የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገር ውስጥ በረራን ለማሳደግ እና በአገልግሎት የቆዩ አውሮፕላኖችን ለመተካት ሲል አውሮፕላኖቹን ለመግዛት ማሰቡን የአየር መንገዱ ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ገልፀዋል።
ስራ አስፈፃሚው ለግዢ 3 ሞዴሎች መታሰባቸውን ሲገልፁ የኢምብራኤሩ E-2፣ የኤይርባሱ A220 እና የቦይንጉ 737 ማክስ 7 አውሮፕላኖች መሆናቸውን አንስተዋል።
ከእነዚህ ሞዴሎች ውስጥ የቦይንጉ 737 ማክስ 7 አውሮፕላን እውቅና ያልተሰጠው ሲሆን ድርጅቱ ቦይንግ ለአውሮፕላኑ በዚህ አመት መጨረሻ ዕውቅና ለማግኘት እየሰራ መሆኑን ከቀናት በፊት መግለፁ ይታወቃል።
አየር መንገዱ በርካታ የበረራ ፍላጎቶች ቢኖሩትም ከኤይርባስ እና ቦይንግ በሚታዘዙ አውሮፕላኖች ላይ ከ3 ወር በላይ ለሚሆን ጊዜ የትዕዛዝ መዘግየት እያጋጠመው ስለመሆኑ ተገልጿል።
አየር መንገዱ እያጋጠመው ካለው የሞተር እጥረት የተነሳ ችግር እየገጠመው መሆኑ ሲገለፅ በሮልስ ሮይስ ሞተር እጥረት 3 ግዙፍ ቦይንግ 787 አውሮፕላኖችን ጨምሮ ሌሎችም ከስራ ውጪ መቀመጣቸው ተመላክቷል።
በተለምዶ ሞተሮችን ለመጠገን 3 ወራትን ይፈጅ ነበር ሲባል አሁን ግን ከዚያ በላይ እየቆየ እንደሆነም ተነግሯል።
አየር መንገዱ አሁን ሊገዛ ያሰባቸው አውሮፕላኖች በተለምዶ ከ30-130 ሰዎችኖ መያዝ የሚችሉ ሲሆን ለአጭር እና መካከለኛ ርቀት በብዛት የሚውሉ ናቸው።
Source: Reuters