ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ኅልፈተ ሕይወት የተሰማቸውን ኀዘን ገለጹ።
“እግዚአብሔር በየዘመናቱ አገርን ያለ መካሪ፣ ሕዝብን ያለዘካሪ አይተወውም” ያሉት ቅዱስነታቸው፤ “ለዚህም ምስክየተጠቁት ወዳጅ ፣ የትውልድ አባት የሆኑት የክብር ዶክተር ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ነበሩ” ብለዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመልዕክታቸው፥ “ኢትዮጵያ በጣት ከሚቆጠሩ አረጋውያን፣ አፈ ማር ከሆኑ መካሪዎችዋ መካከል አንዱ የሆኑትን፣ ለመወደድ የታደሉትን የዘመናችን ጌጥ አጥታለች” ሲሉ ገልፀዋል፡፡
“ይህንን የድካም ዓለም መገላገል ለእርሳቸው ዕረፍት ቢሆንም ለአገር ግን ታላቅ ጉዳት ከመሆኑም በላይ ዕድሜን ከጥበብ ጋር ያዋሐዱ በሁሉ ዘመን አይገኙምና ኀዘናችን ጥልቅ ነው” ነው ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ።
አያይዘውም ለቤተሰቦቻቸው፣ ለእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡