ኢራን ሁኔታው እስካላስገደደ ድረስ ከእስራኤል ጋር ያላት ግጭት ወደ ጎረቤት ሀገራት እንዲስፋፋ እንደማትፈልግ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገለጹ።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራሃቺ ከእስራኤል ጋር የተፈጠረው ግጭት እንዲስፋፋ እንደማይፈልጉ የገለፁ ሲሆን፤ ነገር ግን እራሳችንን እንከላከላለን ሲሉ ገልፀዋል።
ቴህራን ከውጭ ለሚሰነዘራባት ጥቃቶች አፀፋ ስትሰጥ ቆይታለች ያሉት አራሃቺ፤ ይህ ጥቃት ከቆመ የኢራን አፀፋመ ይቆማል ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢራን ከኳታር ጋር በምትጋራው ድንበር አካባቢ እስራኤል የፈፀመችው ጥቃት በጣም አደገኛ እንደሆነ አስረድተዋል። በአካባቢው የኢራን የነዳጅ ማጠራቀሚያ ላይ የተፈፀመው ጥቃት የነዳጅ ዋጋን እንዳናረ ተሰምቷል።
አራሃቺ እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ማብለያ መሰረተልማቶች ላይ ላደረሰችው ጥቃት አሜሪካ አጋር ናት ሲሉ የተቹ ሲሆን፤ አሜሪካ ለዚህ ጥቃት ሀላፊነት መውሰድ አለባት ብለዋል።
አሜሪካ በዚህ ጥቃት ምንም አይነት ተሳትፎ እንደሌላት ከተለያዩ ቦታዎች መልእክቶች እንደደረሳቸው የገለፁት ሚኒስትሩ ይህንን እንደማያምኑ እና ከአሜሪካ የተቃረነ ማስረጃ ያላቸው መሆኑን ገልፀዋል።
ከአሜሪካ ጋር የሚደረገው የኒውክሌር ድርድር ስምምነት ላይ ለመድረስ መንገድ ሊከፍት ይችል ነበር ያሉት አባስ አራሃቺ እስራኤል የድርድሩን ሂደት አጨናግፋለች ሲሉ መክሰሳቸውን ቢቢሲ ነው የዘገበው።