የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተሻለ የትምህርት ተቋም ለመሆን በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ 59 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልገው የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝደንት ሳሙኤል ክፍሌ አስታወቁ።
ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት በዓመት ከአራት ቢሊየን ብር የመንግስት በጀት እንዲሁም ከአንድ ቢሊየን ብር የራሱ ገቢ ያገኛል።
ሆኖም ፕሬዝደንቱ ይህ በቂ እንዳልሆነና ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራቱን ለማሻሻል፣ ምርምሮችን ለማስፋፋትና ለተማሪዎች ምቹ የሆነ የትምህርት ከባቢ ለመፍጠር በዓመት ከ11 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።
የገንዘብ እጥረት ዩኒቨርሲቲው እነዚህን ግቦች ለማሳካት በሚያደርገው ጥረት ላይ እንቅፋት እየሆነ መሆኑንም ፕሬዝደንት ሳሙኤል ክፍሌ ገልጸዋል።