ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ላይ ሊወሰዱ የሚችሉ ወታደራዊ አማራጮችን በተመለከተ ከአሜሪካ ጦር የመካከለኛው ምሥራቅ ከፍተኛ አዛዥ ገለጻ እንደተሰጣቸው የአሜሪካ ዜና ምንጮች ዘገቡ።
በአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዛ አዛዥ ብራድ ኩፐር ባልተለመደ ሁኔታ ለፕሬዝዳንቱ ገለጻ መስጠታቸው፣ አሜሪካ በቅርቡ ኢራን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ልትወስድ እንደምትችል የሚያመለክት እንደሆነ ዎል ስትሪት ጆርናል እና አክሲዮስ በዘገባዎቸቻው አስነብበዋል።
የሐሙስ ዕለቱ ወታደራዊ ማብራሪያ የተሰጠው አሜሪካ ከአማጋሽ ዘመን ምርጫ መጠናቀቅ በኋላ ወደ ወደታራዊ እርምጃ ልትገባ ትችላል የሚሉ ግምቶች እየተሰጡ ባሉበት ወቅት ነው።
የትራምፕ አስተዳደር የባሕረ ሰላጤው አረብ አገራት ከአማጋሽ ዘመን ምርጫ በኋላ ለሚካሄድ ለአጭር ጊዜ ለሚቆይ ግን ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ ዘመቻ እንዲዘጋጁ ማሳወቁን ዎል ስትሪት ጆርናል ጋዜጣ ከቀናት በፊት አስነብቦ ነበር።
አክሲዮስ በበኩሉ አሜሪካ ከኢራን ጋር የሚደረገውን የሰላም ንግግር በድጋሚ ለማስጀመር ከምታደርገው ጥረት ጎን ለጎን ከምርጫው በኋላ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻዎችን ዳግም ለመጀመር እየተዘጋጀች መሆኑን ዘግቧል።
ወታደራዊው አዛዥ ብራድ ኩፐር ባልተለመደ ሁኔታ በአካል ተገኝተው ለፕሬዝዳን ትራምፕ በሰጡት ገለጻ ላይ አሜሪካ ከሆርሙዝ ወሽመጥ መውጫ ያጡ የነዳጅ ጫኝ መርከቦችን አጅቦ በማውጣት ወደ ዓለም አቀፍ የኤነርጂ ገበያዎች ለማድረስ ስለሚከናወነው ወታደራዊ ዘመቻ ማብራሪያ መሰጠታቸውን አክሲዮስ ዘግቧል።
የአሜሪካ ጦር ከግምጃ ቤቱ ጋር በመተባበር እያካሄደ ስላለው የኢኮኖሚ ጫና ዘመቻም መረጃዎችን ለትራምፕ አቅርበዋል ተብሏል።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጄዲ ቫንስ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግዜትን ጨምሮ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት በዚህ ገለጻ ላይ አሜሪካ እያካሄደው ስላለችው የባሕር ጉዞ እገዳም መነሳቱን የዎል ስትሪት ዘገባ ያመለክታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ አሜሪካ ከኢራን ጋር የሚደረገውን ንግግር በድጋሚ ለማስጀመር ጥረት እያደረገች መሆኑ ተዘግቧል። ምክትል ፕሬዝዳንቱ ቫንስ ለኢራን ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ጸሐፊ ሞህሲን ራይዚ ደብዳቤ ልከዋል።
ደብዳቤው ድርድርን የተመለከተ እንደሆነ የአሜሪካ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። ደብዳቤው መላኩን ያረጋገጡት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ደብዳቤው ለኢራን ከሚቀርብ የሕክምና ቁሳቁስ እና መድኃኒት ጋር የተያያዘ መሆኑን ተናግረዋል።
