍ ያለ ክፍያ ፈፅሜያለሁ፤ ነገር ግን ቶሎ አላደረሰልኝም፡፡ የኾነው ኾኖ አሁን በጥራት የተዘጋጀው ሁለተኛ እትም በቅርቡ ይወጣል፡፡ በዶክመንት ደረጃም ከመጀመሪያው እትም የተሻለ ነው፡ የመጀመሪያው እትም ላይ አንዳንድ ዶክመንቶች ስሕተት ነበራቸው፡፡ ሁለተኛው ዕትም ላይ እነርሱ ታርመዋል፡፡ ለምሳሌ ገንዘባችን የተወረሰበትን ሂደት በተመለከተ ማስረጃ የሚጠይቁ አካላት አሉ፡፡ አሁን በታተመዉ እትም ላይ ማስረጃዉ ተካቷል። ይህን በተመለከተ በወቅቱ ከዚህ ጋር የተያያዙ ችግሮች ሲገጥሙ ለነገሩ የመንግሥትን ግልጽነትን ለማስየት ለሕዝብ ምክር ቤቱ ይቀርቡና ይወስናል፡፡ ክዚያ ዉጭ መጠየቅ የሚባል ነገር የለም። ማነዉ የንጉሠ ነገሥቱን መንግሥት ዉሳኔ ያዉም የተቃዋሚ ተብዬዉ ቤተሰብ ወይም ወገን መጠየቅ የሚችለዉ፣ የሚሞክረዉ? ያኔ ለተደረገው ነገር ባጀት ስለሚያስፈልግ ለምክር ቤቱ ይቀርብና ይወስናል፡፡ በቀላሉ የተገኘዉ ገንዘብ የጄኔራል ጽጌ ብቻ ነበር። ጠያቂዎቹ ግን እንኳንስ ያን ጊዜ ይቅር እና ከትንሽ ዓመታት በኋላ በደርግ ሥርዓተ መንግሥት ያለቁት እና ንብረታቸዉን የተዘረፉት ሕጉ እና ደንቡ ቢኖር፣ ከነበረም ካለም ቢከበር እና ቢሰራ እንዴት እነኚህ ሁሉ ተጎጂ ቤተሰቦች ንብረት እና ገንዘባቸዉን ጠይቀዉ ማግኘት ተሳናቸዉ? ለጠያቂዎቹ ጥያቄ ነዉ።
ምክር ቤቱ ጉዳዩን አይቶ በፕሬዝዳንቱ በኩል ይነገራል፡፡ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ደጃዝማች አሥራት ካሣ ናቸው፡፡ ቀድሞ እንዳልኩት ይኽንን የሚያሳየዉ ዶክመንት አሁን መጽሐፉ ላይ ተካቷል፡፡ ያኔ በንጉሡ ጊዜ የተወሰነ ነገር ባንክ አካውንት ላይ አይቀመጥም፡፡ ሌላው በመጀመሪያው እትም ላይ እንደ ስሕተት የተወሰደው ደጃዝማች ዘውዴ ገ/ሥላሴ የኢትዮጵያ አምሳባሰደር አልነበሩም የሚል ነው፡፡ ይሄ ፍጹም ስሕተት ነው፡፡ ደጃዝማች ዘውዴ ገ/ሥላሴ አምባሳደር ነበሩ፡፡ ቪዲዮም አለኝ፡፡ እርሳቸው የኢትዮጵያ ፍርድ ሚኒስተር ኾነው ሦስት ዓመት ከሠሩ በኋላ ሥራቸዉን ለቀው ውጪ ሀገር ሄደው ስምንት ዓመት ተምረዉ የዶክትሬት ዲግሪያቸዉን ከተቀበሉ በኋላ በንጉሡ ተጠርተው መጥተው ‹‹የሶማሌ ጉዳይ ስላለ ዩናይትድ ስቴት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ አምባሳደርነት ሄደህ ጉዳዩን ተከታተል›› ተብለው ጫማ ስመዉ መሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡ የዚህ ቪዲዮ አለ፤ እሳቸዉ የተናገሩትን ታሪክ በትክክል ማስቀመጥ ያቃታቸው የታሪክ ተንታኞች ይህን ነገር ማገናዘብ ተስኗቸዋል፡፡ ማንም ተመዝጋቢ የሚጽፈዉ እና የሚያሻለዉ ዊኪፒድያ ገጽ እንደ አመላካች መረጃ ምንጭ መሆን ሲገባዉ እንደ ዋና እና የመጀመሪያ ምንጭ ሰነድ መዉሰድ ግን የዝግጅት ወይም የተጠቃሚዉን ዉስን መረጃ ችሎታ የሚያመላክት ነዉ። ይኽ በቅርቡ በናሁ ቴሌቪዥን “በሃሳበ ንባብ” ያከናውንኩት ቃለ መጠይቅ ዝግጅት ላይ ተከስቷል።
ግዮን፡- መጽሐፉን ያዘጋጁት እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ አስበው ነው ወይስ ለአባትዎ የሕይወት ታሪክ ማስታወሻነት?
አታመንታ፡- መጽሐፉን ያዘጋጀሁት ዋናው ነገር በአባቴ ሕይወት ውስጥ የሀገር ታሪክ ስለተካተተበት ነው፡፡ እኛ ስናድግ ኢትዮጵያ ከቤተሰብም በላይ ናት ተብለን ነው፡፡ ስለዚሀ እኔ ከኢትዮጵያ ውጪ ዘርና ብሔር አላውቅም፣ ቤተሰቤም አያውቅም፡፡ ይህ በመኾኑ መጽሐፉን ያዘጋጀሁት በኢትዮጵያዊነት መንፈስ በመነሳሳት ነው፡፡ ስለዚህ የአባታችንን የሕይወት ታሪክ ማሳወቅ እግረ መንገድ እንጂ ብቸኛዉ ዋናው ጉዳይ አይደለም፡፡ እናም በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የአባታችን የሕይወት ታሪክና የኢትዮጵያ ታሪክ አንድ ላይ የተሸረቡ ናቸው፡፡ አባታችን የመሠረቷቸው ተቋማት ያዘዙባቸው፣ የመሩባቸው እና የመሯቸው ድርጅቶች ዛሬም ያሉና የአባታችንን አሻራ እና እርሾነት መነሻ ያደረጉ ናቸው፡፡ ይህን እኔ ብጽፈውም ባልጽፈውም ተቋማቱ በራሳቸው ይናገራሉ፡፡ በእርግጥ አንዳንድ አባታችን የመሠረቷቸው ተቋማት ላይ ለምሳሌ ‹‹የፖሊስ ኦርኬስትራ ሙዚቃ ክፍልን ያቋቋሙት ረዳት ኮ/ል ረታ ናቸው›› እየተባለ በውሸትና መስራቹን ጄኔራል ጽጌን ከአንባቢ ለማግለል ተጽፏል፡፡ ነገር ግን ይህ የኾነው የአባታችን ታሪክ እንዳይጻፍ ሰለተፈለገና ተሸፍኖ ስለቆየ ነው፡፡ ይህን መግለፅ ደግሞ የግድ ያስፈልጋል፡፡ ገለፃውም ስለአባታችን ማንነት ሳይኾን በዋናነት ስለተቋማቱ አመሠራረት ነው፡፡ በተጨማሪም በሃገራችን አንድ ታሪክ ለመጻፍ በጣም የመረጃ እጥረት አለ። ስለሆነም የታሪክ ዘጋቢ ጽሑፎች ከዋናዉ የታሪክ ባለቤት የቀን ዉሎ እና የሥራ እድገትና ሓላፊነት ዝርዝር ዉጭ የጊዜዉን ሁኔታዎች፣ በጊዜዉ ወይም ከዚያ በፊት የነበሩትን ባለሥልጣናት ሥራ እና ባሕሪ፣ የሀገሪቱን ቦታ እና ደረጃ (ከሌላዉ ሃገሮች) ጋር ሲንጻጸር ወዘተ… በሚገባዉ መልኩ አይካተትም። እኛም የታህሳሱ ንቅናቄዉ ምን መሰረት ይዞ እና ለምን እንደ ተከሰት ለማሳወቅ ብዙ የኋላ መረጃዎችን ለማካተት ሞክረናል። አለበዚያ ከአንድ ቦታ የማይወጣ የአንድ ሰዉ የቀን ተቀን ዉሎ ትረካ ብቻ ይሆናል ብለን በማሰብ ነዉ።
በጥቅሉ እንዲህ ዓይነት የታሪክ መሸፋፈኖችና እመቃዎች አግባብነት የላቸውም፡፡ ለሀገር ጥሩ እና ጠቃሚ ሥራ የሠራ ሰው የግድ እውቅና ሊሰጠው ይገባል፡፡ ለምሳሌ እኔም በሃገራችን ሁልጊዜ ለምን እንዲህ አይሆንም በሚል አንዳንዴ በኢትዮጵያዊ ድክመታችን እቆጫለሁ፡፡ ምክንያቱም የእኔ ቤተሰብ ብቻ ሳይኾን የብዙዎቹ ታሪክ እየተበላሸ በመኾኑ ነው፡፡ ችግሩ ተወራራሽና ቀጣይ ነው፡፡
ግዮን፡- መጸሐፉ የተመረቀው የት ነው? ፕሮግራሙስ ምን ይመስላል?
አታመንታ፡- መጽሐፉ እንዳለቀ መጀመሪያ የተመረቀው አሜሪካን ሀገር ዋሺንግተን ዲ.ሲ ካቶሊክ ዩንቨርሲቲ ውስጥ ነው፡፡ ዝግጅቱ በጣም ጥሩና ልዩ ነበር፣ ብዙዎቹም ወደውት ነበር፡፡ ሁለተኛው ምርቃት ደግሞ አዲስ አበባ ነበር፡፡ የተዘጋጀውም በአርትስ ቲቪ በኩል ነው፡፡ እነርሱም በጣም ልዩ ዝግጅት አድርገው ነበር፡፡ ምርቃቱ የተዘጋጀበት ቦታ አፍሪካ አንድነት ድርጅት ውስጥ ነው፡፡ መጽሐፉን አፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥሪያ ቤት ማስመረቅ ያስፈለገው ቦታው ለእኛ ታሪካዊ በመኾኑ ነው፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የቀድሞው ሕንፃ አባታችን ለአባ ዲና ፖሊስ ኮሌጅ ያሠሩት ሕንፃ ነው፡፡ ስለኾነም ከ62 ዓመት በኋላ ቦታው ላይ የአባታችንን ታሪክ ያነገበ መጽሐፍ ማስመረቅ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ በምርቃቱ ዕለት የነበረው የፕሮግራም ሂደት በጣም ደስ የሚል ነበር፡፡ ብዙ ሰው አባታችን በዚያች አጭር የሕይወት ዘመናቸዉ ያን ያህል ሥራ መሥራታቸዉን ያወቁት ያን እለት ነው፡፡ ብዙ መጻሕፍትም በዕለቱ ተሸጧል፡፡ ትልልቅ እንግዶችም ታድመው ነበር፡፡ ከፖሊስ ኮሚሽን እንግዶች መጥተው ነበር፡፡ የአባታችን ጸሐፊ የነበሩት ኮ/ል መርሻ ወዳጆም ተገኝተዋል፤ ንግግርም አድርገዋል፡፡ ሌሎች ሰዎችም ንግግር አድርገዋል፡፡
ግዮን፡- ኮ/ል መርሻን ከመጀመሪያው በመጽሐፍ ዝግጅት ጊዜ አግኝታችኋቸዋል?
አታመንታ፡- ለማግኘት ሞክረናል፡፡ ወንድሜ አንድ ሁለቴ አግኝቷዋቸዋል፡፡ ነገር ግን በዋናነት እርሳቸው ያሉበትን ቦታ በግልፅ አናውቅም ነበር፡፡ ብዙ ሰዎች ብናገኝም እሳቸው የት እንዳሉ አላውቅም ነበር፡፡ ለምርቃቱ ግን እርሳቸው ተጠርተው መጥተው ጥሩ ንግግር አድርገዋል፡፡ በዚያን ዕለት ኮ/ል መርሻ በንግግራቸው ከመጽሐፍት ምርቃ ፎርማት አንፃር ጥያቄ ሊያስነሳ የሚችል አንድ ንግግር አድርገዋል፡፡ ይኸውም ‹‹እኔ የጀነራል ጽጌ ጸሐፊ በመኾኔ የመፈንቅለ መንግሥቱ ዕለት የተከናወኑ ተግባራትን ስለማውቅ እርሳቸው በዚህ ውስጥ አልተሳተፉም፡፡ ምክንያቱም መፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎቹ መካከል ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ በተጋጋሚ ስልክ እየደወሉ ጀነራል ጽጌን የት እንዳሉ ይጠይቁኝ ነበር›› የሚል ነው፡፡ ነገር ግን መጽሐፉ ላይ እንዳስቀመጥኩት መፈንቅለ መንግሥቱ ከመጀመሩ በፊት ጀነራል ጽጌ ከእሥራኤሉ የጦር አማካሪ ጋር ስብሰባ ላይ ነበሩ፡፡ ይህ ስብሰባ በምሥጢር የሚካሄድ ነበር፡፡ ስለዚህ ኮ/ል መርሻ በሚሉት ሰዓት ጀነራል ጽጌ ስብሰባ ላይ ስለነበሩ እነ ጄኔራል መንግሥቱ አላገኟቸም፡፡ ይኽም ማለት ንቅንቄዉ ከመጅመሩ በፊት እና ከአዉሮፕላን ጣቢያዉ ሽኝቱ መካከል በነበሩት ሁለት ሰዓታት ዉስጥ የተካሄደዉ ለእሳቸዉ ግልጽ አልነበረም። ኮ/ል መርሻ መጽሐፉን በጊዜዉ ጨርሰው አንብበውት ቢኾን ኖሮ መልሱን እዚያው ያገኙት ነበር፡፡ በጥቅሉ ግን በጣም ድንቅ የምስክርነት ንግግር ነበር ያደረጉት፡፡
ግዮን፡- ወደፊት የአባታችሁን ታሪክ ከመጽሐፍ ውጪ በዶክመንተሪ ለመሥራት ያሰባችሁት ነገር አለ? እስካሁን የእርሳቸውን ንግግርስ በድምፅ አግኝታችኋል?
አታመንታ፡- እንኳን የቪዲዮ ምስላቸውን ወይም የድምፅ ንግግራቸውን ልናገኝ ይቅርና፣ ስለእርሳቸው ያለው መረጃ ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል፡፡ እስካሁን ያገኘነው ንግግራቸው በጽሑፍ እንጂ በድምፅ ወይም ከትንሽ ተንቀሳቃሽ ፊልም በላይ አይደለም፡፡ መጀመሪያ ፎቶግራፍ እንኳን በጣም ጥቂት ነበር ያገኘነው፡፡ እኛ ይሄን አሁን ያከማቸናቸዉ መረጃዎች ለማግኘት ብዙ ደክመናል፡፡ የድምጽ እና ተንቃሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት ግን ምንም አልተሳካልንም፤ ወደ ዋናው ጥያቄ ስመጣ ስለአባታችን በቪዲዮ የተቀናበረ ዶክመንት በቅርቡ ይለቀቃል፡፡ አሁንም የዐሥር ሰዓት ቪዲዮ ተሰርቶ የተቀመጠ ዶኩመንታሪ ፊልም አለ። በቅርቡ የሚወጣ የ3 ሰዓት ርዝመት ሶስት ክፍል ያለው ከትውልድ እስከ መፈንቅለ መንግሥቱ መጨረሻ ድረስ የሚያትቱ ቪዲዮ ቅንብሮች ናቸው፡፡ የሚወጣው በዩቲዩብና በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ነው፡፡ ይህ የሚደረግበት ምክንያት ደግሞ ተደራሽነቱን ለማስፋት ሲባል ነው፡፡ ሁሉም ለምርምር ተቋማት ይሰጣሉ።
ግዮን፡- ጀነራል ጽጌ ከሠሯቸው በርካታ ሥራዎች መካከል አንዱ የነገሌ ከተማን መቆርቆራቸው ነው፡፡ ከሕልፈታቸው በኋላ ግን ከከተማዋ ጋር ያላቸው አሻራ ሲጠቀስ አይሰማም፡፡ ይህ ለምን ኾነ?
አታመንታ፡- አባታችን ወደዚያ የሄዱት ጣሊያን ከተባረረ በኋላ አካባቢውን ለማረጋጋት ነው፡፡ ወደ ነገሌ ሲሄዱ በእንግሊዞች የሚመራ ትንሽ ጦር ነበር፡፡ እርሳቸው ከጅማ ሠራዊታቸውን ይዘው በእግር ነገሌ ገቡ፡፡ ሀገሩ በርሃ ነው፡፡ ስለዚህ ሀገሩን ሸንሽው በመከፋፈል የውሃ ጉድጓድ አስቆፍረው የኩሬ ውሃ አጠራቅመው፣ ለመጠጥ እና ለርሻ አብቅተዋል። መጀመሪያ ሦስት ጉድጓዶች ቆፈሩ፡፡ የጉድጓዶቹ ስም አንዱ መስታወት፣ ሌላው መስከረም ይባሉ ነበር ቀሪውን ደግሞ ስሙን ዘነጋሁት፡፡ የጉድጓድ ውሃው መጠጥን ጨምሮ ለተለያዩ ግልጋሎቶች ይውል ነበር፡፡ ሠራዊቱ የመስኖ ሥራ ያከናውን ነበር፡፡፡ በዚህም ሠራዊቱ ከፊል በላይ ቀልቡን ማግኘት ቻለ፡፡ አርብቶ አደሩም ቋሚ ነዋሪ ሆነ። ጦሩም በደንብ በማጠናከር ከሻለቃነት ወደ ብርጌድነት አጠናከሩ፡፡ በመቀጠል ወደ ሐረር ሄደው ተልዕኳቸውን በመወጣት መዳረሻቸው አዲስ አበባ ኾነ፡፡ በቦረናም፣ በሐረርም፣ በአዲስ አበባም ተመሳሳይ ሥራዎችን አከናውነዋል፡፡ እርሳቸው ካለፉ 13 ዓመታት በኋላ የቦረና ውሃ መበላሸት ይጀምራል፡፡ ይህን ችግር የተለያዩ ከፍተኛ መኮንኖች በተደጋጋሚ በቦታዉ ሄደዉ አይተዋል፡፡ ነገር ግን ለወታደሩ መፍትሔ ሊሰጡት አልቻሉም፡፡ ሠራዊቱም መጨረሻ ላይ አመፀ፡፡ መፍትሔ እንዲሰጡት የተካሉትን መኮንንም አሠረ፡፡ በኋላ እነ ጄኔራል አበራ ወልደ ማርያም ተልከው አስፈቷቸው፡፡ ጉዳዩም ንጉሡ ዘንድ መፍትሔ ሳይሰጠው ሌላ አመጽ ተነስቶ የስድሳ ስድስቱን አብዮት አመጣ፡፡ እዚህ ላይ ታሪክን በትኩረት ካስተዋልን ጄኔራል ጽጌ ያስቆፈሯቸዉ ኩሬዎች እንክባክቤ በማጣታቸዉ የነገሌው ጦር በዚያ በረሃ ዉስጥ የነበረበትን ችግር በተዳጋጋሚ ለመንግሥት አመልክቶ መልስ ባለማግኘቱ ሠራዊቱ ማመጹ የ66ቱ አብዮት ዋነኛ መነሾዉ ኾኖ እናገኘዋለን፡፡
ግዮን፡- ጀነራል ጽጌ ከገነቡት ጦር አንዱ የሐረሩ 3ኛ ክፍለ ጦር በቅፅል ስሙ ‹‹አንበሳው ከፍለ ጦር›› ነው፡፡ ይህ ጦር የኮ/ል መንግሥቱ ኃ/ማርያም መገኛ ነውና ኮ/ሉ ስለአባታችሁ የሰጧችሁ አንዳችም መረጃ የለም?
አታመንታ፡- ጄኔራል ጽጌ በኮሎኔል ደረጃ እያሉ ነበር ጦሩ በሚገባ አደራጅተዉ ብቁ በማድረጋቸዉ ከ3ኛ ብርጌድ ወደ 3ኛ ክፍለ ጦር ደረጃ አድርሰዉት ነዉ ስያሜዉን ያገኘዉ። እሳቸዉ ናቸዉ ያንበሳዉ ጦር ብለዉ የሰየሙት። የጦር ሠራዊቱን ሆስፒታል ወታደሩን ከግዳጅ በኋላ እርሻ እንዲያርስ አድርገዉ ምርቱን በመሸጥ ነበር የሰሩለት። እቃዉን ሁሉ ከአሜሪካን ሃገር ነበር ያስመጡት እንዲሁም ሃኪምም ጭምር። አንድ ወቅት ከፍተኛ ሥልጣን ላይ የነበረ ግለሰብ እንደነገረን ኮ/ል መንግሥቱ ስለቤተሰባችን መኖር ሲሰሙ እጅግ በጣም ተገርመዋል፡፡ ከዚያ ውጪ ምንም መረጃ አላገኘንም፡፡ የሚታወቀው ጀነራል ጽጌ ዲቡ ከነቤተሰባቸው እና ታሪካቸው ከማኅደረ ኢትዮጵያ እንደጠፉ ነው፡፡ እንደሌለን፣ እንዳልኖረን ተደርጎ ነው ሲነገር የነበረው፡፡ እንደ እውነታው ግን 3ኛውን ክፍለ ጦር ያሳደጉት በጀቱን ያስመደቡት ሁሉን ነገር ያደራጁት ጀነራል ጽጌ ዲቡ ናቸው፡፡ ሌላዉ በሞቀ ቤት ነበር የገባዉ።
ግን፡- የጀነራል ጽጌ ሕልፈትን በተመለከተ የሚነገሩትና የተፃፉት መረጃዎች እናንተ ከምትገልጹት አንፃር የተለዩ ናቸው፡፡ ይህ ለምን ኾነ?
አታመንታ፡- ይህ የኾነው የመጀመሪያው እቅድ ተከታይ በመኾኑ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ታሪካቸውም ኾነ ማንነታቸው እንዳይታወቅ ከታሪክ መዝገብ ላይ ተፍቋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በቦታው ላይ የሌሉና ለጉዳዩ ሩቅ የኾኑ ሰዎች ስለጀነራል ጽጌ የተሳሳቱ መረጃዎችን ጽፈዋል፣ አቅርበዋል፡፡ አሁንም አንዳንድ ተነካሁ ባዮችም አካባቢ የሚነገረዉን አልባሌ እንሰማዋለን፣ ስለዚህ በጥያቄው ላይ የቀረበው የአባታችን ታሪክ እና አሟሟት መረጃዎች በእነዚህ ግለሰቦች የቀረቡ እና የሚተረኩ ናቸው፡፡ እኛ ያቀረብነውን የጀነራሉን አሟሟት እውነታ በተመለከተ ግን በወቅቱ የነበሩ የቅርብ ሰዎች የቪዲዮ መረጃዎች አሉን፡፡ ከዚህ አንፃር የእነ ጀነራል ወልደሥላሴ በረካ፣ የእነ አቶ አምዴ ወንድአፍራሽ፣ የእነ ሻምበል ገድሉ ኃይሉ፣ የእነ ሻለቃ ያሬድ ቢተው የእነጄኔራል ጃጋማ ኬሎ፣ የእነ ሻለቃ ያሬድ ቢተዉ የእነ ሻለቃ አስራት ቦጋለ እና የጋዜጠኛ ደራሲ አቶ ማሞ ዉድነህ ወዘተ.. ከ60 እና 70 ሰዓታት በላይ የሚሆኑ ቪዲዮ ቅጂ በእጃችን ላይ አለ፡፡ እነዚህ የጠቀስኳቸው ሰዎች መፈንቅለ መንግሥቱ ሲከናወን ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ በተለያየ ተባባሪ/ተጻራሪ ወገን እና በጉዳዩ ተካፋይ በመሆን በቅርበት የተከታተሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ አቶ አምዴ ወንድአፍራሽ የነገርማሜ ነዋይ የቅርብ ጓደኛ ዘመድም ነበሩ፡፡ እነሻለቃ ያሬድ ቢተው መጀመሪያ በእቴጌ ቪላ ቀጥለዉም በገነት ልዑል ቤተመንግሥት ጥበቃ የነበሩና ጉዳዩን በቅርብ ያዩ ናቸው፡፡ ንቅናቄዉም ከተፈጸመ በኋላ እስከ እሁድ አጥቢያ ድረስ ከእነ ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ እና ወንድማቸዉ አቶ ገርማሜ ነዋይ ጋር አብረዉ የቆዩ ናቸዉ። ስለዚህ ከእነዚህ ዋና እማኞች ዉጭ ታሪክ አዛብተው የፃፉት ሰዎች በቦታው ያልነበሩና ለአባታችንም ሆነ ለጉዳዩም የሩቅ ሰዎች ናቸው፡፡ ሌላዉ እንዲህ ዐይነት ክስተት በመንግሥትም ሆነ በባለሥልጣናቱ ላይ ከፍተኛ ጥያቄ ማስነሳቱ እንደማይቀር ግልጽ በመሆኑ በተቻለ መጠን ጉዳዩን ማንቋሰስ እና ማሳነስ ከሚመለከተዉ ስርዓት የሚጠበቅ ነበር።
ግዮን፡- ለአባታችሁ መታሰቢያ የሚኾን ሕንፃ አዲስ አበባ ላይ ሠርታችኋል፡፡ ሥሙም ‹‹ጽጌ ዲቡ መታሰቢያ›› ይሰኛል፡፡ ለምንድነው ማዕረጋቸውን የተዋችሁት?
አታመንታ፡- ይህ የኾነው በሁለት ምክንያት ነው፡፡ የመጀመሪያው እርሳቸው ከሞቱ በኋላ ሹመታቸው የተገፈፈ በመኾኑ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ቀደም ሲል በነበሩት መንግሥታት እንዲህ ዓይነት የማዕረግ ስሞች አላስፈላጊ ገጽታን ያላብሳሉ በሚል ነው፡፡ ነገር ግን አስፈላጊ ከኾነ የስም ጉዳይ በመኾኑ አሁንም ማድረግ እንችላለን፡፡
ግዮን፡- የአባታችሁ ሕልም ምን ነበር? ሕልማቸውን ለማሳካት ምን ያህል ተጉዛችኋል?
አታመንታ፡- የጀነራል ጽጌ ዲቡ ሕልም መጽሐፉ ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ እኛ ኢትዮጲያውያን ማንንም ሳንለምን እና ሳንለማመጥ እራሳችንን፣ ሃገራችንን እና ወገናችንን በእራሳችን ሥራ እና ጥረት ራሳችንን እንድንችል እና ከሌላዉ ካደጉት ሃገራት እኩል ወይም በላይ እንድንሆን ለማድረግ ነበር። ድካማቸዉ እና ጥረታቸዉ ይኽዉ ነበር። በአብዛኛው በጊዜው የነበረው ሥርዓት በቂ የተማረ ኃይል ስለሌለው እሱን በታትኖ አዲስ መንግሥት ከማቆም ይልቅ ጥገናዊ ለውጥ አድርጎ ሀገርን በተሻለ መልኩ እናስቀጥል የሚል ነበር፡፡ በወቅቱ መፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎቹም ቢኾኑ የፈለጉት ከንጉሡም ጋር ንግግር አላቸው ብለን የምናስበው (ብዙ ያላወጣናቸው ዶክመንቶች አሉ) በሕግ የተወሰነ የዘውድ መንግሥታዊ ሥርዓት መሥርተዉ እሳቸዉም አልጋወራሹ አንድ ቦታ ተቀምጠው በፓርላሜንት ሥርዓት ሀገራችን እንድትመራ ነበር፡፡ ሕልሙ እውን ሳይኾን ቀረ፡፡ ያንን ሕልማቸውን እኛ መናገር የቻልነው በብዙ አቅጣጫዎች የውስጥ ሰዎችንም ስለምናውቅ ነው፡፡ በቀጨኔ፣ በኮተቤ ክበቦች እና የተለያዩ ቦታዎች ላይ አባታችን ያደረጓቸው ጉብኝቶች በፍሬ ከናፈር ላይ የተመዘገቡት ንግግሮች የሚያመላክቱትም ይኸንን ነው፡፡ ለምሳሌ ከታኅሣሱ ግርግር አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ ንጉሠ ነገሥቱ ሥልጣናቸዉን እንዲያስረክቡ ወጥረው ይዘዋቸው ነበር፡፡ ከወራቶች በፊት ያልታያቸዉ አሁን ደግሞ ባጭር ጊዜ የተገለጸላቸዉ ምንድን ነዉ ብሎ መጠየቅ በጣም አግባቢነት ያለዉ ጥያቄ ነዉ። ብዙዉ ዝርዝር መጽሐፉ ዉስጥ ይገኛል። ሌላው እኛ የጄኔራል ጽጌ ቤተሰቦች በቤተሰብ ደረጃ መጽሐፍ ጽፈን በስማቸው የሚደረገውን አድርገናል፡፡ ሀገራችንን እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንወዳለን፡፡ በእጃችን ያሉ ማንኛውም ዶክመንቶችንም ለወመዘክርና መሰል ቤተመጻሕፍቶች ይሰጣሉ፡፡ እነዚህ ዶሴዎች እና መረጃዎች ቀጣዩ ትውልድ የጄኔራል ጽጌ ዲቡን ሕልም እና ራዕይ እንዲያዉቅና በተግባር እዉን እንዲያደርግ መነሻ ይሆናል ብለን እናምናለን። ሕልማቸዉን በእሳቸዉ ደረጃ ለመቀጠል በገደብ የኖርን ስለነበርን ባይሳካልንም ባለን አቅም ግን የሚቻለንን አድርገናል እያደረንም ነዉ እላለሁ። ይኽንን በተመለከተ ማድረግ የምንችለዉ ይኽንን ነው።
ግዮን፡- ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከአባታችሁ ሕልፈት በኋላ ያላቸው ስሜት ምን ነበር?
አታመንታ፡- ጀነራል ወልደሥላሴ ለእኛ ቅርብ ሰው ነበሩ፡፡ ከእኛ ቤተሰብ ያልተለዩና ወንድሜንም ያተረፉት እሳቸው ናቸው፡፡ እሳቸው በእኛ ምክንያት የጄኔራል ጽጌ ዲቡን ቤተሰቦች ይረዳል ተብለዉ በጊዜዉ ባለሥልጣናት ተከሰዉ ጃንሆይ ፊት ሦስት አራቴ ያህል ቀርበው ነበር፡፡ በዚህ ሰዓት እርሳቸው “ጀነራል ጽጌ ጓደኛዬ ነበር፤ ልጆቹ ልጆቼ ናቸው፤ ለዚህ ወቅት ብዬ አልተዋቸውም” ሲሉ ንጉሡ ነገሥቱም “የእግዜር ሥራ ነው የምትሰራዉ፤ ጽጌ እኮ ለእኛም ታማኛችን ነበር፤ ልጆቹንስ ብናሳድግለት፤” ሲሉ መለሱላቸው፡፡ በተጨማሪም ይህን ሲናገሩ ንጉሡ የሚያስቡትን መፈጸም ያልቻሉት ‹‹ለሞተዉ ጽጌ ሌሎቹን ላለማስቀየም›› ሲሉ እንደኾነ ጀነራል ወልደሥላሴ ነግረዉናል፡፡ ስለዚህ ያለ ንጉሡ ፈቃድ አንዲትም ሳንቲም አናገኝም ነበር፡፡ ጀነራል ወልደሥላሴ በተቀረጸዉ ቪዲዮ ላይም ንጉሡ እኛ የረዱን ለእኛ ቤተሰብ ጥሩ አመለካከት ያላቸው በመኾኑ እና እንደኾነም ተናግረዋል፡፡ ስለዚህ በአባታችን ሕልፈት በጣም ያዝኑ ነበር፡፡ ሁልጊዜ አንድ ነገር ሲበላሽ “ያ ጽጌ ቢኖር ኖሮ ይኽ አይደረግም ነበር” እያሉ በቁጭት ጭምር እንደሚያዝኑም ሰምተናል፡፡ ስለዚህ ንጉሡ የነበራቸው ስሜት በዚህ መልኩ የሚቃኝ ነበር፡፡
ግዮን፡- ጀነራል ጽጌ ለሀገር ካበረከቱት አስተዋፅኦ አንፃር ንጉሠ ነገሥቱ ቢያንስ የጀነራሉን የቀብር ቦታ እውቅና ያለው እንዲኾን ያላደረጉት ለምንድን ነው?
አታመንታ፡- ጀነራል ጥላሁን ቢሻኔ የ4ተኛ ክፍለ ጦር የሕክምና ዶ/ር ነበሩ፡፡ በቅርቡ ነው ያረፉት፡፡ እርሳቸውን ስጠይቃቸው በወቅቱ የአባታችን አስክሬን አራተኛ ክፍለ ጦር ፊት ለፊት ሀዲዱ ላይ ከቆየ በኋላ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን ወስደው መቀበራቸውን እንደሚያውቁ ነግረውኛል፡፡ በኋላ ላይ ግን አውጥተው “ደብረ ሊባኖስ ቀበሯቸው” የሚባል ነገር እንዳለም መስማታቸውን ገልጸውልኛል፡፡ በአጠቃላይ ግን እንደአባታችን ዓይነት በተቃውሞ የተገደሉ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት ቀብራቸው እንዲታወቅ አይፈለግም፡፡ ይኼ ታሪካችን እና ባሕላችን ነው፡፡ እኛ መጨረሻውን ለማወቅ ብዙ ሞክረን ነበር፡፡ ካርታ አዘጋጅተን የተቀበሩበትን ቦታ ለማወቅ ጥረን ነበር፡፡ ነገር ግን ፍንጭ በማጣታችን አሁን ላይ ተስፋ ቆርጠናል፡፡ ኾኖም መጽሐፉ ለሕትመት ለአሳታሚዎች ሊላክ ጥቂት ቀናት ሲቀረዉ አባታችንን ከወድቁበት አንስተዉ ቅዱስ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን እንደ ቀበሯቸው የቁርጥ ቀን ወዳጃቸዉ ነገሩን። የነበረዉንም እማኝነቸው በቪዲዮ ተቀርጿል።
ግዮን፡- መጽሐፉ በርካታ ገጽ ያለው ከመኾኑ አንፃር ይህን መጽሐፍ ለማዘጋጀት ሲነሱ የሥነ ጽሑፍ ልምድ ነበረዎት?
አታመንታ፡- ምንም ዓይነት የሥነ ጽሑፍ ልምድ አልነበረኝም፡፡ ስጀምረው የተለያዩ ሰዎችንና ጸሐፊዎችን አነጋግሬ ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሉም ነገር ተስፋ አስቆራጭ ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ ግን እጄ ላይ ያሉትን ከ27 ዓመታት በላይ የሰበናቸዉን ዶክመንቶች በማየት ድንገት አንድ ነገር እንኳን ብሆን የትም ተበትኖ እንዳይቀር ብዬ ለመጻፍ ተነሣሁ፡፡ በመጨረሻዉ ሰዓት በፍጥነት እንድ ጀምር ግፊት ያደረገችብኝ ታናሽ እህታችን ሶፊያ ጽጌ ነች፡፡ የጽሑፍ ሥራውን ከጀመርኩ በኋላ ምንም እረፍት አልነበረኝም፡፡ መጀመሪያ ላይ በኮምፒውተር አማርኛ መጻፍም ያስቸግረኝ ነበር፡፡ ኾኖም ግን በከፍተኛ ትግል ይህን መጽሐፍ አዘጋጅቼ ለመጨረስ በቃሁ፡፡ ለሁለት ዓመታት ጽሑፉን ሳዘጋጅ ቆይቻለሁ፡፡ ብዙ ሰዎችም ረድተውኛል፡፡ በሐሳብ የቤተሰቡን ታሪክ እህቶቼ እቴነሽ ጽጌ፣ ራሄል ጽጌ፣ ሶፊያ ጽጌ፣ የወንድማችን ባለቤት ወ/ሮ አልማዝ አያሌዉ ደግሞ በእርማት በጣም ረድተዉኛል። ባለቤቴም ወ/ሮ ቅድስት ሱራፌልም ሁኔታዎችን በማስተካከል በጣም ረድታኛለች። እኔ ግን ስለጽሑፍ ምንም ዓይነት ቅድመ ዝግጅት አልነበረኝም፡፡ የተሰማኝን የሚሰማኝን እንዳለ ነዉ ያስቀመጥኩት። የጽሑፉን እርማት በተመለከተ ግን መላው ቤተሰባችን አስተያየት ሰጥቶበታል፡፡ ይህ በመኾኑም ከሺህ በላይ ገፆች ሊኖሩት የሚችለው መጽሐፍ በስድስት መቶ ስልሳ ሰባት ገጾች ገደማ እንዲጠናቀቅ አድርጎታል፡፡ መጽሐፉ አሁን ያለውን ይዘት ይዞ የወጣዉ በጣም ተጨምቆ እና እጅግ አጥሮ ነው፡፡ በመጽሐፉ አስፈላጊ የኾኑ ማጣቀሻዎች ተካተው ቀሪው ደግሞ ለሚመለከተው አካል ስለሚሰጥ ትውልዱ በራሱ መንገድ እየተጠቀመበት ይሄዳል በሚል ነው መጽሐፉ በዚህ መንገድ የቀረበው፡፡
ግዮን፡- ለመጽሐፎ ‹‹የጠዋት ጤዛ›› የሚል ንዑስ ርዕስ ሰጥተውታልና ምን ለማለት ነው?
አታመንታ፡- ‹‹የጠዋት ጤዛ›› ማለት ጠዋት ላይ ጎህ ሲቀድ በእጽዋትና በአትክልት ላይ እንደ እንጥፍጣፊ ውሃ ተንጠልጥሎ የሚታይና ሰዓቱ እየረፈደ ሲሔድ የሚጠፋ ዉሃ ነው፡፡ ያ ጠብታ “የጠዋት ጤዛ” ውሃ አትክልቱን መሬቱን አርሶ እና አለስልሶ ተክሉን እንደሚያለመልመው ሁሉ ከብዙዎች አንዱ ጄነራል ጽጌም ለኢትዮጵያ እንዲሁ ነበሩ ለማለት ነው፡፡
ግዮን፡- በመጨረሻ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ?
አታመንታ፡- አብዛኛው ችግራችን ላጠፋነው ጥፋትም ኃላፊነት መውሰድ አለመቻል ነው፡፡ ለጥሩ ነገር እውቅና መስጠትም ደግሞ የተለመደ ባሕላችን አይደለም፡፡ እነዚህን ሁለት ነገሮችን መተግበር ይኖርብናል፡፡ ብዙ ሰዎች ከፍተኛ ዋጋ ከፍለው ነው እዚህ የደረስነው፡፡ ያለፉትን ሰዎች ታሪክ መዘርዘር ይኖርብናል፡፡ እጃችን ላይ ያለውን ለሀገር ብለን ማስጠበቅ ይኖርብናል፡፡ ከትንሽ የፖለቲካ እሳቤ ወጥተን ትልቁን ነገር ማሰብ አለብን፡፡ በጎጥና በጎራ ተቧድነን ሀገር ማልማት አንችልም፡፡ ስለዚህ ይህን እሳቤ አሁኑኑ ማስወገድ ይኖርብናል፡፡ በዚሁ እኩል የፖለቲካ ስለባ የሚሆኑት ቤተሰቦች ባለቤቶች እና ልጆች በታሪካችን በተደጋጋሚ እንደታየዉ ቀን ሲጎድል ይገደላሉ፣ ይጋዛሉ፣ ይወገዛሉ ይዘረፋሉ። እነሱን መሆን ያሳዝናል፣ እኛ እነ እርሱ ነበርንና። እኛንም ከዚያ ሁሉ መከራ አዉጥታ ለዚህ ያበቃችን፣ ከአባታችን ጋር በረሃ ለበረሃ ስትንከራተት ኖራ ድጋሚ እኛን ከእርግጠኛ ሞት አፋፍ አዉጥታ ቀጣይ ሕይወት የሰጠችን እናታችንን የወ/ሮ ከበቡሽ ተስፋዬን ቆራጥነትን ማስታወሱ ለእኛ ቤተሰቡ መሠረታዊ ነዉ።
በመጨረሻም ትውልድ ለወገን እንዳይቆም “ይህንን ያየ ነግ በእኔ” በማለት ዝምተኛ ካልሆነም ወደ ሞቀበት ማዘንበል፣ ከዚያም ካለፈ ወኔ ቢስነት፣ አልማጭነት እና ፌዘኛነት እንዲሰፍን አድርጓል ብዬ አምናለሁ። ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ ሀገራችን በጥቂት ቆራጥ ልጆቿ ጥረትና መሥዋዕትነት እስከ አሁን በነጻነት ታፍራ ቆማለች።
ግዮን፡- ስለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ሥም ከልብ እናመሠግናለን፡፡