አገር ጥቁር ትልበስ!

Date:

ቃለ መጠይቅ የማድረግ እድል ሳገኝ ኢቲቪ ገብቼ ዓመትም አልሆነኝ። ገና አዲስ ማይክ ያዥ ነበርሁ።

የእስልምና እምነት ተከታዮች በዓል ነበርና ስለመንዙማ ለመስራት እሳቸውን ደውዬ በመኖሪያ ቤታቸው ስርዓቱን ለመከወን ፍቃደኛ ሆኑ።

ደረስን። ሌሎች አባቶችን ሰብስበው ተቀበሉን።

የሃይማኖት በዓላትን መስራት ከባድ የሚያደርገው የቤተ እምነቱን ሥርዓት መጠበቅ፣ ሕግጋትን ማክበር የግዴታ ግዴታ መሆኑ ብቻም ሳይሆን ስህተት ብንፈጥር በተቋምም ሆነ በግል የሚመጣውን ጫና ጥያቄ መመለስ ከባድ ነው። ገና ጀማሪ ስትሆኑ ደግሞ አስቡት።

እኔ የእምነቱ ተከታዮች የሚለብሱትን ድርያ ብለብስም እየተንሸራተተ ፀጉሬ እንዳይታይ በሰቀቀን ወዲያ ወዲህ እላለሁ። እቀመጥና እንደገና እንዲህ መቀመጥ የለብኝም ብዬ እነሳለሁ። እንደገና እቀመጣለሁ….

የእሳቸው ግርማ ሞገስ ደግሞ እንዲሁ ብርክ ያስይዛል።

ብቻ የእምነት አባቶች መሀል በመሆኔ እምነቱ የማይፈቅደውን ሁኜ ላለመታየት ተጨነቅሁ።

ይህንን የውስጤን ገልጠው ያዩት ሀጂ ጠሩኝ። ፈገግ ብለውና ቀስስ ባለድምጽ

“እዚህ ያሉ ሁሉም አባቶችሽ ናቸው- የለበስሽውም ሁሉም አክብሮትሽን ያሳያል። ልጃቸ‍እን ስለመጣሽ ደስ ብሎናል፤ ሳትጨናነቂ ያሰብሸውን ጀምሪ” አሉኝ።

የእኔ አባት! ያ የጠፋው በራስ መተማመኔ ወደ ቦታው ሲመለስ ይታወቀኛል። ነጻነቴን ሳገኝ በቃ…እንዴት አይነት ፕሮግራም ሠራን መሰላችሁ።

ደግሞ ሌላ ቀን እንደገና ሌላ ቀን አገኘኋቸው። እንደሚዲያ ሰው እድለኛ የለም እኮ።

ገና ሳገኛቸው ያ የተጨነቀን የሚያረጋጋ ፈገግታቸው ይቀበለናል። ብዙ የሚናገሩ ባይሆንም ከቀረጻ በፊትና በኋላ ድንገት በመጣ ሃሳብ የመከሩን ብዙ ነው። አንዳንድ ሰዎች አሉ የእናንተ ሃይማኖት አባት ባይሆኑም የራሳችሁ እየመሰሏችሁ ማግኘት ማማከር በእሳቸው መገሰፅ የምትመኟቸው። ሀጂ ሙፍቲ እንዲያ ነበሩ።

ሰውነት በእግሩ ቁሞ ሲሄድ ለማየት ታድለናል። ለበጎነት ሃይማኖት ድንበር የሚከልል ሳይሆን አፍርሶ የሚያገናኝ፣ ልዩነት የምንሰብክበት ሳይሆን ሰው መሆንን የምናስተምርበት መሆኑን አሳይተዋል።

በ2017 ዓም እንግዳዬ ለማድረግ ብዙ ሞክሬ ነበር እየደከማቸው ነው በሚል ዙሪያ ያሉሰዎች አላገናኙኝም። ግን ምጠይቃቸው ብዙ ነበረኝ። ነበር!

ተቀዳሚ ሀጂ ሙፍቲ ስለመከሩኝ እና ስላስተማሩኝ ነገር ሁሉ አመሰግንዎታለሁ።

ዛሬ ብዙ ጽፌ ልመሰክርልዎት ብመኝም ቃላቶች ደከሙብኝና ተውሁት።

ሀገር ጥቁር ለብሳ ታልቅስ- የጎደለባትን ያጣችውን የምታውቅ እሷ።

አባቴ ፈጣሪ ነፍስዎን በሰላም ያሳርፍልን።

ከመስክረም ጌታቸው

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ

የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ሥርዓተ ቀብር ተፈጽሟል፡፡ በሥርዓተ...

የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ አስክሬን ሽኝት በሚሊንዬም አዳራሽ ተካሂዷል

የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ታየ አጽቀስላሴ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት...

ሸህ ዑመር ገነቴ!!!

እንዲህ ወደ ደገር…እንዲህ ወደ ገታ…ደግሞም ወደ ዳና፤ጫሌ ገንደጎራ፤የተሰየማችሁ፤ሰው መሆን…..ሰው...