የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ፤ በሁሉም አካባቢዎች በሚባል ደረጃ የጤና ተቋማት አገልግሎት “ያለምንም መቆራረጥ መቀጠሉን” ገለጹ። ሚኒስትሯ ይህን የተናገሩት የጤና ባለሙያዎች የስራ ማቆም አድማ እያደረጉ መሆኑ እና በተለያዩ ሆስፒታሎች አገልግሎት መስተጓጎሉ እየተገለጸ ባለበት ወቅት ነው።
ዶ/ር መቅደስ ዳባ ትናንት ምሽት ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የጤና ባለሙያዎች በጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች ለተኝቶ ታካሚዎችም ሆነ ለተመላላሽ ታካሚዎች “ያልምንም መቆራረጥ” አገልግሎት እየተሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።
ሚኒስትሯ አክለውም፤ “ህዝባቸውን እያገለገሉ ሁሉም የጤና ባለሙያዎች ምስጋናዬን ማረብ እፈልጋለው “ ብለዋል።
ነገር ግን “በጥቂት የመማር ማስተማር ሆስፒታሎች የአገልግሎት መቆራረጦች” መስተዋላቸውን ጠቅሰው፤ ይህንን ችግርም ከሲኒየር ሃኪሞች እና ነርሶች ጋር በመሆን “በፍጥነት አገልግሎቱን በማስጀመር መቅረፍ ችለናል” ብለዋል።
ዶ/ር መቅደስ፤ ባለሙያዎች ወደ ጤና ተቋማት ሄደው አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት አንዳንድ አካላት “ውዥንብር በመፍጠር እና በማስፈራራት ስራውን ለማስተጓጎል” እንደሚጥሩ አንስተው፤ እነዚህ አካላት ላይ በሕግ እና በጤና ስነ ምግባር ደምቡ መሰረት አስፈላጊውን እርምጃ የሚወሰድባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ሚኒስትሯ፤ በጤናው ዘርፍ በአገልግሎት ጥራት እንዲሁም በጤና ባለሙያዎች የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
“ዘላቂ መፍትሄም ለማምጣት ለጥያቄዎቻችንን በውይይት ምላሽ እንሰጣለን” ያሉት ዶ/ር መቅደስ፤ ለዚህም አሁን ላይ “በየደረጃው ውይይት እየተደረገ” መሆኑንና በቀጣይነት በየደረጃው እንደሚደረግ ገልጸዋል።