ፕሌቶ
ከሁሉ በፊት ራስህን እወቅላይላ ሠላሳ ዓመቷ ነው። የአብራኳ ፍሬ የሆኑ ሦስት ልጆች አሏት። ሕይወት ለላይላ ጣእም አልባ ሆናባታለች። ጀምበር ወጥታ እስከትገባ ድረስ መተንፈሻ የላትም፤ባለቤቷ በጋራ በከፈቱት ጋራዥ ውስጥ ዘወትር ተፍ ተፍ ሲል እርሷ ደግሞ የቤት ጣጣውን ትሸፍናለች። ምሽት ምሽት ደግሞ የገራዡን ሂሳብ ኦዲት ታደርጋለች።ባላት የተጣበበ ጊዜ ውስጥ በእድሜ የገፉ ወላጆቿን ለመንከባከብ ወደ መኖሪያ ቤታቸው በዕየለቱ መለስ ቀለስ ትላለች። ባተሌነቷ በዚህ አያበቃም። በአንድ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ የዲሲፒሊን ኮሚቴ በመሆን ነጻ አገልግሎት ትሰጣለች።
ላይላ ይህንን ሁሉ ሃላፊነት በምትወጣ ጊዜ ከሰዎች የምትጠብቀው ፍጹም ይሁንታን ነው። ሰዎች ስህተት አልባ ሥራ እንደምትሠራ እንዲያውቁላት በእጅጉ ትሻላች። ይህ በሰዎች ዘንድ ስለእርሷ ያላቸው እምነት ከተጓደለ ግን የላይላ ስሜት በቀላሉ ይጎዳል።
አንድ ቀን እንደተለመደው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለመስጠት ወደ ትምህርት ቤቱ ጎራ አለች። ያ ቀን መጥፎ ዱብዳ ጣለባት። ድንገት ከአንዲት ወላጅ ጋር እዚህ ግባ በማይባል ጉዳይ እሰጣ ገባ ውስጥ ገባች። ሴትየዋ የላይላን ስህተት መሥራት እየደጋገመች ትናገራታለች። ይህ ደግሞ ለላይላ ከባድ ዱላ ነበር። እርሷ በሌላ ሰው መተቸት በፍጹም ጤና አይሰጣታም። ይረብሻታል፤ ስሜትዋ ቶሎ ይጎዳል። እንደመተቸት የምትፈራው አውሬ የለም። በዚህም ምክንያት ሌሊቱን በሙሉ ስታነባ አደረች። ይህ የስሜት መጎሳቆል ነው ወደ እኔ የጤናና የስነልቦና ማዕከል ብቅ እንድትል ያስገደዳት ፡“የበጎ ፍቃድ እሠራበታለሁ ባልኩበት ት/ቤት ውስጥ መልካም ባደረኩ እንዴት እወገዛለሁ? የጽድቅ ሥራ እስራለሁ ብዬ በዚህ መልኩ መተቸቴ በጣም እጅግ በጣም ተሰምቶኛል፤ ድሮም ይሄ ሕዝብ ወርቅ ይነጠፍልህ ሲባል ፋንድያ….” እያለች ቢሮዬ ውስጥ እንባዋን ዘራችው።
እንደተረዳኹት ከኾነ ላይላ ፍጹምነትን በራሷ ላይ ትጠብቃች። ካላት የሳሳ በራስ መተማመን እና ስር የሰደደ የጸጸት ስሜት የተነሳ ሰዎችን ማባበል፣ በምላሹም ፍጹም እንደኾነች እንዲነገራት ትሻለች።ይህን የምታደርገው ኋላ ላይ ሊመጣባት ከሚችለው ደስ የማይል የትችት ስሜት ለመሸሸግ ነው። ጥሎባት ሁሉም ሰዎች የፍቅር ሰው እንደሆነች አድርገው እንዲስሏት ትፈልጋለች። የኋላ ኋላ እንደተረዳኹት ሰዎች ስለርሷ ስለሚያስቡት ነገር አብዝታ መጨነቋ ሳይጎዳት አልቀረም።እዚህ ጋር የምንረዳው አንድ ትልቅ ነጥብ አለ። የላይላ ሰዎችን የማባበልና ስለርሷ በጎ አመለካከት እንድይዙ አጥብቆ የመሻት ባህሪ በ “ሲቢቲ” አጠራር አስኳል እምነት በሚል ይታወቃል። የላይላ አስኳል እምነት ሰዎችን ማባባልና ሁልጊዜም ከኔ ጎን እንዲቆሙ ማድረግ ካልቻልኩ ዋጋ አይኖረኝም የሚል ነው። ነገር ግን ይህንን አስኳል እምነት መገላለጥ እንድትችል ላይላን ብንረዳት ቀሪው ሥራ እጅግ በጣም ቀላል ይሆናል። በእርግጥም ለይላ ለራሷ የሰጠችውን ያልተገባ ግምት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መስበር ከቻለች እንደማንኛውም ሰው መሆን ትጀምራለች። በዚህም ለይላ ከራሷ ጋር ትታረቃለች። ይህም ሕይወቷ በሁሉም መስመር እንዲቃና ያደርግላታል።
አንዳንድ ሰዎች ሆደ ቡቡ ናቸው። ለሠው ይራራሉ፤ ሠዎችን ማገዝ ያስደስታቸዋል። ያንን የሚያደርጉት ግን እንደ አለመታደል ኾኖ ሰዎች ስለነርሱ መልካም ነገር እንዲያስቡ ለማድረግ ብቻ ይኾናል። ይህ ቀስበቀስ ስለራሳቸው ፍጹምነትና እንከን የለሽነት አብዝተው እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል። ስለራሳቸው የገነቡት ምስለ-ራስ ድንገት ሲነካ አእምሯቸውም አብሮ ይነካል። በሁለት እግር መቆም ሁሉ ያቅታቸዋል። ሕይወታቸው እንደ የእምቧይ ካብ ፍጹም ይናጋል። ይህን አስኳል እምነታቸውን በማከም ወደ ጤናቸው መመለስ ግን ከባድ አይደለም።
እስቲ ራሰህን ቆም ብለህ ተመልከት
አስተሳሰብህ እና ተግባርህ ምን ያህል እንደሚታረቅ ለመፈተሸ ሞክር። ይህ ጉዳይ ምናልባት ብዙም ተነሳሽነትን ላይፈጥርብህ ይችል ይሆናል። ነገር ግን ከዚህ መጽሐፍም ሆነ ከ “ሲቢቲ” ሕክምና ለማትረፍ የግድ ራስህን መገምገም ይኖርብኻል። ቀጥለው በዚህ ምዕራፍ የሚዘረዘሩትን ምልከታዎች ገቢራዊ ማድረግም ያንተ ፋንታ ነው።እስኪ አሁን ደግሞ እስካሁን ስንንደረደርበት የነበረውን ሀሳብ በተግባር አንድ ብለን እጀምር።
የሲቢቲ ምልከታ
ሲቢቲ አስተሳሰብህ እና ባህሪህ ከአንድ ወንዝ ነው የሚቀዱት ይልኻል።የምታሳየው ባህሪ የሚጸነሰው በአስተሳሰብህ ውስጥ ነው። አስተሳሰብህ ደግሞ በባህሪህ ይገለጣል። ይህ ነጥብ እጅግ ቁልፍ ነጥብ ስለኾነ ልብ ብለህ ተከታተል። ለመድገም ያህል ባሕሪህ የሚጸነሰው ከአስተሳሰብህ ነው። ባህሪህ የአስተሳሰብ ሞተርህን ይቀሰቅሰዋል። ወይም ደግሞ ሁሉቱ እርስ በእርስ አንዱ አንዱን እየቆሰቆሰ ያለማቋረጥ የሚሸከረከሩ መዘውሮች አድርገህ አስባቸው። ለምሳሌ ሕዝብ ፊት ቆሞ ማውራት ትፈራለህ። ያልብሀል። ለምን አላበኝ ብለህ ራስህን ጠይቅ እስኪ። ያላበህ አዳራሹ ስለታመቀ ይመስልኻል? አይደለም። ምክንያቱም የአዳራሹ መስኮቶች በሙሉ ቢከፈቱና አንድ ሺ የንፋስ ማራገቢያ አዳራሹ ውስጥ ቢሽከረከር ያንተን ፍርሃትና ላብ አያጠፉትም። ያላበህ ሰዎች አንተ ላይ በሕብረት ስላፈጠጡ ይመስልኻል? አይደለም። የሰዎች ዐይን ምንም ቢያፈጥ አንተ ላይ ትኩሳት የመልቀቅ ጉልበት አይኖረውም። እውነት ለመናገር አንተን ያላበህ አስተሳሰብህ ስላላበው ነው።
በሌላ አነጋገር አስተሳሰብህ (ሕዝብ ፊት ቆሞ የመናገር ግንዛቤህ) የፍርሃት ሞተርህን ተረክ አድርጎ ስላስነሳው ሰውነትህ ሁሉ መንዘፍዘፍ ጀመረ። እንደምታውቀው ሁሉም የሰውነት ክፍልህ ትዕዛዝ የሚቀበለው ከአእምሮህ ነው። ይህም ማለት የፍርሃት አስተሳሰብ በአእምሮ ውስጥ ተጋግሮ ነበር ማለት ነው። ይህ በአእምሮህ የተጋገረ የፍርሃት አስተሳሰብ ንግግሩን ለማድረግ ገና ከመድረክ ላይ መውጣት ስትጀምር እጅህ እንዲንቀጠቀጥ እና ፊትህ በላብ እንዲጠመቅ ምክንያት ሆኗል። ስለዚህ እመነኝ ክምር ሶፍት ወረቀትና ተጣጣፊ ፎጣ ግንባርህ ላይ ሽፍ ያለ ላብህን ይቀንሱት ይኾናል እንጂ ዘላቂ መፍትሄ አይሰጡኽም። ዘላቂ መፍትሄ ያለው ከአእምሮ ላይ ነው። “ሲቢቲ” ለዚህ መፍትሄ ይጠቁምኻል።
እንዴት ነው ዓለምን የምታያት?
ራስህን እና አካባቢህን የምትመለከትበትን መነጽር ዳግም እንድትፈትሽ የ“ሲቢቲ” ሕክምና ይመክርኻል። የቆምክበትን የአመለካከት ንጣፍ እንድትመረምር ፈተናውን በሰፊው ዘርግቶ ያቀርብልኻል። ልክ ላይላ ራሷንና ሰዎችን የምትመለከትበትን መነጽር የተንሸዋረረ እንደነበረና መቀየር እንደነበረባት ሁሉ አንተም አካባቢህንና ዓለምን የምታይበትን መነጽር ድብን አድርገህ መጥረግ ይኖርብኻል። ምክንቱም ሁሉም ስብእናችን የሚወለደው ሰለራሳችን እና ሰለ ዓለም በምንሰጠው አመለካከት ምክንያት ስለኾነ ነው።
ስለምታስበው ሀሳብ
ማሰብ በየዕለቱ በአእምሮህ የሚመላለሱ ሀሳቦችን የምትመለከትበት ማጉያ መነጽርን ሳይንሱ ሜታ ኮግኒሽን ብሎ ይጠረዋል።ይህንን ማጉያ መነጽር ውስጥህን ለመመልከት ስትጠቀምበት ትንሽ ደምበርበር የሚል ስሜት ሁለመናህን ይወረዋል። በምታስባቸው ሀሳቦች መናኛነት ክፉኛ ትሸማቀቃለህ።ነገር ግን ገበናህን የማየት ልምምድን በቀጠልክ ቁጥር ግርምታው እየቀነሰልህ ትሄዳለህ።እስቲ የቢኒያምን ገበና እንደራስህ አድርገህ ተመልከት።ቢኒያም ሀገር ያወቀው ጎበዝ አናጢ ነው። እድሜው ሠላሳዎቹን ተሻግሯል። የቢኒ ተቀዳሚ ሥራ የደምበኞቹን ፍላጎት ማጥናት ነው። በጥናቱ መሠረት የደምበኞቹን ዐይን ሊይዝ የሚችል ሁነኛ ሥራን ለማበጃጀት የሚያሰፈልገውን እንጨት ይመርጣል። ሥራው ትንሽም ሆነ ትልቅ የሚከተለው መንገድ አንድ ዓይነት ነው።የቢኒ ችግር በሚሠራው ሥራ የልቡ አይደርስም። እያፈረሰ ይጠግናል።ይህ አለቅጥ እንከን አልባ ሥራን የመፈለግ አባዜ ከደምበኞቹ ጋር በየጊዜው ያጋጨዋል።
ለምን መሰለህ? በጊዜ ማግኘት የሚገባቸውን አገልግሎት ባለማግኘታቸው የተነሳ ደምበኞቹ ለዳግም ትእዛዝ የቢኒን ደጃፍ ላለምርገጥ ይምላሉ። አንድም ሥራ በቀጠሮ አድርሶ አያውቅም። በቅርቡ የአንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወንበሮችን ሰርቶ ለማድረስ ተዋውሎ እንኳ እርሱ ስራውን የጨረሰው ህዳር ወር ላይ ነበር። ትምህርት ከተጀመረ ከሁለት ወራት በኋላ። ቢኒ ሰነፍ ኾኖ አይደለም የሚዘገየው። ፍጹም የኾነ ሥራ፣ እንከን አልባ ሥራ ለመሥራት ካለው ጽኑ ፍላጎት እንጂ። በግልፅ እንደምንረዳው ቢንያም በተጣባው አጓጉል አመለከከት የተነሳ ሥራው ተጎድቷል።ደምበኞቹን አጥቷል። “ሲቢቲ” ይህን መሰሉ የቤኒያምን የተጋነነ አመለከከት የእንከን-የለሽነት ሀሳብ ብሎ ይሰይመዋል።
እኔ ማለት የማስበው ነገር ነኝ
“ሲቢቲ” ዓለምን ጉራማይሌ በሆነ መልክ የምንመለከትበት መንገድ ያሳየናል። ቢኒን ፍጹም እንከን የለሽ በሆነ መልኩ ሥራውን ለማቃናት ይታትራል።ትችትን በጽኑ ይጠየፋል።ይህም ሥራውን የሚተረጉምበት ስልት ነው። ቢኒያም ያልተረዳው ነገር ቢኖር ጊዜ ለደንበኞቹ እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ መኾኑን ነው። ትችትን በመስጋትና ፍጹም ለመሆን በመታተር ውስጥ የጊዜን አስፈላጊነት ዘንግቶታል።የ “ ሲቢቲ” ሕክምና በቅድሚያ ዐይንህን የሚገልጥልህ ዓለምን የምትተረጉምበትን አስተሳሰብ በማሳየት ነው። ከዚህ ለጥቆ የሚመጣው ሥራ እጅግ በጣም ቀላል ይሆናል።ስለዚህ ከሁሉም ተቀዳሚ ሥራ የሀሳቦችን ዘረመል መለየት ነው። ላንተ አንድን ሥራ ባቀድከው መሠረት መከወን ማለት ምን ማለት ነው?
ሀሳብህን መረዳት
ብዙ የስነልቦና ባለሙያዎች እንደሚስማሙበት ከሆነ ዓለምን የምንመለከትበት መነጽር የተበጃጀው ባለን የኋላ ታሪክ፣ ልምድ እና እምነት ነው።ሁላችንም የራሳችን ትንንሽ ዓለም ባለቤቶች ነን። “ሲቢቲ” እዚህ ጋር ብቅ ይላል። በ “ሲቢቲ” ሕክምና መሠረት ማንኛውም ሀሳብ የሚታሰብበት ስድስት መሠረታዊ መርህዎች ይኖራሉ።
1. ሁላችንም ዓለምን የምንተረጉምበት መነጽር ይለያያል፤
2. አስተሳሰብህን በመለወጥ ባህሪህን መለወጥ ይቻላል፤ ባህሪህን በመለወጥ ስሜትህን መቀየር ይቻላል፤
3. ሁላችንም በየጓዳችን ይነስም ይብዛ ችግሮች አሉብን፤
4. ችግሮችህን ለመፍታት የአሁን ቅጽበትን ብቻ መጠቀም ያሻል፤
5. ራስህን ሁለንተናዊ በሆነ ገጽታ መመልከት ጠቃሚ ነው፤
6. ውጤቱን ሳይሳዊ በሆነ መንገድ መተንተን ያስፈልጋል፤
1. ሁላችንም ዓለምን የምንተረጉምበት መነጽር ይለያያል
እምነታችን ፣አስተሳሰባችን እና ለዓለም የምንሰጠው ትርጉም አጠቃላይ ኮግኒሽን በሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ይገለጻል። በመኾኑም ከነገሮች ጋር ፊት ለፊት ስንላትም የምናሳየው ስሜት እና ምላሽ እንደየግለሰቡ ኮግኒሽን ይለያያል።
• የቡና ቡድን ደጋፊ ከሆንክ ምናልባት ስለቡድንህ አሸናፊነት ምልክት እያሳየህ ሊመስልህ ይችላል።ወይም ደግሞ የባላጋራህ የጊዮርጊዝ ቡድን ዸጋፊ ሆኖ እየተሳለቀብህ ይመስልሃል።
• የቆየ ወዳጀህ መጠጥ ቀማምሶ ሰላምታ ሊሰጥህ በስሜት እጁን እያወዛወዘ ሊመስልህም ይችላል፡
• ወይም ወዳጅህ ከአንተ ጋር ለመሄድ ፈልጎ እንድትቆየው ምልክት እያሳየህ ይመስልሃል።
• ወይም አንድ ግለሰብ “የሆነ መርዶ ሊያረዳን ፈልጎ ይኾን” ብለህ ታስባለህ።
ምላሽህ ምን ሊሆን ይችላል?
• አንተ መጀመርያውኑ በራስህ የምትብከነከንበት ሀሳብ ከነበረኸ ሰውዬውን በፍጠነት መሸሽ ነው የምትፈልገው፤
• ሰውዬውን እንደለየኸው እርግጠኛ ከሆንክ ፈጥንህ ሰላም ልትለው ወደ እርሱ ትንደረደራለህ፤
• ሰውዬው ለዱላ የሚጋበዝ ሰካራም እንደሆነ ካሰብክ ደግሞ ከፊቱ ዞር ልትል እርምጃህን ትጨምራለህ፤
• ሰላማዊ ሰው እንደሆነ ካሰብክ ምን እንደፈለገ ለማወቅ ትቀርበዋለህ፤
እነዚሁ ሁሉ ምላሾች ለአንዲት አጋጣሚ የምትፈበርካቸው ጉራማይሌ ትርጉሞች ናቸው።ይህ እውነታ ሁሉም ሰው ላይ የሚስተዋል ነው።አንድን አጋጣሚ በብዙ ዓይነት ወርድ እና ቁመት መመልከት የተለመደ ተግባር ነው። ለዚህም የመጣንበት የሕይወት ተሞክሮ፣ ልምድ ፣እምነት እና እውቀታችን ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
ምልከታ
ኮግኒሽን ወደ ስሜት ያነጉዳል
እጁን ሲያወዛውዝ የነበረውን ሰው የመዘንክበት አስተሳሰብ ኮግኒሽን ይባላል።እያንዳንዱ ኮግኒሽን በጀርባው ጉራማይሌ ምላሽን አዝሏል።ሰውዬውን የእኛ ቡድን ደጋፊ እንደሆነ ከቆጠርን ውስጣችን ሰላም ይሰማዋል።የተቃራኒ ቡድን እንደሆነ ስናውቅ ደግሞ በተቃራኒው የባላንጣነት ስሜት በውስጣችን ያቆጠቁጣል። መጠጥ ቢጤ የቀማመስ ፣ለጠብ የሚጋበዝ እና ሞገደኛ ሰው እንደሆነ ከቆጠርነው ደግሞ ፍርሃት በውስጣችን ይነግሳል።አልያም ሰውዬው ወዳጃችን እንደሆነ ከለየነው የደስታ ስሜት ውስጥ እንገባለን። በመሆኑም በሲቢቲ መሰረት ዓለምን እንደእየበኩላችን እንተረጉማለን ሲባል ሰዎች ለነገሮች ያላቸው ኮግኒሽን(አስተሳሰብ) ሲለወጥ የሚሰማቸው ስሜትም አብሮ ይለወጣል ማለት ነው።