በደቡብ ኢትዮጵያ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ፣ በሞያሌ ከተማ በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት ባለፈው ሳምንት ብቻ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች ድንበር አቋርጠው ወደ ኬንያ መሰደዳቸውን የአካባቢውን ባለሥልጣናት እማኝ በማድረግ የተባበሩት መንግሥታት ትናንት ረቡዕ አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኤጀንሲ በሁለቱ ክልሎች ኃይሎች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት ወደ ኬንያ የተሰደዱ ሰዎች ቁጥር ማክሰኞ ዕለት ከተመዘገበው 36 ሺህ ወደ 50 ሺህ በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡን አመልክቷል፡፡
በኬንያ የድርጅቱ ተወካይ ፋጢማ መሀመድ ኮል እንደተናገሩት “በአካባቢው ባለሥልጣናት መረጃ መሠረት እስካሁን እስከ 50 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ድንበር አቋርጠው ወደ ኬንያ ገብተዋል”። አሁንም አዳዲስ ተፈናቃዮች ድንበር አቋርጠው እየገቡ በመሆናቸው በቦታው ባለው ሁኔታ ምክንያት ይህ ቁጥር በፍጥነት ሊቀየር እንደሚችልም አስረድተዋል።
ይህ አለመረጋጋት የተቀሰቀሰው በሁለቱ ክልሎች በጋራ የምትተዳደረው የሞያሌ ከተማ ላይ ጥቅምት 10 ቀን የሶማሌ ክልል ሰንደቅ ዓላማ ከተሰቀለ በኋላ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ በተቀሰቀሰው ግጭት የሰዎች ህይወት ማለፉን ምንጮች ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎ፤ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ገልጸዋል።
ከተፈናቃዮቹ መካከል አብዛኞቹ ሴቶችና ሕፃናት መሆናቸውን የጠቆሙት ፋጢማ ሞሐመድ ኮል፤ “ጥቂቶቹ ከዘመዶቻቸውና ከሚያስተናግዷቸው ማህበረሰቦች ጋር የተጠለሉ ቢሆንም፣ ሌሎቹ ደግሞ እንደ ትምህርት ቤትና ቤተክርስቲያን ባሉ ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ ይገኛል”ብለዋል።
ኤጀንሲው ወደ አካባቢው የአደጋ ጊዜ ቡድን የላከ ሲሆን፣ ለተፈናቃዮች እርዳታ ለማቅረብ ከኬንያ መንግሥት እና እንደ ቀይ መስቀል ካሉ የሰብአዊ ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል።
