ከአባታቸው አቶ ኢድሪስ ዘለቀ እና ከእናታቸው ወ/ሮ መነን ሽፋው፣ በ1924 ዓ.ም. በወሎ ቦረና ገነቴ አካባቢ ልዩ ስሙ “ዳሎታ” በተባለ መንደር ነው የተወለዱ። ለአባትና ለእናታቸው ዐራተኛ ልጅ ነበሩ።
የልጅነታቸው የመንፈስ ምሪት በቤተሰብ ሥነ ልቡናዊ ቅኝት ቢታጠርም፣ ወሰኑን ሰብረው እስከ ኅልፈት ለተንጸባረቁበት የሕይዎት ዳና እራሳቸውን ሰጡ። ከምቾት አፀድ ወጥተው ከሥጋ ድካም ጋር የሚፀድቁበትን ዕጣፈንታ ገለጡ።
አዕምሯዊ፣ ሃይማኖታዊና ሥነ ልቡናዊ ዕውቀቶችንና ልምምዶችን ከዐስራ ሦስት የኢትዮጵያ ዓሊሞች ሲገበዩ ለማጠናቀቅም 35 ተከታታይ ዓመታትና የሙሉ ጊዜ ጥረት ወስደው “መምህር(ሙደሪስ)” የኾኑት በተማሪነታቸው(በደረስነታቸው) ወቅት – በዳሎታ፣ በጥላንታ፣ በከቶ የዕውቀት ማዕከላት ነበር፡፡ በሦስት የዕውቀት መምህሮቻቸው “የመምህርነት ፈቃድ(ኢጃዛ)” ተችረው ዕውቀት ፈላጊዎችን ያስተምሩ፣ ለመምህርነት አብቅተውም ያሰማሩ ነበር፡፡
ተቀዳሚ ሙፍቲ የዕውቀት፣ የሃይማኖት፣ የማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን በመመስረት ሂደት ከዐስራ አምስት ዓመታቸው ጀምሮ ተሳትፈዋል። በአዲስአበባ 9 መስጅዶችን፣ በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል በመቶዎቹ የሚቆጠሩ የዕውቀትና የአምልኮ ተቋማት እንዲመሰረቱ አስችለዋል፡፡
በ1967 የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጠቅላይ ም/ቤት ቀዳሚ መስራች አባል ኾነው እስከ 2014 ድረስ ደማቅ አሻራ አስቀምጠዋል፡፡ ለተቋሙ ሕጋዊ ተክለ-ሰውነት በማጎናጸፍ፣ የኢስላማዊ ባንክ፣ ሚዲያዎች፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንዲመሠረቱና እንዲስፋፉም አበረታትተዋል፡፡
በ1959 ወደ አዲስአበባ ከአቀኑበት ጊዜ ወዲህም፤
1).ከ1960 ጀምሮ በኑር መስጅድ ለ16 ዓመታት በምክትልነት እና ለ3 ዓመታት በዋና ኢማምነት
2).በ1967 የቀዳሚው የእስልምና ጉዳይ ጠ/ም/ቤት መስራች አባል
3).የቀዳሚው የኢትዮጵያ ዓሊሞች ጉባኤ ሰብሳቢ
4).የቀዳሚው የኢትዮጵያ ዓሊሞች የፈትዋ ኮሚቴ መስራችና አባል
5).የሐገር አቀፍ የዑለማ ጉባኤ ሰብሳቢና ሙፍቲ የነበሩ ሲኾን በዚሁ ወቅት በዐስራ አንድ ዓመታት ውስጥ በ58 የኢትዮጵያ ከተማዎች ተዟዙረው በሙስሊሞችና በሙስሊሞች እንዲሁም በሙስሊሞችና በሌሎች ወገኖች መካከል ከ130 በላይ ለቅራኔና ለግጭት የጋበዙ አጀንዳዎችን እልባት መስጠት ችለዋል፡፡
6).የአዲስአበባ የእስልምና ጉዳዮች ጠ/ም/ቤት ምክትል ሰብሳቢና ለዘጠኝ ዓመታት ዋና ሰብሳቢ
7).የኢፌድሪ የእስ/ጉ/ጠ/ም/ቤት የሐጂ እና ዑምራ ዘርፍ እንዲሁም የዳዕዋና የትምህርት ዘርፍ ተጠሪ
- በ2010 በተቋቋመው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ
9) ከ2011-2014 የኢትዮጵያ የእስ/ጉ/ጠ/ም/ቤት ፕሬዝደንት
10) ከ1960-2018 ድረስ በተለያዩ መስጅዶች በመምህርነት፣ በስነ ምግባር እነፃ፣ በመካሪነት፤ አገልግለዋል፡፡
በብሔራዊ የሰላም፣ የዕርቅ፣ የሽምግልና፣ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ኮሚቴዎች እና ቡድኖች አባል እና አስተባባሪ በመኾን ያገለገሉበት አጋጣሚም ሰፊ ነው፡፡
እንደ ገለልተኛ ጸሐይ አንጸባራቂ በኾነው በ“ሠውነት ይቀድማል” መርሃቸው የሚታወቁት ሙፍቲ ሐጂ ዑመር – ኢትዮጵያን ከአንደበታቸው ሳይዘነጉ፣ ከዱዓቸው ሳያጎድሉ፣ የእንባ ዘለላቸውን ሳይከትሩ ለሐገር ታምነው፣ በሐገር ፍቅር ተሸምነው ኑረዋል፡፡ በዓድዋ የተሰው አጎታቸውን አርበኛ ፋርስ ቱፋን በክብር ኩራት ከማመስገን ጀምሮ፣ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ከግብጻዊያን አቻ ሊቀ ሊቃውንት ጋር በአደባባይ እስከመሟገት የሚወሳ ተጨባጭ በረከት አላቸው፡፡
በአስቸጋሪ ወቅቶች ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚበጅ አቅጣጫ በመስጠት፣ መንፈሣዊ ግሳጼ እና ለበጎ ስራ ቡራኬ በመለገስ ለሐገር ሰላማዊ ሽግግር እንዲሁም መረጋጋት ንጡህ ድርሻ አላቸው። አዲሱ ትውልድ ሐገሩን እንዲያፈቅር፣ ሁሉም ዜጋ ለሐገሩ እንዲተባበር ከመምከር ታቅበው አያውቁም።
በትዳር ዓለም ከባለቤታቸው ወ/ሮ ሐሊማ ዐብዲልጀሊል ጋር 9 ልጆችን አፍርተዋል። እልፍ አዕላፍ ዓሊሞችንና ደረሳዎችን፣ የዕውቀት ማዕከላትን ተክተዋል፡፡ በእግራቸው ተጉዘው ያከናዎኑትን ጨምሮ አርባ ጊዜ የሐጂ ሥነ ስርዓት አከናውነዋል፡፡ እስከ መስከረም 2018 ድረስ አካላዊ፣ አዕምሯዊ፣ መንፈሳዊ ንቃታቸው እጅግም የተሟላ ነበር፡፡
ከሳምንቶች በፊት በአጋጠማቸው ድንገተኛ ሕመም ምክንያት የሕክምና ክትትል ሲያደርጉ ቆይተው ዕለተ ዕሁድ ጥቅምት 9 ቀን 2018 ከዚህ ዓለም አርፈዋል፡፡
የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪ ስርዓተ ቀብራቸው ጋርመንትን አልፎ ከመስጊዳቸው ጎን በሚገኘው መካነ መቃብር በዛሬው እለት 10፡00 ሰአት ላይ ይፈፀማል።