የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር 23ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የመክፈቻው ሥነ_ሥርዓት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአድዋ መታሰቢያ ሙዚያም ተካሂዷል፡፡ በዚህ ዕለት የተለያዩ እህት ማህበራት ተገኝተው የአጋርነት መልዕከት ያስተላለፉ ሲሆን ዶ/ር ዴኒስ ሲኞሎ የትምህርት ዓለም አቀፍ አፍሪካ አህጉር ዳይሬክተር ተገኝተው መልዕክት ከማስተላለፋቸውም በላይ ከጉባኤ አባላት ጋር በመሆን “Go public Fund Education” ዘመቻን መርተዋል፡፡
ጉባኤውን የትምህር ሚንስትር ተወካይ ዶ/ር ሰለሞን አብርሃም በንግግር ከፍተውታል፡፡እውቅናዎችም ለማህበሩና ለመምህራን የጎላ ድጋፍና አስተዋጽኦ ላደረጉ ድርጅቶችና ግለሰቦች ተሰጥቷል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት፣ ፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን፣ ኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ፣ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ፣ አሀዱ ሬድዮ ፣ ቬሎሲቲ ትራንስፖርት(ፕ.አል.ሲ)፣ ፐብሊክ ትራንስፖርት እንዲሁም በአፈጻጸማቸው የኦሮሚያ ክልል መምህራን ማህበር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መምህራን ማህበር እና የማዕከላዊ ኢት/ክልል መምህራን ማህበር ዕውቅና ያገኙ ሲሆን በችግር ወቅት አባሎቻቸውን ላገለገሉ ለአማራ፣ ለትግራይና ለቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልሎች እውቅና ተሰጥቷል፡፡
በግለሰብ ደረጃ አምባሳደር ዶ/ር ገነት ዘውዴ፣ አምባሳደር ዶ/ር ሽፈራው ሽጉጤ ፣ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ማህበሩን ሲያገለግሉ ቆይተው በሌላ ለተተኩ የቀድሞ ክልል ማህበራት ፕሬዝደንቶች እንዲሁም ማህበሩን ለረጅም ዓመታት በትጋት ሲያገለግሉ ለነበሩት መ/ርት ደስታዬ ታደሰ የእውቅናው አካል ነበሩ፡፡ ከመክፈቻ ሥነስርዓት በኋላ የአፊሪካ ኮንቬንሽን ሴንተርን ጨምሮ በአዲስ አበባ በአራዳ፣ ለሚ ኩራና አቃቂ ቃልቲ ክፍለ ከተሞች የተለያዩ የልማት ሥራዎች ጉብኝት ተደርጓል፡፡
ጉባኤው ከጥቅምት 5-6/2018 ዓ/ም በአዳማ ከተማ በአባ ገዳ እኮኖሚ ዞን በሚገኘው የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ አዳራሽ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ የመከረ ሲሆን በተለይ በትምህርት ጥራት ፣ መብትና ጥቅም፣ የመምህርነት ሙያ ተመራጭ አለመሆን ፣ ሰላም እና ሀገራዊ ጉዳዮች ፧ የተማሪዎች ወደ ት/ቤት መምጣት አለመቻል በተለይ በአማራ ክልል ያለው ሁኔታ ላይ ሲመክር ቆይቶ በሀገር ደረጃ ለቀጣይ ዓመታት ማህበሩን የሚመሩ ሥራ አስፈጻሚ እና የኦዲት ኮሚቴ አባላትን መርጧል፡፡
ተመራጮቹም
ዶ/ር ዮሐንስ በንቲ ፕሬዚዳንት ከኦሮሚያ፤
አቶ ሽመልስ አበበ ም/ፕሬዚዳንት ከአማራ፤
አቶ ጥላሁን ታረቀኝ ዋና ፀሐፊ ከትግራይ፤
ወ/ሮ መስታወት በላቸው ም/ዋና ፀሐፊና ስርዓተ ፆታ ኃላፊ ከኦሮሚያ ፤ እንስፔክተር ታረቀኝ ኃይሌ ትምህርት ስልጠናና ምርምር ኃላፊ ከደቡብ ኢትዮጵያ፤ ዶ/ር በፈቃዱ ዘለቀ የከፍተኛ ትምህርት ተወካይ ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች (አዲስ አበባ ዩኒ.) ፤ ወ/ሮ ደብሪቱ ጌታቸው የኦዲት ኮሚቴ ሰብሳቢ ከድሬዳዋ፤ ወ/ሮ ገነት ከበደ የኦዲት ኮሚቴ አባል ከደቡብ ምዕ/ኢትዮጵያ፤ አቶ ታከለ ታደሰ ከሲዳማ ክልል የኦዲት ኮሚቴ አባል ሆነው ከተመረጡ በኋላ ባለ 12 ነጥብ የአቋም መግለጫ ወጥቶ ጉባኤው በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል፡፡