ሊቀ ኅሩያን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ
ኢትዮጵያውያን አባቶች በሕዝባቸው ላይ ይሾሙ ብለው የተከራከሩ ነገሥታትና ሊቃውንት የመኖራቸውን ያህል፤ በፍፁም አይገባንም፤ አንችለውም፣ እናቃልለዋለን ብለው የተከራከሩ አባቶች መኖራቸው በታሪካችን ተጽፏል። ወቅቱ እንዲያ እንድንል ያስገድዳልና፤ አይገባንም ብለው ከተከራከሩት ኢትዮጵያውያን አባቶች መካከል አንዱን እንጥቀስ።
በዚህኛው ጎራ በቀዳሚነት የሚጠቀሱት ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ናቸው። በገድላቸው እና በልዩ ልዩ መዛግብት ተጽፎ እንደምናገኘው ጻድቁ በዕጨጌነት የአገልግሎት ዘመናቸው ኹለት ጊዜ የኢጲስ ቆጶስነት ዕድል አግኝተው ነበር።
የመጀመሪያው በጻድቁ ዘመን የነበረ አቡነ ዮሐንስ የተባለ ግብጻዊ የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ የጻድቁን ቅድስናና ዐዋቂነት ተረድቶ፤ “ኩን ኤጲስ ቆጶሰ በመንፈቀ ኢትዮጵያ ወአነ እከውን በመንፈቃ፤ በአኩሌታው የኢትዮጵያ ክፍል ኤጲስ ቆጶስ ኹን፤ እኔም በእኩሌታው እኾናለኹ/እሾማለኹ” የሚል ግብዣ ነበር። ጻድቁ ግን አይገባኝም ብለው፤ መልሰዋል። (ገድለ ተክለ ሃይማኖት፣ 2004 ዓ.ም፣ ከገጽ 250-252)።
ኹለተኛው በወቅቱ በነበረው (የመስቀል) ጦርነት የተነሣ ዐዲስ ግብጻዊ ጳጳስ ወደሀገራችን መምጣት ባልቻለበት ጊዜ ጻድቁ በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ተመርጠው በመንበረ ጵጵስናው ላይ በመሾም ሀገሪቷን በመባረክ፣ ተዘጋጅተው ለቀረቡትም ዲቁናና ቅስና ሲሰጡ ቆይተዋል። ጦርነቱ ተጠናቅቆ፣ ሰላም ሰፍኖ፣ በመንበረ ማርቆስ ተሹመው የተላኩት አባት ኢትዮጵያ በደረሱ ጊዜ ጻድቁ በክብር ተቀብለው፣ ለዓመታት ተግተው ያገለገሉበትን መንበረ ጵጵስና ለመጡት ዐዲስ ግብጻዊ ጳጳስ ከአክብሮት ጋር አስረክበዋል።
ጻድቁ አይገባኝም/አይገባንም ካሉባቸው ምክንያቶች የሚከተሉት ይጠቀሳሉ። የመጀመሪያው፤ ግብጻዊ አባት በመንበሩ ካለ ሕዝቡን ኹሉ ያለምንም ማዳላት እኩል ያስተዳድራል፤ ኢትዮጵያዊ ከኾነ ግን ለዘር ለወገኑ ሊያዳላ ይችላል የሚል ነው። ኹለተኛው ምክንያት ኢትዮጵያውያን በመንበሩ ላይ መሾም ከጀመሩ ሊቃውንቱና ገዳማውያኑ የእኛ ሰው ይሾም፣ የዚህ አካባቢ ሰው ይሾም በሚል ይከፋፈላሉ፤ ባዕዳን በመንበሩ ከተቀመጡ ግን አንዱ ሌላውን በመውቀስ ሽኩቻ ውስጥ አይገቡም ከሚል የመነጨ ነበር።
ይህ የጻድቁ ሐሳብ ብዙ ትውልድ አልፎ ዛሬም የሚከራከሩለት ሰዎች እንዳሉ ለዚህ አጭር ሐተታዬ ምንጭ ያደረኩትን ዜና ጳጳሳት (1997 እና 2012 (ገጽ 2-5 እና 51-52)) መጽሐፌን ለማዘጋጀት ከተለያዩ ሊቃውንት ጋር ስወያይ ተገንዝቤአለኹ። ጻድቁን ጨምሮ ሐሳባቸውን የሚያራምዱት ያለፉትም ይኹኑ በሕይወት ያሉት ሊቃውንት እየኾነ ያለውን ጉድ ሲያዩ ምን ይሉ ይኾን?
ከ1600 ዓመታት በኋላ፣ 111 ግብጻውያን ጳጳሳት እየተፈራረቁ ከተሾሙብን በኋላ፤ በ1921 ዓ.ም. መንበረ ጵጵስና በቤተ መንግሥቱ ድጋፍ በኢትዮጵያውያን አበው ተያዘ። በቤተ መንግሥቱ ጋላቢነት አንድ እርምጃ ወደፊት አምስት እርምጃ ወደኋላ የኾነውን ሶምሶማ ሩጫውን ሲሮጥ ከእኛ ዘመን ደረሰ። ዛሬ የኾነውንና እየኾነ ያለውን እያየን እየሰማነው ነው። የልጆቹን ደም የማያይ፤ ጩኸታቸውን የማይሰማ፤ ለመጻሕፍቱ ሐተታ ባይተዋር፤ ለሊቃውንት ድምጽ ባዕድ የኾነ ራስ ወዳድ፤ ግዙፏን ቤተ ክርስቲያን በሰፈር አሳንስሻለሁ ያለ ከንቱ። ጻድቁ ወደዬት አሉ? ምነው በእርስዎ ዘመን ተፈጥረን በነበረ?
*** *** *** ***
“ከሁለተኛው ፓትርያርክ ጀምሮ እስከ አሁን የመጣንበት ጉዞ ሲገመገም አመርቂ አይደለም ፤ አካሄዳችን ሁሉ ለፈተና የሚዳርግ ነው”
ባሳለፍነው ሳምንት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በተደረገ የኤጲስ ቆጶሳት በዓለ ሢመት ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ይህንን አሉ። ለምን? ቅዱስነታቸው ያሉትን ጨምሮ በአጠቃላይ ጵጵስና በኢትዮጵያውያን አበው ከተያዘበት 1921 ዓ/ም ጀምሮ ያጋጠሙ ፈተናዎች (ዋና ዋናዎቹ) የሚከተሉት ናቸው።
፩/ የመጀመሪያዎቹ አምስት ኢትዮጵያውያን አባቶች ከተሾሙ በኋላ ሀገረ ስብከት የተደለደሉት በራሳቸው ጉባኤ (ሲኖዶስ) ሳይኾን በቤተ መንግሥቱ ነበር። በመኾኑም መንበሩ ገና ከጅምሩ በቤተ መንግሥቱ ተሸብቧል።
፪/ የመጀመሪያዎቹ ተሿሚዎች ቀደም ሲል በቤተ መንግሥቱ ተፈጥሮ በነበረው የንግሥቷና አልጋ ወራሹ ውስጣዊ መቃቃር የተነሣ ለንግሥት ለንጉሥ በሚል ተለያይተው ነበር። በመኾኑም አንዳንዶቹ ለአንዱ ወግነው ሌላውን አኩርፈዋል።
፫/ በ1928 ዓ/ም ፋሺስት አገራችንን ሲወር ከነበሩት አራት የመጀመሪያ ተሿሚዎች ኹለቱን ገድሏል፤ አንዱን አግዟል፤ አንዱን ሊቀ ጳጳስ ብሎ ሾሟል።
፬/ በፋሺስት ፈቃድ በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ሊቀ ጳጳስ ኾነው ኅዳር 21 ቀን 1930 ዓ/ም የተሾሙት (አቡነ አብርሃም) በዕለቱ አምስት ኢትዮጵያውያን ኤጲስ ቆጶሳትን ሾሙ። የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን አቡነ አብርሃምንና የሾሟቸውን አወገዘች።
፭/ በውግዘት ላይ የነበሩት ብፁዕ አቡነ አብርሃም ሐምሌ 14 ቀን 1931 ዓ/ም ሲያርፉ፤ ቀደም ሲል ከሾሟቸው አንዱ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ሊቀ ጳጳስ ተብለው መስከረም 1 ቀን 1932 ዓ/ም ተሾሙ፤ እሳቸውም በተራቸው ስድስት ኤጲስ ቆጶሳትን ሾሙ።
፮/ በ1933 ዓ/ም ወራሪው የጣልያን ኃይል ድል ተነሥቶ ከአገሪቱ ሲወጣ፤ ንጉሡም ሲመለሱ ከላይ በአቡነ አብርሃም እና በአቡነ ይስሐቅ የተሾሙት በሙሉ በቤተ መንግሥቱ ተሻሩ። በኢትዮጵያውያን ተይዞ የቆየው መንበር ተነጥቆ ለግብጻዊው አቡ ቄርሎስ ተሰጠ። የተሾሙትን የሻረ፣ መንበረ ጵጵስናውንም ከኢትዮጵያውያኑ እጅ ነጥቆ ለግብጻዊው የሰጠው ቤተ መንግሥቱ ነው።
፯/ ሐምሌ 18 ቀን 1940 አምስት ዐዳዲስ ኢትዮጵያውያን ኤጲስ ቆጶሳት በመንበረ ማርቆስ ተሾሙ። ግብጻዊው የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ሲያርፉ፤ ከተሾሙት አምስቱ ኤጲስ ቆጶሳት አንዱ አቡነ ባስልዮስ ጥር 6 ቀን 1943 ዓ/ም ሊቀ ጳጳስ ዘኢትዮጵያ ተብለው ተሾሙ። ሊቀ ጳጳሱም ይኹኑ ኤጲስ ቆጶሳቱ በቤተ መንግሥቱ ጥላ ሥር እንዳሉ ሰኔ 21 ቀን 1951 ዓ/ም ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ ሊቀ ጳጳስ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ተብለው ተሾሙ። የቀኖናን ጥሰት በቀኖና ማስተካከል በሚል በጣልያን ወረራ ጊዜ ከተሾሙት ጥቂቱን እንደገና ካኑ (በወቅቱ አባባል ከለሱ)። ይህም እስኪረሳ ድረስ በሊቃውንቱና በሲኖዶሱ መካከል መለያየትን ሲፈጥር፤ ቤተ መንግሥቱ ግን ደፍጥጦታል።
፷/ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ሲያርፉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ግንቦት 5 ቀን 1963 ዓ/ም ኹለተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ኾነው ተሾሙ። የጀመሯቸውን መልካም ሥራዎች ሳይገፉ፤ በሲኖዶሳቸው ይሁንታ ወይም ዝምታ የካቲት 9 ቀን 1968 ዓ/ም በወታደራዊው መንግሥት ከመንበረ ፕትርክናቸው ተወግደው ለእስር ተዳረጉ። እሳቸው በእስር ላይ ሳሉ ፤ በቤተ መንግሥቱ ጫናና አስፈጻሚነት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሣልሳዊ ፓትርያርክ ተብለው ነሐሴ 23 ቀን 1968 ዓ/ም ተሾሙ። “የተቀባ ፓትርያርክ ሳይሞት በላዩ ላይ ሌላ ፓትርያርክ አይሾም” የሚለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ተጣሰ። የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን፣ ሌሎች አኀኀት አብያተ ክርስቲያናትም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን አወገዙ። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስም ከሦስት ዓመት የእስር እንግልት በኋላ ሐምሌ 7 ቀን 1971 ዓ/ም ታንቀው ተገደሉ።
፱/ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላትም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በመቃወም የተለዩ አባቶች ነበሩበት። የዛሬው ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስ አንዱ ናቸው። በመቃወማቸውም ፓትርያርኩ የውግዘት ቃል ተላልፎባቸዋል።
፲/ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት መንበር ተተክተው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ነሐሴ 29 ቀን 1980 ዓ/ም አራተኛው ፓትርያርክ ኾነው ተሾሙ። የመንግሥት ለውጥ ሲመጣ ቅዱስነታቸው መንበራቸውን ትተው ስደት ገቡ። እሳቸው በሕይወት እያሉም ሐምሌ 4 ቀን 1984 ዓ/ም አምስተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ኾነው ተሾሙ። ቀኖና ቤተ ክርስቲያን መጣሱን ቀጠለ
፲፩/ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በስደት ሳሉ ተከትለዋቸው የኼዱትን ሊቃነ ጳጳሳት ይዘው ሲኖዶስ አቋቁሜያለሁ አሉ። የአንዲቷ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ኹለት ኾነ። ቆይቶም ኤጲስ ቆጶሳትን ሾሙ። ውግዘት ኡትዮጵያ ካለው ሲኖዶስ ተላለፈ፤ ከዚያም ወደኢትዮጵያው ተላለፈ። የኋላ ኋላ አንድነት ተፈጠረ የውጪው ገባ። የውስጡም ተቀበለ።
፲፪/ በውጭ የተጀመረወረ ስንጥቅ በውስጥም ሊፈጠር፤ የተወሰኑ መነኮሳት ስለተገፋን ጳጳስም ፓትርያርክም ኾነናል ባሉ በሦስተኛው ዓመት፤ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ/ም ሦስት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ራሳቸው መራጭ፣ ራሳቸው ሿሚ ኾነው ፣25 ኤጲስ ቆጶሳት ሾመናል ብለው ዐወጁ። ተወገዙ አወገዙ። ሰላም መጣ ተባለ።
፲፫/ ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ/ም ጥር 14 ቀን 2015 ዓ/ም ኤጲስ ቆጶሳት ተብለው ተክነዋል ከተባሉትና ከተወገዙት ውስጥ ሦስቱ እንደገና ተመርጠው እንደገና ተካኑ።
፲፬/ በሌላም በኩል አኩርፈናል ያሉና ቀደም ሲል የራሳችን ቤተ ክህነት አቋቁመን ተለይተናሉ ያሉ አራት ሊቃነ ጳጳሳት ልንሾም ነው ብለዋል። ወይም ሾመዋል።
ቅዱስነታቸው “አመርቂ አይደለም” ባሉትና መቶ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ዓመታት ብቻ በቀሩት በዚህ የኢትዮጵያ የመንበረ ጵጵስና ወፕትርክና ጉዞ በቅድስና አገልግለው ያለፉ፣ እያገለገሉም ያሉ አባቶች አሉ። የውስጡ ችግር እንዲስተካከል፤ የውጩም እንዲመከት በጥብአት የታገሉ ፣ የሚታገሉም አባቶች አሉ። በደምም ካለደምም ሰማዕታት የኾኑ አሉ።
ስለዚህ ጥቂቶቹ እንዲበዙ የባሰ ጊዜም እንዳይመጣ መወያየት፣ ሐዘንንና ቁጭትን አየታገሱ ቀርቦ በጋራ መሥራትን ይጠይቃል። የታየውና የሚታየው ምስቅልቅል የዘመናት ድምር ውጤት ነው። የሚመጣው ካለፈው እንዳይበዛ እየመረረም ቢኾን መወያየት፣ መከራከርና መመካከር ያስፈልጋል። የኾነው ኹሉ ወደፊት እንዳይደገም ይኹን ብሎ ተቀብሎ መታገል ሳይሻል አይቀርም።
መንበረ ጵጵስናም ይኹን ፕትርክና በአስተምህሮዋ ነቅዕ የሌለባት፣ አሐቲ፣ ኵላዊት፣ ቅድስትና ሰማያዊት የሆነች ቤተ ክርስቲያን መገልገያ መሣሪያ ነው። ይህ መሣሪያ በአሠራሩም ይኹን በእርምጃው አመርቂ ባይኾን፤ የማዳን ሐዋርያዊ ጉዞዋ በሰው ኅሊና የማይገመገም ቤተ ክርስቲያን ልጆች ተስፋ መቁረጥ አይጠበቅባቸውም። ይልቁንም አሻግረው ሳያዩ በቅርባቸው ባለች ቤተ ክርስቲያን ቢተጉ፤ ቢታገሉ መልካም ይኾናል።
ለመሪዎቻችን ጥበብን ከጥብአት ጋር አብዝቶ ይስጥልን።