የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትያትርና ፊልም ተማሪዎች፣ መምህራን፣ እንዲሁም እንግዶች በተገኙበት፣ ጉባኤዉ ጥር 16 ቀን 2918 ዓም በባህል ማእከል አዳራሽ ተካሄደ፡፡ ጉባኤዉን ዶክተር መሰለ መንግስተአብ በሊቀመንበርነት መራ፡፡
የሙዚቃ ተመራማሪዉ ሰርጸ ፍሬሰንበት የሙዚቃንና የሰዉን ልጅ ጤንነት መስተጋብር፣ እንዲሁም ሙዚቃ ቴራፒ በአገራችን ምን ገጽታ እንዳለዉ አንደበተ-ርቱእነቱ አብራራ፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትያትር ጥበባት ከተመረቀች በኋላ፣ አየርላንድ በሚገኘዉ ትሪኒቲ ኮሌጅ፣ አለም አቀፍ የአንጎል ጤና (Bain Health) ኢኒስቲቲዩት፣ ለአንድ አመት ተምራ የተመለሰችዉ ሜሮን ሲሳይ ስለ ስነጥበባት ቴራፒ ትምህርትና ተግባራዊ ተሞክሮዋ፣ በተለይም ስለ ስእልና ቅብ ህክምና በድንቅ አቀራረብ ጥልቅ እዉቀት አስጨበጠች፡፡
ይህ ጸሀፊም ስለስነጥበባት ቴራፒ ንድፈሀሳና ስለ አገራችን የስእል፣ የሙዚቃና የትያትር ቴራፒ አጠቃላይ ገጽታ ጥናቱን አቀርበ፡፡ ከአቅርቦት በኋላም የሞቀ ጠቃሚ ዉይይት ተካሄደ፡፡ ከቀረቡት ዋና ዋና ፍሬነገሮች ዉስጥ፡ በአገራችን ያለዉ የስነጥበባት ቴራፒ ግንዛቤ አናሳነት ያስከተላቸዉ አሉታዊ ገጽታዎች ተወስተዋል፡-
፩. በስነጥበባት ህክምና ዘርፎች፣ ማለትም በድራማ/ትያትር ቴራፒ፣ሙዚቃ ቴራፒ፣ የስእል ቴራፒ፣ የቅብ ቴራፒ፣ የሴራሚክ ቴራፒ፣ በዳንስን ቴራፒ፣ የአእምሮ ህክምና ለመስጠት የሚያስችል ልዩ የትምህርት ዝግጅት እና የማከም የብቃት ማረጋገጫ ያለዉ አንድም የአእምሮ ሀኪም ሆነ የስነጥበብ ሰዉ በአገራችን አለመኖሩ፤
፪. የNGo ን ፍላጎት ለሟሟላት፣ በዉጭ አገር ሰዎች ለሳምንታትና ለጥቂትወራት በተሰጡ፣ ግን አለም አቀፋዊ የብቃት ደረጃ ባላሟሉ አጫጭር የስነጥበብ ቴራፒ ስልጠናዎች ብቻ፣ የአእምሮ ህክምና ለመስጠ እየተደረገ ያለዉ ሙከራ በተገላቢጦሽ ለአደጋ የሚያጋልጥ መሆኑ፣
፫. የአእምሮ ህክምና የግል የንግድ ተቋሞችና Ngo ዎች ከዚህ አኳያ ሲንቀሳቀሱ፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በአለም አቀፍ መስፈርት ቁጥጥር ለማድረግ ግንዛቤ አለማዳበሩ፣
፬. የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንኩዋን የስነጥበባት ህክምና ብቃትን ሊቆጣጠር፣ የሙዚቃ ቴራፒ ተምሮ የተመለሰዉ ዶክተር መልካሙ መአዛ በሙያዉ እንዳያገለግል እንቅፋት ሆኖ ተስፋ በማስቆረጥ ካገር ማሳደዱ፤ ብቸኛ የካዉንስሊን ስፔሻሊሰቱ አንጋፋዉ ዶ/ር ዮሱፍ ኡመር የግል የምክር አገልግሎትን እንዳይሰጥ ፈቃድ ከልክሎ ድርጅቱን ያዘጋዉ፣ ባኩዋያዉ ደግሞ አንድ ህንዳዊ በዶልፊን ሆቴል ዉስጥ ቅር የሚያሰኝ የሴክስ ቴራፒ አገልግሎት ሲሰጥ በዝምታ አይቶት ነበርዉ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በዚህ ረገድ ጉዞዉ ምንኛ ቀሰስተኛ መሆኑን ማመልከቱ፤
፭ የስነጥበባት ቴራፒን ትምህርት በአገራችን ለመጀመር፣ ካሪኩለም ማዘጋጀትና ማስተማር የሚቻለዉ፣ በስነጥበባት ቴራፒ ስፔሻላይዝ ባደረጉና በማስተማር አለምአቀፋዊ የብቃት ደረጃ ባሟሉ ፕሮፌሰሮች መሆን እንደሚገባዉ ያልተገነዘቡ አንዳንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የስነጥበባት ቴራፒን እዉቀት ባልቀሰሙ ሳይካትሪስቶችና የስነጥበብ ባለሙያዎች ስብስብ የድህረ-ምረቃ ፕሮግራም ለመመስረት የሚቻል እየመሰላቸዉ የሚያደርጉት የጨዋነት እንቅስቃሴ አሳሳችና ለአደጋ የሚያጋልጥ መሆኑ፤ ብቃት በሌላቸዉ ካሪኩለም የማስነደፉና ስለትምህርቱ እዉቀት በሌላቸዉ የማስተማሩ ተመሳሳይ ልምድ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ዉስጥ እየታየ ያለ በመሆኑ፣ የአርት ቴራፒም ጉዳይ ከዚህ ለማምለጥ ያለዉ አጋጣሚ አስተማማኝ አለመሆኑ፤
፮ ይልቁኑ፣ ባደጉ አገሮች ከግማሽ ምእት በላይ የተቀመረን ንድፈሀሳብና በተግባር የዳበረ እውቀትን ከአገር በቀል እዉቀት ጋር በማዛመድ ካሪኩለም የሚነድፉና የሚያስተምሩ ሁለት የአርትስ ቴራፒ ፕሮፌሰሮችን በቅጥር ወይ በእርዳታ በመስመጣት፤ በአኳያዉም ተማሪዎች በስነጥበባት ቴራፒ ስፔሻላይዝ እንዲያደርጉ ወደ ዉጭ አገር በመላክ አስተማማኝ መፍትሄ መመላከቱ በጉባኤዉ ተዳሷል፡፡
፯. ከዚህ ጋር ተጓደኝነት ያለዉን፣ ስነጥበባትን እንደ መደበኛ ትምህርት ማስተማርያ ዘዴ የመገልገል አቅም፣ ከላይ በተጠቀሰዉ አቅጣጫ ለማጎልበት ተመሳሳይ ጥረት መደረግ እንደሚያስፈልግ ተወስቷል፡፡
(አቦነህ አሻግሬ )
