ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ለመጠናቀቅ ሁለት ወራት ብቻ በቀሩት የዘንድሮው የፈረንጆቹ ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ7.2 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነበየ። ድርጅቱ ሀገሪቱ በቀጣዩ የፈረንጆቹ 2026 ዓመት ይኖራታል በሚል ያስቀመጠው እድገት፤ ለዚህ ዓመት ከተነበየው በ0.1 በመቶ ያነሰ ነው።
መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው አይ ኤም ኤፍ ይህን ያስታወቀው፤ ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 6፤ 2018 ይፋ ባደረገው ዓመታዊ ሪፖርቱ ነው። ሪፖርቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች የሚገኙ 45 ሀገራትን የኢኮኖሚ ሁኔታ የዳሰሰ ነው።
ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት በውጫዊ ሁኔታ፣ ባልተረጋጋ የሸቀጦች ዋጋ፣ መፈናፈኛ በሚያሳጡ የብድር ሁኔታዎች እንዲሁም ባሽቆለቆለው ዓለም አቀፍ የንግድ እና እርዳታ አካሄድ ቢፈተኑም፤ ኢኮኖሚያቸው ይህንን የመቋቋም ችሎታ ማሳየቱን አይ ኤም ኤፍ አትቷል። በዚሁ ቀጠና ያለው የኢኮኖሚ እድገት፤ በፈረንጆቹ 2025 ዓመት 4.1 በመቶ በሆነ የተረጋጋ ሁኔታ እንደሚቀጥል አመልክቷል።
ይህ የኢኮኖሚ ትንበያ በመጪው የፈረንጆቹ ዓመት “በትንሹ ከፍ” እንደሚል የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ለዚህም እንደ ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ ባሉ ሀገራት እየተተገበሩ ያሉ “የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጥረቶች” አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው አመልክቷል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በቀጠናው ያሉ እንደ ቤኒን፣ ኮትዲቯር፣ ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ ያሉ ሀገራት በዓለም አቀፍ ደረጃ “ፈጣን እድገት የተመዘገበባቸው” መሆኑንም ሪፖርቱ በበጎ ጎኑ ጠቅሷል።
በዘንድሮው እና በመጪው የፈረንጆች ዓመት የሚኖረው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ እድገት አምና ከነበረው በ0.2 በመቶ እንደሚያንስ ቢጠበቅም፤ ከሰሃራ በታች ያለው የኢኮኖሚ ሁኔታ ግን ከሚያዝያ ወዲህ “መጠነኛ መሻሻል” ማሳየቱን አይ ኤም ኤፍ ገልጿል። በመጪዎቹ ጊዜያት የነዳጅ ዋጋ ይበልጥ ይቀንሳል ተብሎ ቢጠበቅም፤ ቡና እና ወርቅን የመሳሰሉ ዋነኛ ሸቀጦች ዋጋ ግን ከኮቪድ ወረርሽኝ በፊት ከነበረውም ጊዜ በላይ እንደሚሆን ሪፖርቱ አትቷል።
ይህ ሁኔታ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በተፈጥሮ ሀብት ላይ ለተመሰረቱ ሀገራት ጠቃሚ እንደሚሆን አይ ኤም ኤፍ አስታውቋል። የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሁኔታ በሪፖርቱ ደጋግሞ በበጎ ጎን የጠቀሰው ድርጅቱ፤ ኢትዮጵያ በዘንድሮው የፈረንጆች ዓመት እንደ አንጎላ ሁሉ ባለ ሁለት አሃዝ የዋጋ ግሽበት የተመዘገበባት ሀገር መሆኗንም አልሸሸገም።
አይ ኤም ኤፍ ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራትን የኢኮኖሚ እድገት ትንበያ ባስቀመጠበት ዝርዝር፤ ኢትዮጵያ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ኢትዮጵያ 7.2 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት እንደምታስመዘግብ አስፍሯል። ሀገሪቱ በመጪው የፈረንጆች ዓመት የሚኖራት የኢኮኖሚ እድገት 7.1 በመቶ እንደሚሆንም ተንብይዋል።
ይህ የድርጅቱ ትንበያ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ይፋ ካደረገው አሃዝ ያነሰ ነው። ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ከሳምንት በፊት የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶችን በይፋ በከፈቱበት ወቅት፤ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት በዘንድሮው በጀት ዓመት ወደ 9 በመቶ ከፍ ለማድረግ መንግስት ማቀዱን ገልጸው ነበር። ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2017 በጀት ዓመት “8.8 በመቶ እድገት” ማስመዝገቡንም በዚሁ ንግግራቸው አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)