የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ታህሳስ 26 ቀን 2018 ዓ.ም ይፋ ባደረጉት መረጃ፤ በአሜሪካ የሚኖሩ የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ ተወላጅ ቤተሰቦች ከፍተኛ የመንግሥት ድጋፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታወቁ።
ፕሬዝዳንቱ “ትሩዝ ሶሻል” በተሰኘው የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ “የስደተኞች ማኅበራዊ ድጋፍ ተጠቃሚነት መጠን በትውልድ ሀገር” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሰንጠረዥን አጋርተዋል።
ሰንጠረዡ በሀገሪቱ የሚኖሩ ስደተኞች ከተወለዱበት ሀገር ጋር በተያያዘ በአሜሪካ ውስጥ ያላቸውን የመንግሥት ድጋፍ ተጠቃሚነት መጠን የሚያሳይ ሲሆን፣ ወደ 120 የሚጠጉ ሀገራትን እና ግዛቶችን በዝርዝሩ አካቷል።
በሰንጠረዡ፤ 47.6 በመቶ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ተወላጅ ቤተሰቦች እና 71.9 በመቶ የሚሆኑ የሶማሊያ ተወላጅ ቤተሰቦች የመንግሥት ድጋፍ እንደሚያገኙ አመልክተዋል። ይህም ሶማሊያን ከቡታን (81.4%) እና ከየመን (75.2%) በመቀጠል በዝርዝሩ ሦስተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል።
በተጨማሪም አፍጋኒስታን እና ዶሚኒካን ሪፑብሊክ እያንዳንዳቸው 68.1 በመቶ ተጠቃሚነት እንዳላቸው የተጠቀሰ ሲሆን፤ በአንፃሩ እንደ ሳውዲ ዓረቢያ እና ኩዌት ያሉ ሀገራት ተወላጆች በ25 በመቶ ዝቅተኛው የድጋፍ ተጠቃሚነት መጠን ላይ ይገኛሉ።
አሃዞቹ ይፋ የሆኑት የትራምፕ አስተዳደር የተወሰኑ የስደተኛ ማኅበረሰቦች በአሜሪካ “የበጀት ጫና” እያደረሱ ነው በሚል ጠንከር ያለ ንግግር እያደረገ ባለበት ወቅት ነው።
