‹‹ሀገርና የውርስ ቤትም አንድ ናቸው›› ጠበቃ መሠረት ሥዩም
ግዮን መጽሔት : ‹‹ማኩታ›› የተሰኘው ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የሕግ አገልግሎት ሰጪ ድርጅት መሥራችና ማኔጂንግ ፓርትነር ከኾነችው መሠረት ሥዩም ጋር ያደረግነው ቆይታ እንደሚከተለው ተጨዋውተናል፡፡ መልካም ንባብ!
ግዮን፡- በዘርፉ ያለው የትምህርት ሥርዓትስ ምን ዓይነት መኾን አለበት ትያለሽ?
መሠረት፡- የሕግ ትምህርት ቤቶች በጣም ጠንካራ ሥራ መሥራት እንዲችሉ መታገዝ እና ጠንካራ መኾን ይኖርባቸዋል፡፡ ተማሪዎች ለዘርፉ ዕውቀት ግብዓት የሚኾኗቸውን ማናቸውንም ነገሮች ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ መጽሐፎች፣ በቴክኖሎጂ የታገዙ የኢንተርኔት አገልግሎቶችና መሰል ነገሮች በተገቢው ሁኔታ ለተማሪዎች መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ የአስተማሪዎች ብቃትም መሠረታዊ ነው፡፡ በሌላ በኩል ሕግ ማለት ተግባር ስለኾነ ተማሪዎቹ በተማሪነት ዘመናቸው ወጥተው ከተግባራዊ የሕግ ሥራዎች ጋር እንዲገናኙ ማድረግ ለፍትሕ ሥርዓቱ መጎልበት ትልቅ ሚና አለው፡፡ ምክንያቱም ተማሪዎቹ ጨርሰው ሥራ ሲጀምሩ ተግባራዊ ሥራውና የሕግ ንድፈ ሐሳቡ ይጣጣምላቸዋል፡፡ በዚህም የተሟላ የፍትሕ አገልግሎት መሥጠት ይችላሉ፡፡ ተማሪዎች የሕግ ሥርዓት ከዳበረባቸው ሀገራት ልምድ እንዲቀስሙ ማድረግም ያስፈልጋል፡፡
ግዮን፡- እንደሕግ ባለሙያነትሽ እስካሁን በነበረሽ ቆይታ ላይ የገጠመሽ የተለየ ኬዝ (ጉዳይ) አለ? ከሙግት ይልቅ በስምምነት የሚያልቁ ጉዳዮችስ አሉ?
መሠረት፡- አብዛኛውን ጊዜ እኛ ቢሮ ውስጥ ከ80% በላይ የሚኾኑ ትልልቅ የሕግ ጉዳዮች በስምምነት ያልቃሉ፡፡ ግለሰብና ግለሰብ ቀርቶ ተቋምና መንግሥት በስምምነት የጨርስናቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ባለጉዳዮች እኛ ጋር ሲመጡ ቀድመን ጉዳያቸውን በስምምነት እንዲጨርሱ እንገፋቸዋለን፡፡ በባልና ሚስት፣ በነጋዴዎች መካከል የሚያጋጥሙ በጣም ብዙ ጉዳዮችን በስምምነት እንዲጨርሱ አድርገናል፡፡ ከዚህ ባለፈ አብዛኛውን ጊዜ የሚያጋጥመኝ የግምት ውል ማስተናገድና በባለሙያ ያልተደገፈ ሥራ መሥራት ናቸው፡፡ በግምት ውል ሲዋዋሉ የሚያመጣባቸውን ችግር አለማወቅን ጨምሮ፣ የግለሰቦች ግትርነትና አልሸነፍ ባይነት ብሎም ነገሮችን በሰላም ከመፍታት ይልቅ በጀብድ ለመፈፀም መሞከር ይታያል፡፡
የግልፅነት ጉዳይም በተደጋጋሚ የሚታይ ችግር ነው፡፡ በአቋራጭ ነገሮችን ለመጨረስ መሞከርና ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት መሻት የሚታዩ ችግሮች ናቸው፡፡ ለምሳሌ አንድ የማልረሳው ገጠመኝ አለ፡፡ ብዙ ጊዜ በውልደት ሂደት ውስጥ መካካድና አለመተማመን ያለው በአባትነት እንጅ በእናትነት አልነበረም፡፡ ነገር ግን አንዴ ‹‹እከሊት እናቴ ናት›› ብሎ የተከረራከረን ሰው አውቃለሁ፡፡ ገንዘብ ስላላቸው እናቴ ናት ብሎ ነበር ክስ የመሠረተው፡፡ ኾኖም በረጅም የክርክር ሂደት ሊረታ ችሏል፡፡ እኝህ ሴት በጣም የሚያሳዝኑ ነበሩ፡፡ ልጅም የላቸውም ፤ መሀን ናቸው፡፡ የክርክሩ መቋጫ የኾነው የሕክምና መረጃ ነበር፡፡ ሰው በውሸት እዚህ ድረስ መከራከሩ ይገርመኝም ያሳዝነኝም ነበር፡፡ ባለሙያ ላይ ተማምኖ መሥራት ተገቢ ነው፡፡ ባለሙያ ደግሞ ደንበኛው መተማመን እንዲችል ጤናማ የኾነ፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የዝግጅት አገልግሎት መሥጠት ይኖርበታል፡፡
ግዮን፡- በእናንተ ተቋም ሐሰተኛ ክሶችን ይዘው የመጡ እንግዶችን ስታገኙ ምን ታደርጋላችሁ?
መሠረት፡- አናስተናግደውም፡፡ የሙያ ሥነ ምግባሩ ራሱ የማያዋጣውን አያዋጣም ብሎ መመለስ እንዳለበት ይነግራል፡፡
ግዮን፡- ከአለባባስ አንፃር የምትከተይው መርህ ምንን መሠረት ያደረገ ነው? ጸጉርሽን የምታስሪበት ሻሽ ምሥጢርስ ምንድነው?
መሠረት፡- እንደ አጋጣሚ በበርካታ የአፍሪካ ሀገሮች ውስጥ ሠርቻለሁ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ሳላስበው ከኢትዮጵያዊ ባሕል ወደ አህጉራዊ ባሕል የተሸጋገርኩ ይመስለኛል፡፡ አፍሪካውያን በርካታ ተመሳሳይ ባሕሎች አሏቸው፡፡ እነዚህን ባሕሎች በእኛ ሀገርም መገልገል አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለዚህ ብዙ የአፍሪካ ሀገር ላይ እንደሚሠራ ሰው አፍሪካዊ አለባበስ መልበስ እወዳለሁ፡፡ ደግሞም ምቾት አለው፡፡ እንደምታየኝ እኔ ቀይ ነኝ፡፡ ብዙ ሰው የሌላ ሀገር ዜጋ ነው የምመስለው፡፡ ይኼ ሻሽ ምርቱ የኢትዮጵያም ስለኾነ፣ ስለብሰው ኢትዮጵያዊነቴንም አፍሪካዊነቴንም በደንብ ይገልጽልኛል፡፡ በዛ ላይ የጊዜ እጥረት ስለሚያጋጥመኝ ፀጉር ቤት አልሄድም፡፡ ሌላ ነገር ማድረግም አልወድም፡፡ እንዲህ ዓይነት የአለባበስ ሥርዓት መከተል ከጀመርኩ ቆይቻለሁ፡፡ ከ17 ዓመት በላይ ይኾነኛል፡፡
ግዮን፡- በድርጅታችሁ መግቢያ ላይ የሚታየው ምልክት ምንድ ነው?
መሠረት፡- ሎጐ ነው፡፡ ሎጎው ላይ ጄስቲስ ሌዲ ትታያለች፡፡ ጄስቲስ ሌዲ ብዙ ጊዜ ፈረንጅ ነች፡፡ ከስር ደግሞ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፒላር አለ፡፡ ሚዛኑም አለ፡፡ እኔ ሎጎ ላይ ግን ጄስቲስት ሌዲዋ አፍሪካዊት ኾነች፡፡
ግዮን፡- በአንቺ ተቋም ውስጥ ምን ያህል የሕግ ባለሙያዎችና አጠቃላይ ሠራተኞች አሉ?
መሠረት፡- አጠቃላይ ከእነ ባለሙያዎቹ ብዙ ናቸው፡፡ ነገር ግን እኛ ሥራ የምንሠጣቸው በጣም በርካቶች ናቸው፡፡ ይህ የሥራ ሥርጭት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይኾን በርካታ የአፍሪካ አገሮችንም ጭምር ያካተተ ነው፡፡
ግዮን፡- የተቋማችሁ ሠራተኞች ወደ ሥራ ሲገቡ ስልካቸው በሌላ ይቀየራል ይባላል፡፡ ይህ ለምን ኾነ? ከሌላው ዓለም የተማርሽው ተሞክሮ አለ?
መሠረት፡- እዚህ ሠራተኞች የሚጠቀሙት የሥራ ስልካቸውን እንጅ የግል ስልካቸውን አይደለም፡ የግል ስልክ የምንጠቀመው ምሳ ሰዓት፣ የሻይ ሰዓትና ከቢሮ ስንወጣ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ትኩረታችንን ሰብስበን ከሥራው ጋር የተገናኘ ሥራ ብቻ እንድንሠራ ነው፡፡ ይህ ተግባር በበርካታ ሀገራትም የሚደረግ ነው፡፡ ይህ መደረጉ ሠራተኛው ራሱን ለሥራው ብቻ እንዲሠጥ ያደርገዋል፡፡ የግል ስልክ አለመያዝ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አላስፈላጊ ጊዜ ከማባከን ይቆጥባል፡፡ ሥራው ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ፣ ለሥራው የተሰጠው ሰዓት በሥራው ብቻ ያልቃል፡፡
ግዮን፡- እንደሕግ ባለሙያ፣ ሥራንና ለሥራ የተመደበን ጊዜ ከማክበር ጋር በተያያዘ ማለት የምትፈልጊው ምንድን ነው?
መሠረት፡- ተሞክሮዬን ላጋራ፤ እኛ መሥሪያ ቤት ኮምፒዩተር ላይ ጌም መጫን አይቻልም፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀምም አይቻልም፡፡ በግል ስልክ መገልገልም አይቻልም፡፡ በሥራ ግምገማ ጊዜ የምንገመግመው የሥራውን ፍሬ ነው፡፡ ሠራተኛው የሥራ ሒደቱን በቀንና በሳምንት ሪፖርት ያደርጋል፡፡ በዚህም በየሳምንቱ ይገመገማል፡፡ ሠራተኛው የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣት አለበት፡፡ ደንበኛውን በአግባቡ ይዞ እንዲያስተናግድ ሥራን በእኔነት መንፈስ መሥራት፣ ከነገ ተበድሮ ዛሬ አለማጥፋት፣ ከትናንትና ዛሬ አለማጉደል በእኛ ድርጅት አይፈቀደም፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሰው ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ የተሰጠውን የሥራ ኃላፊነት በተገቢው መንገድ ያከናውናል፡፡
ግዮን፡- ከሠራተኞችሽ ጋር ሥራዎችን በተመለከተ ያላችሁ ምክክር ምን መልክ ያለው ነው?
መሠረት፡- በየጊዜው ሐሳብ እንለዋወጣለን፡፡ በርግጥ አሁን ላይ ጊዜ ስለሚያጥረኝ በየአጋጣሚው መሰብሰብ አንችልም፡፡ ነገር ግን በየሳምንቱ ሁሌ ሰኞ ስብሰባ አለን፡፡ የሥራ ሠዓቱን የተመለከተ ሪፖርቶችና የሀሳብ ልውውጦች አሉ፡፡ ሁሉም ሰው ይሠራል፡፡ እኔም ብኾን ካልሠራሁ ድርጅቴ ይቀጣኛል፡፡ ከሰራተኞቼ ጋር እንደ ጓደኛ ነው ቅርበታችን፡፡ እንደውም መሥሪያ ቤታችንን ‹‹ማኩታ ፋሚሊ›› ነው የምንለው፡፡ በተቋማችን አለቃ የለም ፤ ሥራው ነው አለቃ፡፡
ግዮን፡- ካለሽ የሥራ ጥበት አንፃር የእረፍት ጊዜ አለሽ? በእረፍትሽ ጊዜስ ምን ትሠሪያለሽ?
መሠረት፡- ማንበብ እወዳለሁ፤ ከቤተሰብ ከጓደኛ ጋር ተሰብስቦ መጫወት ደስ ይለኛል፡፡ ውሃ ዋና እወዳለሁ፡፡ ከልጆች ጋር መጫወት እወዳለሁ፡፡ አንዳንዴም ምስኪን ሠዎችን መርዳት፣ ሔዶ መጠየቅ ያስደስተኛል፡፡ የበጎ አድራጎት ሥራም እወዳለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር ለምሳሌ ፍቼ ላይ ‹‹ፍቅር›› የሚባል መረዳጃ መኅበር መሥርተን ወላጆች ኖሯቸው በቂ ምግብና ልብስ የሌላቸውን ልጆች እናግዛለን፡፡ በተመሳሳይ በደብረዘይትም ‹‹ጆሻይ አካዳሚ›› የሚል ወላጅ አልባ ልጆችን በተቋም ደረጃ እንረዳለን፡፡
ግዮን፡- ‹‹ለምን የሕግ ሙያ ውስጥ ገባሁ›› ብለሽ የተማረርሽበት ጊዜ ኖሮ ያውቃል?
ማስታወሻ- ውድ አንባቢያን፣ ከጠበቃ መሠረት ሥዩም ጋር ያደረግነው ተከታታይ ቃለ ምልልስ በዚህ አልተጠናቀቀም፡፡ ቀሪዉንና የመጨረሻዉን ክፍል በሚቀጥሉት ቀናት ይዘን የምንመለስ ይኾናል፡፡
ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 231 መጋቢት 2018 ዓ.ም
