(የ‹‹ጀ.ጀኮን ኮንስትራክሽን›› መሥራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር)
ግዮን መጽሔት :- ከኢሉባቦር የገጠር መንደር እስከ አዲስ አበባ የንግድና የግንባታ ማዕከላት፤ ከሞያሌ የድንበር ንግድና የሕይወት ውጣ ውረዶች እስከ ማዕከላዊ እስር ቤት… ኢንጂ. ጀበል ጀማል በፈተናዎችና በተስፋ መቁረጥ መንገዶች ውስጥ አልፈው የዛሬውን ስኬታቸውን የገነቡበት የሕይወት ታሪክ እጅግ አስደናቂና ለብዙዎች ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። የ12ኛ ክፍል የማትሪክ ፈተናቸውን በእስር ቤት ውስጥ ተፈትነው ካለፉ በኋላ፣ በምሕንድስና ሙያ ተመርቀው ባለፉት 13 ዓመታት በኮንስትራክሽንና በሕንፃ ግንባታ ዘርፍ ስማቸውን በጉልህና በክብር መጻፍ ችለዋል።
ዛሬ ላይ በ‹‹ጀ.ጀኮን ኮንስትራክሽን›› (JJCON Construction) አሻራቸውን በከተማዋ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች ላይ ያሳረፉት ኢንጂ. ጀበል፤ የኢትዮጵያ ሪል እስቴት አልሚዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን የዘርፉን ዕድገት፣ ጥራትና ታማኝነት ለመገንባት በግንባር ቀደምትነት እየሠሩ ይገኛሉ።
ለመኾኑ በቅንነት፣ በሙያ ሥነ ምግባርና በጠንካራ የሥራ ባሕል የታነጸው የእነዚህ ረጅም ዓመታት ውጣ ውረድ ውጤት ምንድን ነው? ከኮንስትራክሽን ተቋራጭነት ወደ ሪል ስቴት አልሚነት የተደረገው ሽግግር በምን ዓይነት እይታ ላይ የተመሠረተ ነው? ኢንጂ. ጀበል ስለ ሀገር በቀል ዕውቀት፣ ስለ ቤተሰብ አስተዳደግና የቁጠባ ባሕል፣ ስለ ንግድ ሥነ ምግባር፣ እንዲሁም በፈተናዎች ውስጥ ስለመጽናትና ስለ ሀገር እድገት ያላቸው ጥልቅና ግልጽ ዕይታስ ምን ይመስላል? ከግዮን መጽሔት ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ጋር ያደረጉት ቆይታ እነኚህንና ተያያዥ ጥያቄዎችን በዝርዝር ይመልሳል፡፡ መልካም ንባብ!
ግዮን፡- በመጀመሪያ ለግዮን መጽሔት እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ በመሆንህ በአንባቢያን ስም ከልብ እናመሰግናለን! ለመሆኑ ኢንጂ. ጀበል ማን ነው? የትስ ነው የተወለድከው?
ጀበል፡- ጀበል ጀማል እባላለሁ፡፡ የተወለድኩት ኢሉባቦር ውስጥ ነው። ነገር ግን ገና በስድስት ዓመቴ ወደ ጅማ አጋሮ መጣሁ። ያደግኩት በአጋሮ 03 ቀበሌ፣ ‹‹ኩዬ›› በሚባለውና በቡና ምርቱ በሚታወቀው አካባቢ ነው። እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለውን የትምህርት ደረጃዬንም እዚያው ነው ያጠናቀቅኩት። በወቅቱ በአካባቢው የቡና ንግድ በሰፊው ይካሄድ ስለነበር፣ እኔም ቡና በፕላስቲክ እያሸግኩ መኪና ላይ እሸጥ ነበር። በሥራዬ በጣም ንቁና ፈጣን ከመሆኔ የተነሳ፣ በአካባቢያችን ሱቅ የነበረው አንድ ባለሀብት ‹‹ሰርቆ›› ወደ አዲስ አበባ ይዞኝ መጣ። ሰውየው ‹‹አልዩ›› የሚባል የስልጤ ማህበረሰብ ተወላጅ ሲሆን፣ አዲስ አበባ ላይ ሱቆች ስለነበሩት እንድሠራለት ፈልጎ ነበር።
አጋሮ እያለሁ ይህን ሰው የሚያውቅና ቀድሞ ወደ አዲስ አበባ የገባ አንድ ሰው — ‹‹ወደ አዲስ አበባ መሄድ ትፈልጋለህ?›› የሚል ጥያቄ አቀረበልኝ። ጊዜው 1985 ዓ.ም ነበር። በዚያን ዘመን ወደ አዲስ አበባ መምጣት ማለት ለዛሬው ትውልድ ወደ ኒው ዮርክ የመሄድን ያህል የሚያጓጓና እጅግ ትልቅ ነገር ነበር። በመሆኑም ጥያቄው እንደቀረበልኝ ሳላመነታ ተስማማሁ፤ ማለዳ 11 ሰዓት ላይም ከመሪዎቼ ጋር ተነስተን መኪና በመሳፈር አዲስ አበባ ገባን።
አዲስ አበባ እንደመጣሁ የመጀመሪያው የሥራ ቦታዬ ‹‹ምን አለሽ ተራ›› ነበር። ይህ ሰፈር ስያሜውን ያገኘው እናቶች ወደ ገበያ ሲወጡ የሚይዙትን እቃ ተመልካች ገዢዎች ‹‹ምን ይዘሻል?›› ወይም ‹‹ምን አለሽ?›› ከሚሉት የገበያ መጠየቂያ ዘይቤ እንደሆነ ይነገራል።
የሱቁ ባለቤት የሚኖረው አሜሪካን ግቢ አካባቢ ነበር። እኔም በየዕለቱ የሸጥኩበትን ገንዘብ በፌስታል ይዤ ማታ ማታ ወደ ቤቱ እወስድለት ነበር። አሰሪዬ ገና አጋሮ እያለሁም ቢሆን ምን ያህል ታታሪና ፈጣን እንደሆንኩ ያውቅ ነበር። በዚያ ላይ እንደ አሁኑ ሌብነት ያልተስፋፋበትና ታማኝነት የሰፈነበት ዘመን ነበር። ለምሳሌ ሥጋ የሚበላው በሳምንት ሁለት ቀን—በጁሙዓ እና በእሁድ ቀን ብቻ ነበር። የአሰሪዬ ወንድሞችም ቢሆኑ ከእኔ ጋር ልዩ ቅርበትና ፍቅር ነበራቸው፤ እንደውም አሁን አንደኛው ወንድሙ በለንደን የሚኖር ሲሆን፣ ዛሬም ድረስ የቅርብ ወዳጄ ነው።
ያም ሆኖ በምን አለሽ ተራ የገበያ ቦታ ላይ የሠራሁት ለአንድ ዓመት ያህል ብቻ ነው። ከዚያ በኋላ አንድ ወዳጄ በሞያሌ—በኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር አካባቢ ይሠራ ስለነበር ‹‹ለምን የድንበር ንግድ አንነግድም?›› የሚል ሐሳብ አቀረበልኝ፤ እኔም ሐሳቡን ተቀብዬ ወደዚያው አመራሁ።
ግዮን፡- በወቅቱ እዚያ ሱቅ ውስጥ አንድ ዓመት ሙሉ ስትሠራ ወርሃዊ ደሞዝህ ምን ያህል ነበር?
ጀበል፡- በወቅቱ ደሞዝ የሚባል ነገር አልነበረኝም። ቀደም ሲል እንደገለጽኩት በሳምንት ሁለት ቀን ሥጋ፣ በሌሎቹ ቀናት ደግሞ ጥሩ ምግብ ይቀርብልናል፤ ያ ለእኔ በቂ ነበር። ከዚያ ውጪ ሙሉ ትኩረቴ ሥራው ላይ ብቻ ነበር። የሚገርመው ግን በዚያ ምክንያት ትምህርቴን አቋርጬ ነበር።
ግዮን፡- እስቲ ጥቂት ስለ ቤተሰብህ ታሪክ ንገረን?
ጀበል፡- እናቴና አባቴ አሁን በሕይወት የሉም፤ አልፈዋል። ሦስት ወንድሞችና አንድ እህት አሉኝ። የክፍለ ሀገር ኑሮ ደግሞ ይታወቃል—ሙሉ በሙሉ ከመሬት ጋር የተያያዘ ነው።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ከመሬት ጋር ያለን ቁርኝት እጅግ የጠበቀ ነው። መሬታችንን አብዝተን እንወዳለን። ኢትዮጵያ ሰፊ መሬትና የታደለ የተፈጥሮ ሀብት አላት፤ ነገር ግን ትውልድና ሕዝብ በጨመረ ቁጥር ያ ሰፊ መሬት እየጠበበ ይሄዳል። ስለዚህ ያንን መሬት በአግባቡና በዘመናዊ መንገድ መጠቀም ያስፈልጋል። ሕዝባችን ግን መሬቱን ይዞ ከዓመት ዓመት ተመሳሳይ ባሕላዊ አሰራር ከመከተል ውጪ፣ የተሻለ ፈጠራ ታክሎበት እንዲሠራ ወይም ደግሞ አልምተው ለሚሠሩ ሰዎች አሳልፎ መስጠት አይወድም።
በተለይም ቀደም ሲል የነበረው የመሬት የሕግ ማዕቀፍ ደካማ ስለነበር፣ ሕዝቡ መሬቱ የሚነጠቅ እየመሰለው ሥጋት ነበረው። አሁን ነው አዲስ የገጠር መሬት ፖሊሲ የተዘጋጀው። አሁን ላይ በገጠር ያለው ማኅበረሰብ እየነቃ መጥቷል፤ ማኅበራዊ ሚዲያውም ቢሆን ሕዝቡን በደንብ አንቅቶታል።
የእኛ ሕዝብ በመሠረቱ መንግሥትን ያምናል። ስለዚህ አሁን መንግሥት በመሬት ላይ የያዘውን አዲስ ፖሊሲ ሁላችንም ተባብረን ከተገበርነው የዚህች ሀገር ሁኔታ በፍጥነት ይቀየራል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ። መንግሥት መሬት ላይ አልምተው ሥራ ለሚፈጥሩ ሰዎች በልዩ አሠራር መሬቱን ማመቻቸት ይኖርበታል። መሬት የሌላቸው ዜጎችም መሬት ካላቸው ሰዎች ጋር አብረው በመስራት ሀገርንም ሆነ የራሳቸውን ሕይወት መቀየር ይችላሉ።
ግዮን፡- ትንሽ ወደኋላ እንመለስና፣ ወደ ሞያሌ ያደረግከው ጉዞና የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?
ጀበል፡- በወቅቱ ሶማሌ ተራ አካባቢ ይሠራ የነበረ አንድ ወዳጅ ነበረኝ፤ እሱ ‹‹ምን አለሽ ተራ›› እያለሁ የተዋወቅኩት ጓደኛዬ ነው። ለድንበር ላይ ንግድ ወደ ሞያሌ ይዞኝ የሄደው እሱ ነው። በዚያን ዘመን በሰዎች መካከል ትልቅ መተማመን ስለነበር፣ ተያይዘን ወደ ሞያሌ አመራን።
ለተወሰነ ጊዜ ከኬንያዋ ሞያሌ ዕቃ እየገዛን በኢትዮጵያዋ ሞያሌ በኩል በማስገባት እንኖር ነበር። ዕቃዎቻችንንም መጀመሪያ ወደ ዲላ ከተማ እያመጣን እንሸጥ ነበር፤ እየቆየን ስንሄድ ደግሞ ወደ ሀዋሳ፣ ከዚያም አልፎ ወደ አዲስ አበባ እያመጣን መሸጥ ጀመርን። የሚገርመው ነገር ከሞያሌ በሦስት ሺህ ብር የገዛነውን ዕቃ አዲስ አበባ አምጥተን በሠላሳ ሺህ ብር እንሸጠው ነበር። በዚያን ወቅት የአንድ ዶላር ምንዛሬ አምስት ብር ገደማ ነበር።
ሥራው እጅግ ውጤታማ ስላደረገን ከዚሁ ጓደኛዬ ጋር አንዲት መኪና ገዛን። የገንዘብ አቅማችን በከፍተኛ ሁኔታ ተሻሻለ፤ የምንለብሰው ልብስ ጥራት ያለው፣ የምናደርገው ጫማም እጅግ ውድ ነበር። በዚያን ወቅት በሶማሊያ የዚያድ ባሬ መንግሥት የወደቀበት ጊዜ ነበር።
መኪናዋን የሸጠልን አካል ‹‹መኪናዋ ከሶማሊያ የመጣች ነች›› ብሎን ነበር። ነገር ግን መኪናዋ ከሶማሊያ የመጣች ሳይሆን፣ ከአዲስ አበባ ተሰርቃ የተወሰደች የመከላከያ መኪና ነበረች። የመኪናዋ የሰሌዳ ቁጥር ግን የሚያመለክተው ሀዋሳን ነበር። ያችን መኪና አንድ ሁለት ወር ያህል እንደሠራንባት ዲላ ከተማ ላይ በቁጥጥር ሥር ውላ ተያዘች። መኪናዋ ስትያዝ እኔ አዲስ አበባ ስለነበርኩ ደውለው ነገሩኝ። መኪናዋን ለሸጡልን ሰዎች ስንደውል ግን አስተባበሉ።
ወዲያው ተነስቼ ወደ ዲላ ሄድኩ፤ መኪናዋ በፖሊስ ጣቢያ በር ላይ ቆማ ስላየኋት በፍርሃት ተመልሼ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ። አዲስ አበባ በመጣሁ በሁለተኛው ቀን፣ አሜሪካን ግቢ በሚገኝ አንድ ሱቅ ባንኮኒ ላይ ቁጭ ብዬ ሳለ፣ በ‹‹DX›› መኪና የመጡ ሁለት ወጣቶች ያዙኝ። ሰዎቹ የደኅንነት አባላት ነበሩ። ‹‹ጀበል እንፈልግሃለን›› አሉኝ። እሺ ብዬ ስከተላቸው የደኅንነት መታወቂያቸውን አሳዩኝና መኪና ውስጥ አስገብተውኝ የትግርኛ ሙዚቃ ከፍተው ቀጥታ ወደ ማዕከላዊ ወሰዱኝ።
ቀደም ሲል ፖሊስ ጣቢያ እንኳ ገብቼ የማላውቅ ሰው በመሆኔ፣ ማዕከላዊ ስደርስ እጅግ ደነገጥኩ። በሰዓቱ መርማሪዎቹ በስልክ ‹‹ተይዟል! ተይዟል!›› እያሉ ይደዋወሉ ስለነበር፣ እንደ አደገኛ ወንጀለኛ ነበር የታየሁት። ወዲያው መኪናዋም ተይዛ ወደ አዲስ አበባ መጣች። ሰዎቹ ‹‹ዘራፊው እሱ ነው›› ሲሉ፣ እኔ ግን ገዝቼ እንደሆነ ለማስረዳት ሞከርኩ። የሰጠሁት መረጃ ትክክል በመሆኑ መኪናዋን የሸጡልን ሰዎች ተያዙ።
ከዚያ በኋላ ጉዳዩ ሲጓተት ቆይቶ ረጅም ጊዜ ወሰደ። መጀመሪያ በዋስ ተለቅቄ የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ ላይ ግን ድጋሜ ታሰርኩ። በዚያን ወቅት ኦሮሞዎች ‹‹በኦነግነት››፣ አማሮች ደግሞ ‹‹በመአሕድ›› ይታሰሩ ስለነበር፣ እኔም በኦነግ ስም ልታሰር ችያለሁ። በነገራችን ላይ እኔ የ12ኛ ክፍል ማትሪክ ፈተና የወሰድኩት እስር ቤት እያለሁ ነው።
በዚያን ወቅት መንግሥት በርካታ ጋዜጠኞችን ያስር ነበር። መንግሥት በወቅቱ ሚዲያውን ከፍቶት የነበረው ሰብስቦ ለማሰር ይመስለኛል። ምክንያቱም በኋላ ላይ ስናየው ሁሉንም ሰብስቦ ካሰረ በኋላ፣ ከፍቶት የነበረውን የሚዲያ ነፃነት መልሶ ዘጋው።
እስር ቤት እያለሁ ከፖሊሶች ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበረኝ። በዚህም የተነሳ ውሎዬ ከቤተሰብ ጋር ያህል ነበር፤ በተለይም አሁን የአፍሪካ ሕብረት ሕንፃ የተገነባበት ቦታ የዚያን ወቅት የእኛ መዋያ ነበረ። እኔ እስር ቤት ውስጥ የምጋጨው ከእስረኞች ጋር ነበር፤ ምክንያቱም ‹‹አቃጣሪ ነው›› ብለው ስለሚያስቡ ይጣሉኝ ነበር። እኔ ደግሞ ወንጀልን አልደግፍም፤ ወንጀል ሲሠራ ካየሁ ስለምቃወም ከፖሊሶች ጎን እቆም ነበር።
እኔ እዚያ ውስጥ የኮሚቴ አባል ስለነበርኩ፣ ጫትና መሰል ነገሮች ሲገቡ ዝም ስለማልልና ከማረሚያ አስተዳደሩ ጋር አብሬ ስለምሠራ ‹‹አቃጣሪ›› ይሉኛል። እኔ ደግሞ ከእስረኞች በኩል የተወከልኩ የሁሉም ኮሚቴዎች ኃላፊና የእስረኞች አስተዳዳሪ ነበርኩ። የእስረኞች አስተዳደር የወሰነው ነገር ቀጥታ ወደ ዞን ተጠሪ ይላካል፡፡
በእስር ቤት ውስጥ ለአራት ዓመታት ያህል ቆይቻለሁ። እነዚህን አራት ዓመታት ግን በአግባቡ ተጠቅሜባቸዋለሁ። እዚያ እንደገባሁ ትምህርቴን መማር ጀመርኩ። የመጀመሪያውን አንድ ዓመት ማረሚያ ቤቱ ጥናት ያደርጋል፤ ምክንያቱም ማንኛውንም እስረኛ ዝም ብሎ ወደ ትምህርት ቤት አይልክም። ከዚያ በኋላ ግን ትምህርቴን በቀጥታ ቀጠልኩ።
በማረሚያ ቤቱ ውስጥ እኔን የማያውቀኝ አልነበረም፤ ምክንያቱም የአስተዳደሩ አካል እንደመሆኔ መጠን ወንጀል መከላከል ላይ እሳተፍ ነበር። ‹‹ያቃጥራል›› ስለሚሉኝ ድብደባ ሳይቀር ያስተናገድኩበት ጊዜ ነበር። በኋላ አካባቢ ግን ከእኔ ተደብቀው ወንጀል መፈፀም ጀመሩ። እኔም ያላየሁት ነገር ላይ ትኩረት አላደርግም ነበር። ለምሳሌ ‹‹የተክለሃይማኖት ልጆች›› የሚባሉ በወቅቱ ኃይለኛ ወጣቶች ነበሩ። የሚንቀሳቀሱት በቡድን ነበር፤ የአራት ኪሎ፣ የኮልፌና የመሰል ሰፈሮች ልጆች በቡድን እየተደራጁ በድንጋይ ይማቱ ነበር። በጨለማ ቤት ተቀጥተው እንኳን የማይታረሙ ነበሩ።
ማስታወሻ፡- ውድ የግዮን መጽሔት አንባቢያን ከኢንጂ. ጀበል ጀማል ጋር ያደረግነው የመጀሪያዉ ክፍል በዚህ መልክ አዘጋጅተነዋል ፡፡ ቀጣዩ ክፍል በሳምንቱ መጨረሻ የምናቀርብ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን ።
ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 237 ጥቅምት 2019 ዓ.ም
