የጤና ባለሙያዎች እና ለምሬት የዳረጋቸው ኑሯቸው
ባለፉት ሳምንታት የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ከደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጋር የተያያዘ ለዓመታት የቆየ ጥያቄዎችን ለመንግሥት አቅርበዋል።
ጥያቄያችን መልስ ካላገኘ የሥራ ማቆም አድማ እንመታለን ያሉት ባለሙያዎቹ ወርሃዊ ደሞዛቸው በአገሪቱ ካለው የኑሮ ውድነት እና ከሥራ ፀባያቸው አንፃር ለመኖር ፈተኝ እንደሆነባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ለመሆኑ የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ምን ያህል ይከፈላቸዋል? ሕይወትንስ እንዴት እየገፉት ነው? ቤተሰባቸውን ለመመገብ ምን ያህል ይታገላሉ?
ለንጽጽር ይሆን ዘንድ የጎረቤት አገር ኬንያን የጤና ባለሙያዎች ወርሃዊ ደሞዝ እናንሳ። በኬንያ አንድ ጀማሪ ጠቅላላ ሐኪም በወር ከ1,500 ዶላር በላይ (190 ሺህ ብር በላይ) የሚከፈላቸው ቢሆንም አሁንም መንግሥታቸው በሚገኙት ገቢ ላይ ማሻሻያ እንዲያደርግ እየጠየቁ ነው።
የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች “የዳቦ ጥያቄ” ሲሉ የሰየሙት ሰሞነኛ ጥያቄ፤ ከባዱን የጤና አገልግሎት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እየሰጡ ቢያንስ ከረሃብ እና ከጭንቀት እንዲወጡ የሚወተውት ነው።
ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ እየናረ የመጣው የኑሩ ውድነት የሕክምና ባለሙያዎቹ ሕይወት አዳጋች እንዳደረገባቸው ሁሉም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ እየተናገሩ ነው።
በተለያዩ የሕክምና ዘርፎች ላይ ተሰማርተው አገራቸውን እና ሕዝባቸውን እያገለገሉ ከሚገኙት ሐኪሞች መካከል የተወሰኑት የሁላችንም ታሪክ ነው የሚሉትን ፈታኝ ሁኔታ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከእነዚህ የሕክምና ባለሙያዎች የሰቆቃ ድምፆች መካከል የጥቂቶቹን እነሆ. . .
“ቁርስ መዝለል ከጀመርኩ አንድ ዓመት ሆኖኛል”
ስፔሻሊስት ሐኪም ነኝ። 26 ዓመት በትምህርት ላይ አሳልፊያለሁ። ደሞዜ 35 በመቶ ታክስ ተቆርጦ እጄ ላይ 8 ሺህ ብር ገደማ ይደርሰኛል። በዚህም ምክንያት መኖሬ ጥያቄ ውስጥ ከወደቀ ቆይቷል።
ባለትዳር እና አንድ ልጅ አለኝ። የቤት ኪራይ ከደሞዜ በእጥፍ 16 ሺህ ብር ነው የምከፍለው። ሳይከፈለኝ እየሠራሁ ነው ብል ይሻላል። ኑሮ ሙሉ ለሙሉ አልቀመስ ብሏል።
ባለቤቴ ጥሩ ሥራ ስላላት በጀኝ እንጂ፤ ምኑን ከምኑ አደርገው ነበር? የጋራ የባንክ አካውን አለን። የእኔን ደሞዝ ለአንዱ መሠረታዊ ወጪ አድርገን የእሷን እጋራለሁ።
አብዛኛውን ወጪያችንን ባለቤቴ ትሸፍናለች። መሠረታዊ ወጪዎችን የሆኑትን ልጅ ማስተረማር፣ ማልበስ . . . ባለቤቴ ናት የምትሸፍነው።
በግልፅ ለመናገር ቁርስ መዝለል ከጀመርኩ አንድ ዓመት ሆኖኛል። ራሴን ለማሳመን ፆም መንፈሳዊ ነው እላለሁ። በቀን ሁለቴ ነው የምመገበው። ብዙ ማስተካከያዎችን ማድረግ ግድ ብሎኛል።
ሕይወቴን በተአምር ነው የምኖረው። እንዴት እየኖርኩ እንደሆነ ማሰብ አልፈልግም። ሳስበው በጣም ያመኛል።
አእምሯችን ደኅንነት ይፈልጋል። ሰላም ይፈልጋል። ነፃነት ይፈልጋል። ስለ ምግብ ማሰብ የለብንም። ግን ይሄ መደበኛ ሕይወቴ ሆኗል። ለመኖር እየሞከርን ነው ብል ይቀላል።
ይህ የእኔ ብቻ ሕይወት ብቻ አይደለም። ሁላችንም የሕክምና ባለሙያዎች በአንድ ጀልባ ውስጥ ነን።
ክፍለ አገር ነው የምሠራው። ባለፈው ዓመት ቡና አምስት ብር እንጠጣ ነበር። አሁን 15 ብር ነው። ቡና እንኳ በሦስት እጥፍ አድጓል። የእኛ ደሞዝስ?
በዚህ ዓመት የኑሮ መናሩ ታሳቢ ተደርጎ የደሞዝ ጭማሪ ተደርጎልናል። 600 ብር ነው የተጨመረልኝ።
ሌላ አገር ሐኪም ምን ያህል ይከፈለዋል? እዚሁ አገራችን ውስጥ ባለው ነባራዊ ሁኔታ መኖር የሚቻል አይደለም። ከአቅም በላይ የሆነ እሮሮ እና ስቃይ ውስጥ ነን። እናም የዳቦ ጥያቄ እንድናነሳ አድርጎናል።
ይህን ጥያቄ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስተኛ ጊዜ እየጠየቅን ነው። ውሎ ያደረ፤ ሞልቶ እየፈሰሰ ያለ ጭንቅ ነው። ወደ ውስጥ አልቅሰን፤ አልቅሰን ሲያቅተን የወጣ ብሶት ነው።
ሐኪም ለመሆን የወሰንኩባትን ቀን ባልረግምም ትምህርትን የሙጥኝ በማለቴ ግን አዝናለሁ። ያን ሁሉ ጊዜ እና ኃይል ማውጣቴ የእኔ ስህተት ነው። ብልሃታዊ ውሳኔ አይመስለኝም።
ወደ ሌላ አገር ሄደው እጃቸውን ተስመው የሚሰሩ ጓደኞች አሉኝ። አገሬን አገሬን የምል ግትር ነኝ። እኔ እዚህ ለመድረስ ኢንቨስት ተደርጎብኛል፤ አስተማሪዎቼ ለፍተዋል እያልኩ ወደ ሌላ አገር መሄድ አልፈለኩም። አሁን ግን መቶ በመቶ ስህተት እንደሆነ ተረድቻለሁ። ይህ አስተሳሰቤ ሙሉ ለሙሉ አሁን ተቀይሯል።
ጠቅላላ ሐኪም 80 ሆነን ነው የተመረቅነው። ከ40 በላይ የሚሆኑን አሁን ከአገር ወጥተዋል። ከቀረነው ስፔሻሊስት እና ሰብ ስፔሻሊስት ሐኪሞች ውስጥ ከ15 በላይ የሚሆኑት በጎረቤት አገራት ተቀጥረዋል።
ሀሳቤ አገልግዬ እገለገላለሁ ነበር። አሁን ግን እውነታው ገብቶኛል። ግን እንደረፈደብኝ ይሰማኛል።
እንኳን ትዳር መመስረት ጫማ መቀየር አልቻልኩም’
በአንድ የመንግሥት ሆስፒታል ፋርማሲስት ነኝ። ደሞዜ ተቆራትጦ 7 ሺህ ብር በወር ይደርሰኛል።
በዚህ ደሞዝ እንኳን ትዳር መመሥረት ጫማ መቀየር እንኳን አልችልም።
የደሞዜን 70 በመቶ ለቤት ኪራይ አውላለሁ። 5 ሺህ ብር ቤት ኪራይ ከፍዬ እጄ ላይ የሚቀረው 2 ሺህ ብር ነው። ዘይት ብቻ ገዝቼ ለስኳር ሊተርፈኝ ይችላል። በቃ ደሞዜ አለቀ።
ትራንስፖርት አለ፤ ምግብ አለ፤ ልብስ መቀየር ሊያስፈልግ ይችላል፤ ማኅበራዊ ሕይወት ሊኖር ይችላል። እነዚህ ወጪዎችን በትርፍ ሰዓት ክፍያ (ዲዩቲ) ለመሸፈን ነው የምሞክረው።
ትዳር ለመመሥረት ከእጮኛዬ ጋር ቀን ቆርጠን ነበር። ግን በገንዘብ ምክንያት ተለያን። ቤተሰቤም ሥራ ከያዝኩ በኋላ እንደማልደውልላቸው፤ እንደተውኳቸው ነው የሚያስቡት።
ከቤተሰቤ ጋር አልገናኝም። ከማኅበራዊ ሕይወትም ተገድበን ነው ያለነው። ከሁሉም ሕይወት ታቅቤ ብቻዬን ነው እየኖርኩ ያለሁት። እንዲህ ሆነንም እየተራብን ነው ያለነው።
በአጭሩ ጭንቅንቅ ባለ ሁኔታ ውስጥ ነው እየኖርኩ ያለሁት። ሳት ብሎኝ የተለየ ወጪ ካወጣሁ ሙሉ ሕይወቴ ነው የሚናጋው።
አንዳንዴ በቀን አንድ ጊዜ ወይም ሁለት ጊዜ ነው ምግብ የምበላው፤ ቀለል ያለ ብስኩት በልቼም ልውል እችላለሁ።
መደበኛ የሆነውን የአንድ ቀን ሕይቴን ልናገር።
አካላዊ እና አእምሯዊ ድካም እንዳይሰማኝ ጠዋት ቡና እጠጣለሁ፤ የምግብ ፍላጎቴም ይዘጋል። ጨጓራዬ እንዳይጎዳ ደግሞ ውሃ እጠጣለሁ። ምሳዬን ወደ 8፡00፤ 9፡00 ሰዓት ገፋ አድጌ እበላለሁ። ይህ ለእራት ያደርሰኛል።
ምግብ ከቤት ልቋጥር ብል እስከ 48 ሰዓት ሥራ ላይ ልሆን ስለምችል አያደርሰኝም፤ ይበላሻልም። ይህ ነው ሕይወቴ በቃ።
‘ልጄ ከምግብ ጋር በተያያዘ ከሦስት፤ ከአራት ጊዜ በላይ ታሟል’
በአንድ ጤና ጣቢያ አዋላጅ ነኝ። አሁን እንኳን [ጠዋት 03፡00 ሰዓት አካባቢ] ሦስት እናቶችን አዋልጄ ነው።
ከደሞዜ 35 በመቶ ታክስ ተቆርጦብኝ እጄ ላይ 7300 ብር ገደማ ይደርሰኛል። ከዚችም ደሞዝ ላይ ለግዴታ መዋጮዎች ይቆረጣል። በትርፍ ሰዓት ክፍያ በአማካኝ 6 ሺህ ብር አገኛለሁ።
ባለትዳር እና ሁለት ልጆች አሉኝ። ለቤት ኪራይ 9500 እከፍላለሁ። የሚተርፈኝ 4 ሺህ ብር ነው። ለትራንስፖርት 2 ሺህ ብር አወጣለሁ። በቀሪው ነው እንግዲህ ቤተሰብ የምመራው።
እኛ ቤት ጤፍ አስፈጭተን፤ የወር አስቤዛ አሟልተን አናውቅም። ያለፈው ፋሲካ ጎረቤት ሲበላ፤ ሲጠጣ ባለቤቴ ልጆቿን ይዛ ተኝታ ነው የዋለችው።
ከሌላው ጊዜ በተለየ በጣም ያዘንኩበትን ጊዜ ልናገር። ለአራስ እናት ምን ዓይነት ምግብ እንደሚያስፈልግ ለማንም የተደበቀ አይደለም። የተመጣጠነ ምግብ መመገብ አለባቸው። እንደ ባለሙያም ይህን ነው የምመክረው። ለእኔ ባለቤት ግን ይህን ማድረግ አልቻልኩም። አያሳዝንም?
አራስ ሆና በግ ማረድ፤ ወተት ማቅረብ፤ ብዙ ነገር ማሟላት ነበረብኝ። ግን ከየት መጥትቶ? ለአራሷ ባለቤቴ ሽሮ ነበር ሳቀርብ የነበረው። እሱንም በመከራ ነው። የእኔ ኑሮ ይሄው ነው።
ባለቤቴ ሥራ ስትጀምር ለልጄ ወተት መግዛት ነበረብኝ። ግን አልቻልኩም። አጥሚት ነው እየጠጣ ያለው። ከሦስት፤ ከአራት ጊዜ በላይ ተቅማጥ (ዲያሪያ) ታሟል። ምን ላድርግ? ነገሩ የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው ዓይነት ነው።
በቅርቡ አገር ቤት ቤተሰብ ሞተብኝ። ቀብር መሄድ አልቻልኩም። ትራንስፖርት እንዴት እችላለሁ? በምን አቅሜ? በቃ እዚሁ አልቅሼ ነው ዝም ያልኩት።
ሕይወታችን አደጋ ላይ ነው ያለው። በጣም ተቸግረናል። የጤና ባለሙያ እኮ ሻይ በዳቦ ነው የሚበላው። ያለንበት ሁኔታ የሞት እና የሕይወት ጉዳይ ነው። መንግሥት ይድረስልን።
የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ እንደ ሌላው የሚታይ አይደለም። ለመማር ረጅም ዓመታትን ከማሳለፍ ባለፈ፤ ለቀናት ያለ እረፍት ሥራ ላይ ነን፤ ጫና አለብን። ሌላ ሥራ ለመሥራት ፋታ የለንም፤ ሥራ ለመቀየርም አማራጮች የተገደቡ ናቸው።
ለዚህ የዳቦ ጥያቄ ግን ምላሹ እስራት፣ ድብደባ እና ዛቻ ሆነ። እኔ የምሠራበት ተቋም በደኅንነት ተከቦ ነው ያለው። በአለቆቻችን በኩል ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ እና ማስፈራሪያ እየተሰጠን ነው። ‘እየለቀምን እናባርራችኋለን’ ተብለናል። ‘ጠያቂ እንኳ አታገኙም’ እያሉን ነው።
የጤና ባለሙያዎች ከክፍያ ጋር በተያያዘ ከዘርፉ እየወጡ እና እየተሰደዱ ነው። በተለይም ወደ ሌሎች አፍሪካ አገራት ፈልሰው የሚሠሩ የጤና ባለሙያዎች የተሻለ ክፍያ እያገኙ ስለመሆኑ ይነገራል።
ባለፉት ሳምንታት የተቀሰቀሰው የጤና ባለሙያዎች ንቅናቄ “ዘመኑን የዋጀ አሠራር” እንዲፈጠር እና የባለሙያዎቹን የኑሮ ጫና የሚያቃልል ማስተካከያ እንዲደረግ የሚጠይቅ ነው።
ባለሙያዎቹ ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ ካላገኙ በከፊል፤ ከግንቦት 10/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሙ “ሙሉ ለሙሉ” የሥራ ማቆም አድማ እንደሚመቱ አስታውቀዋል።
እስካሁን ግን መንግሥት ምላሽ እንዳልተሰጣቸው አስተባባሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።