በራያ ባህል፣ ወግ፣ ታሪክና ማንነትን በዜማዎቻቸው ለሀገርና ለዓለም ያስተዋወቁት ተወዳጁ ድምፃዊ በላይ ዘነበ በሞት ተለዩ።
ለረጅም ጊዜ በሕመም ሲሰቃዩ የቆዩት ድምፃዊው፣ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ዛሬ ኅዳር 13 ቀን 2019 ዓ.ም. በራያ አላማጣ ወረዳ፣ ኩሉጊዜ ለምለም ጣቢያ በሚገኘው ጓል ኣጆ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል።
በላይ ዘነበ የራያን ባህላዊ ሙዚቃ፣ ቋንቋ፣ ወግና ማንነት በጥበብ ሥራዎቻቸው ያስተዋወቁ ሲሆን፣ በተለይ የራያ ባህላዊ የሙዚቃ ሥልት የሆነውን «ጉማየ» በማስጠበቅና በማስፋፋት የማይረሳ አሻራ አኑረዋል።
«ዋራሞዋ»፣ «እማነየ» እና «ጉማየ» ከሚታወሱት የሙዚቃ ሥራዎቻቸው መካከል ሲሆኑ፣ በዜማዎቻቸው የራያን ባህልና ታሪክ ለቀጣዩ ትውልድ አስተላልፈዋል።
የከያኒው ሕልፈት በቤተሰቦቻቸው፣ በራያ ሕዝብ፣ በጥበብ ባለሙያዎችና በአድናቂዎቻቸው ዘንድ ትልቅ ሐዘን የፈጠረ ሲሆን፣ ያበረከቱት የባህልና የሙዚቃ ቅርስ ግን ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ነው።
ነፍስ ይማር!
