የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያን ጨምሮ በ36 ሀገራት ላይ የጉዞ እገዳ የመጣል ዕቅድ አለው

Date:

የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ጅቡቲን ጨምሮ 36 ሀገራትን የጉዞ እገዳ ከተጣለባቸው ዝርዝር ውስጥ የማካተት ዕቅድ እንዳለው ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል። እገዳ ይጣልባቸዋል ከተባሉት ውስጥ 25 የአፍሪካ ሀገራት ይገኙበታል።

ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ ኤርትራን ጨምሮ የ12 ሀገራት ዜጎች አሜሪካ ከመግባት ታግደዋል።
በዶናልድ ትራምፕ የሚመራው የዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ኢትዮጵያን ጨምሮ 36 ሀገራትን የጉዞ ዕቀባ ከጣለባቸው ጎራ የማካተት ዕቅድ አለው ተባለ።

የአሜሪካው ዋሽንግተን ፖስት እንደዘገበው በዩናይትድ ስቴትስ የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የውስጥ ማስታወሻ የጉዞ ዕቀባ ይጣልባቸዋል ተብለው ከሰፈሩ መካከል 25 የአፍሪካ ሀገራት ይገኙበታል።

ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ጅቡቲ፣ ናይጄሪያ እና ደቡብ ሱዳን በዝርዝሩ ውስጥ ከተካተቱ መካከል ናቸው። ውሳኔው ተግባራዊ ከሆነ ዜጎቻቸው ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ በፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ዕቀባ የተጣለባቸውን ሀገራት ቁጥር ወደ 48 ያደርሰዋል።

ባለፈው ሰኞ ገቢራዊ በሆነው የትራምፕ አስተዳደር ውሳኔ ኤርትራን ጨምሮ የ12 ሀገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚከለክል ገደብ ተጥሎባቸዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የተፈረመው እና ዋሽንግተን ፖስት ተመለከትኩት ያለው የውስጥ ማስታወሻ የጉዞ ዕቀባ ሊደረግባቸው ይችላል በተባሉት 36 ሀገራት ለሚሰሩ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች የተሠራጨ ነው።

በማስታወሻው ኢትዮጵያን ጨምሮ 36ቱ ሀገራት የቪዛ ዕቀባ እንዳይጣልባቸው በአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የተቀመጡ ቅድመ-ሁኔታዎችን በ60 ቀናት ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው መገለጹን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል። ሀገራቱ ቅድመ ሁኔታዎቹን ካላሟሉ ሙሉ ወይም ከፊል የቪዛ ዕቀባ ይጠብቃቸዋል።

ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ በውስጥ ጉዳይ ወይም የውስጥ የመረጃ ልውውጥ ላይ አስተያየት እንደማይሰጡ ለዋሽንግተን ፖስት ምላሽ ሰጥተዋል።

ሀገራቱ የተቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎች ካላሟሉ በውስጥ ማስታወሻው የቀረበው የጉዞ ማዕቀብ መቼ በትክክል ተግባራዊ እንደሚሆን እንደማይታወቅ ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል።

የጉዞ ዕቀባ ይጣልባቸዋል ከተባሉት መካከል አንጎላ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ካሜሩን፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ጋና እና አይቮሪ ኮስት ይገኙበታል። ዝርዝሩ ከአፍሪካ በተጨማሪ የካሪቢያን፣ ማዕከላዊ እስያ እና የፓሲፊክ የደሴት ሀገራትን ጭምር የሚያካትት ነው።
DW Amharic

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ታላቅ አረጋዊ ፣ የበሳል አእምሮ ባለቤት፣ አገርን የሚወዱ…

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት...

የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ አስከሬን ሽኝት እየተደረገለት ነው

የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ አስከሬን ከመኖሪያ ቤታቸው...

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ የህይወት ታሪክ

ከአባታቸው አቶ ኢድሪስ ዘለቀ እና ከእናታቸው ወ/ሮ መነን ሽፋው፣...