በዓመት አንድ ጊዜ የሚደረገው ዓለም አቀፉ የሰበካ መንፈሳዊ ጠቅላላ ጉባኤ ከጥቅምት ፬-፰ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤ/ክህነት በሚገኘው አዲሱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሄዷል፡፡
መሠረቷ የማይናወጽ ላዕለ ኵሉ ጉባኤ ዘአበው ሐዋርያዊት የሆነች፣ አንድነቷ የማይከፈል ቅድስት፣ ጥንታዊትና ታሪካዊት፣ በርኀበ ዓለም ሰፋኒት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ፵፬ኛው ዓመታዊና መደበኛ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ዓለም አቀፍ ጉባኤ የ፳፻፲፯ በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም በመስማት እና በመገምገም፣ ያለንበትን ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያናችን ሁኔታ መሠረት ባደረጉ ርእሰ ጉዳዮች ተወያይቶ የደረሰበትን የመፍትሔ ሐሳብ በማካተት የስብሰባው የአቋም መግለጫ ከዚህ ቀጥሎ ቀርቧል፡፡
መደበኛውና 44ኛው ዓለም አቀፍ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ ከጥቅምት 4- 8 ቀን 2018 ዓ/ም በነበረው የጉባኤ ሂደትና የስብሰባ ሥነ ሥርዓት፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጁ የሰከነ የመድረክ አመራርና አሳታፊነት፣ ያልተዛነፈ የሰዓት አጠቃቀም፣ በወጣው መርሐ ግብር መሠረት በመመራት የቤተ ክርስቲያንን ክብርና ልዕልና የሚመጥን፣ ለውይይትና ምክር ተገቢውን ጊዜና ቦታ የሰጠ፣ የጉባኤው ተሳታፊ በተሰጡት የትኩረት አቅጣጫዎች፣ የሚችለውን ተሳትፎ ያደረገበት ሁሉንም ያስደሰተና ተስፋ የሰጠ በመሆኑ እያመሰገንና ለወደፊቱም በዚሁ ዓይነት የተረጋጋ መደማመጥ የሰፈነበት መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት እንዲቀጥል ጉባኤው እያሳሰበ፤
በ44ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ከቅዱስ ፓትርያርኩ አባታዊ ቃለ በረከት፣ ከብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጁ አባታዊ መልእክት፣ የትኩረት ነጥቦች፣ መመሪያና የጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱ ሪፖርት፣ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የተሰጡ ቃለ እግዚአብሔር ከሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የተላለፉ ልዩ ልዩ መልክቶች፣ ከመላው ዓለም አህጉረ ስብከት ሪፖርት እና በየምድቡ ከተደረጉ ውይይቶችና ምክክሮች በመነሣት ጉባኤው ከዚህ ቀጥሎ ያለውን አቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡
ዓመታዊና መደበኛ የሆነው የ፵፬ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ዓለምአቀፍ ጉባኤ የጋራ አቋም መግለጫ
- ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ጉባኤውን በአባታዊ ቃለ በረከት ሲከፍቱ “ዑቁ እንከ ዘከመ ተሐውሩ ከመ ጠቢባን በንጹሕ ወአኮ ከመ ዓብዳን” ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት በንጽሕና እንድትመላለሱ ዕወቁ” (ኤፌ ፭፡፲፭) በሚል የሰጡትን ቃለ በረከት የሥራችን መመሪያ አድርገን ለመሥራት ቃል እንገባለን፤
- ብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅ “ሠናይ ለነ ወይደልወነ ዘበጽድቅ ዘክሮቶ ለእግዚአብሔር በኵሉ ጊዜ – ለእኛስ በምግባር በሃይማኖት ጸንተን በእውነት ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን ልናስበው ይገባናል፥ መልካምም ይሆንልናል” በሚል ርዕስ ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ባስልዮስ ፴፫፥፪ በመጥቀስ ያስተላለፉት አባታዊ መልእክት በ፳፻፲፯ የበጀት ዓመት ካቀረቡት የሥራ ሪፖርት በመነሣት የሰጡት ማጠቃለያና ለያዝነው የ፳፻፲፰ ዓ/ም በጀት ዓመት ትኩረት ሰጥተን እንድንሠራባቸው የትኩረት አቅጣጫን በመለየት የሰጡትን አባታዊ መመሪያ በመከተል ሁላችንም በተገቢው መንገድ በእውነት እና በትጋት ለመፈጸም ቃል እንገባለን፡፡
- በብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅ ከፍተኛ ጥንቃቄ፣ ከመደበኛው አገልግሎታችን በተጨማሪ በልዩ ትኩረት እንዲፈጽማቸው ተመርጠው የተሰጡት
ሀገራዊ ሰላምና የቤተ ክርስቲያን አንድነት፣
በስብከተ ወንጌልና ሁሉን አቀፍ የአገልግሎት ተደራሽነት ያለው ገጠሩን ያማከለ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት፣
ወቅቱን የቀደመ እጅግ ዘመናዊ የሆነ የአስተዳደርና ፋይናንስ አደረጃጀትን ማጠናከር፣
ቤተ ክርስቲያንን ከልመና የሚያወጣ ፈጣንና ውጤታማ የልማት ሥራ መሥራት እና
የዘመናዊ ቴክኖሎጅ መሠረተ ልማትን ለተቋማችን ጥንካሬና ተደራሽነት ካለው አስፈላጊነት አንጻር ጥቅም ላይ ለማዋል ሁላችንም የሚጠበቅብንን ሁሉ ለመፈጸም ቃል እንገባለን፤
- በብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅ አባታዊ አመራር በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ግቢ “አጸደ ቤተ ክህነትን” የማስተካከልና የማስዋብ ሥራ የመልካም አስተዳደር ዋና ምሰሶዎች ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ ውብ፣ ማራኪና ምቹ የሥራ አካባቢን መፍጠር በመሆኑ ይኽንን አርአያት ያለው አሠራር በየአህጉረ ሰብከት በመውሰድ ተግባራዊ ለማድረግ ቃል እንገባለን፤
- በየአህጉረ ሰብከታችን የአብነት ጉባኤ ቤቶችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መስፋፋትም ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ዕውቀት መዳበር፣ ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት፣ ካለው ጠቀሜታ አንፃር ቅዱስ ሲኖዶስም ልዩ ትኩረት ስለሰጠው እጅግ ከፍ አድርገን እያመሰገንን በሁሉም ደረጃ የሚገኙ የትምህርት እንቅስቃሴዎች የቤተ ክርስቲያናችን የጀርባ አጥንት ከመሆናቸው አንፃር ለሁሉም የትምህርት መስኮችና ለጉባኤ ቤቶች መጠናከር ልዩ ትኩረት በመስጠት ትምህርት መዋቅርን አስፋፍቶ ለመሥራት ቃል እንገባለን፡፡
- የሙያ ማሻሻያና የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች፣ ጉዳይ ተኮር የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት ተግባር ላይ የማዋል ባህል እንዲዳብር ሂደቱም ከፍተኛ ጥቅም ያስገኘ በመሆኑ፣ ሥልጣናዎች፣ ውይይቶችና ምክክሮች ችግርን በጥበብ ለመፍታት፣ ሁለንተናዊ ግንኙነትን ለማጠንከር፣ ተቀራርቦ ለመሥራት የሚያስችል አቅም የሚፈጥሩ ስለሆኑ አጠናክረን ለመቀጠል ቃል እንገባለን፤
- የሰንበት ት/ቤት ማደራጃ መመሪያ ከሊቃውንት ጉባኤ ጋር በመሆን ያዘጋጀው ማእከላዊነቱን የጠበቀ የሰንበት ተምህርት ቤቶች ማስተማሪያ መጽሐፍ ኅትመት እና ሥርጭት መከናወኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየጠየቅን፣ በየቋንቋው እየተተረጎመ በስፋት ሥራ ላይ ለማዋል ቃል እንገባለን፤
- በአዲስ አበባና በየከተማው እየተስፋፋ ያለው የኮሪደር ልማት ተግባር ያመጣው መልካም አጋጣሚ እንደተጠበቀ ሆኖ በልማትና አካባቢን ለኑሮ ምቹ የማድረግ ሥራው በእኛም በኩል ተገቢውን ትኩረት በመስጠት የቤተ ክርስቲያንን ተሳትፎ በማሳደግና የቤተ ክርስቲያንን ይዞታዎች መብት የማስከበር ሥራ በመሥራት ከእድገት ወደኋላ ሳንቀር የሚጠበቀውን ተሳትፎ ለማድረግ ቃል እንገባለን፤
- የቤተ ክርስቲያንን የአምልኮ መካናት፣ የበዐላት ማክበሪና የሥርዓት መፈጸሚያ ቦታዎች ለማስከበር የይዞታ ማረጋገጫ ለማግኘት ከአካባቢ የመንግሥት መዋቅር ጋር ተባብሮ በመሥራት መብትን የማስከበር ሥራዎች በተገቢው ፍጥነት አና ደረጃውን በጠበቀ የአሠራር ጥራት ለመፈጸም ቃል እንገባለን፤
- የቤተ ክርስቲናችን አገልግሎት ሁነኛ መሠረት የሆነቸውን የገጠሪቱ ቤተ ክርስቲያን መጠናከርና ሕልውና ላይ ትኩረት አድርጎ በመሥራት የምእመናንን ደኅንነት እንዲጠበቅ፣ የአገልጋይ ካህናት የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል፣ ስብከተ ወንጌልና የኖሎት አገልግሎት እንዲደራጅ የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማደረግ ቃል እንገባለን፤
- ዘመኑ እንዳይቀድመን፥ ትውልዱንም በሚገባ ሳናገለግል እንዳንቀር የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በዕቅድ እንዲመራ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጅን ያለውን ጠቀሜታ ግምት ውስጥ በማስገባት ከፍተኛ ባለሙያዎች የሆኑ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን በማሳተፍ፣ ወቅቱን የዋጀ፣ ከዘመኑ የቀደመ፣ አሠራርን በየአህጉረ ሰብከታችን ለመተግባር ቃል እንገባለን፤
- በየአህጉረ ሰብከቱ ልማትን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ፥ ለመጨው ዘመን ቅርስ ሚሆኑ ግንባታዎችን በማስፋፋት በአህጉረ ሰብከትና በወረዳ (በክፍለ ከተማ) እና በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች በማስፋፋት የቤተ ክርስቲያንን የማኅበራዊና የኢኮኖሚ ሕልውና በጽኑ መሠረት ላይ ለመስቀመጥ ቃል እንገባለን፤
- ገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ሕልውናቸው ተጠብቆ ራሳቸውን እንዲችሉ፣ ከልመና እንዲወጡ በሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች፥ በአገልግሎት መዳከም የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናትን ለማስከፈት የሚቻለውን ሁሉ ጥረት ለማድረግ ቃል እንገባለን፤
- መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር ለማስጠበቅ፥ ወቅታዊ ችግር ያመጣውን የሰላም እጦትና ስጋት ተቋቁሞ መንፈሳዊ አገልግሎትን ለማካሄድ፣ አንዲት ቤተ ክርስቲያን፥ አንድ ሲኖዶስ፥ አንድ ፓትርያርክ፥ አንድ መንጋ በማለት የቤተ ክርስቲያንን እንድነት ለማስከበር ፈሪሃ እግዚአብሔርና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንዲጠበቅ፣ ቤተ ክርስቲያንን የዓለማዊ ሐሳብ ማራመጃ እንዳትሆን የሚከፈለውን መስዋእነት ሁሉ በመክፈል አንድነቷን፣ ሕልውናዋን፣ ሉዓላዊነቷንና ነጻነቷን ለማስከበር ቃል እንገባለን፤
- ምግባረ ሠናይን በማስፋፋት እውነተኛ ኖሎት በመሆን ምሳሌያዊነትን ለማጠንከር፣ የተፈጥሮ ሀብት ሆነ አጸዶቿን፣ የሃይማኖትና የሥነ ጥበብ ቅርሶቿንና ዘመን ተሻጋሪ ጥንታዊ ሀብቶቿ ለማስጠበቅ፣ ትናንትን አጥብቀው ከሚጠሉ፣ ታሪክን ከሚያረክሱ፣ ያለስሟ ስም በመስጠት ነባር ዕሴቷን ከሚንዱ ዘመን አመጣሽ ሐሳውያን ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ ቃል እንገባለን፤
- አሉታዊ ከሆነ የማኀበራዊ ሚዲያን አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የስም ማጥፋትንና የሐሰት ትርክቶችን መስፋፋት ለመከላከል ለወጣቱ ትውልድ ተገቢውን ዕውቀት በመስጠት፣ የሕግ አገልግሎትን በማጠናከር በፍትሕ ተጠያቂ በማድረግ በየትኛውም ሁኔታ የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ፣ ዶግማና ቀኖና፣ ታሪክ፣ ዘላለማዊ ሕልውና፣ ሁለንተናዊ ትምህርትና ምሥጢራት ከሚበርዙ ሕገ ወጦች ሁሉ እናት ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ ከእኛ የሚፈለገውን ሁሉ ለማድረግ ቃል እንገባለን
- የኪራይ ግብር ስለ መክፈል አለባችሁ በሚል የቀረቡ ጥያቄዎችና ሌሎች በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤና በጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱ ክትትል ተደርጎ ሊፈጸሙ የሚገባቸው ጉዳዮች በበላይ አካል ትኩረት ተሰጥቷቸው አንድ ዓይነት አሠራር ለመላዋ ቤተ ክርስቲያን እንዲፈጸም ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር በመወያየት ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጠው በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፤
- የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በአልታወቁ ሰዎች የሚደርስ ግድያ ጉባኤው አጽንዖት እንዲሰጠው እየጠየቀ በአንዳንድ አህጉረ ሰብከት የአቅም ማነስ፥ የሕገ ወጥ ማኀበራት ጉዳይና መሰል ችግሮች ለመፍታት የበኩላችንን ለማድረግ ቃል እንገባለን።
- በሀገራችን እየተከሰቱ ያሉ በርካታ ችግሮች የኢትጵያን እደገትና የሕዝቧን ልእልና ማየት የማይፈልጉ የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት ያለባቸው በመሆኑ ይኽንን ጣልቃ ገብነት ታላቁ ጉባኤ አበክሮ እያወገዘ ሀገራችን ሙሉ ሰላም እንድትሆንና የቤተ ክርስቲያናችን ልዕልና ታፍሮና ተከብሮ እንዲኖር፣ የሕዝባችን አንድነት እንዲረጋገጥ የአባቶቻችን ጸሎት፣ የቅዱሳን ጻድቃን፣ ሰማእታትና መላእክት ሁሉ አማላጅነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ልመና የልዑል እግዚአብሔር አምላካችን ቸርነት ይርዳን እያልን፤
፵፬ኛውን ዓለም አቀፉ የሰበካ መንፈሳዊ ጠቅላላ ጉባኤ በሰላም ያስፈጸምን አምላክ ከሚቀጥለው ዓመት አድርሶ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችንንና ብፁዓን አበዊነ ሊቃነ ጳጳሳት በተሟላ ጤንነት ጠብቆ ሐዋርያዊ ሥራችሁንም የተሳካ አድርጎ በአባታዊ ጸሎታችሁና በረካታችሁ እኛንም ጠብቆና አክብሮ በሰላም እንዲያገናኝን ፈቃዱ ይሁንልን እንላለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ጥቅምት ፰ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም.
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ