የሐጋይ ኤርሊክ “Greater Tigray”
ሔኖክ ገለታው
ግዮን መጽሔት :- የእስራኤላዊው የታሪክ ተመራማሪና የታዋቂው የአፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ ጥናት ፕሮፌሰር ሐጋይ ኤርሊክ ሥራ የሆነው “Greater Tigray and the Mysterious Magnetism of Ethiopia” የተሰኘው መጽሐፍ፣ የሰሜን ኢትዮጵያንና የቀይ ባሕር አካባቢን ውስብስብ የፖለቲካና የታሪክ ውጥረት የሚያስረዳ የምርምር ውጤት ነው፡፡ ፕሮፌሰር ኤርሊክ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያና በቀይ ባሕር ጂኦ-ፖለቲካ፣ በኢትዮጵያና በግብፅ የውሃ-ፖለቲካ ግንኙነት፣ እንዲሁም በራስ አሉላ አባ ነጋ የሕይወት ታሪክ ላይ ባዘጋጇቸው መጻሕፍቶቻቸው በዘመናዊ የኢትዮጵያ ጥናት ውስጥ ከፍተኛ ስም ያተረፉ ተመራማሪ ናቸው፡፡ በዚህ አዲስ ምሁራዊ ሥራቸው ደግሞ፣ የትግራይን ሕዝብና መሪዎች የታሪክ ጉዞ ከኢትዮጵያ ሃገረ-መንግሥት ግንባታ ጋር ባላቸው ረቂቅና ጠንካራ ትስስር ዐውድ ውስጥ ይተነትናሉ፡፡
የሁለቱ ተቃራኒ አንብሮዎች (Thesis) ፍልሚያ
የኤርሊክ መጽሐፍ መሠረታዊ መነሻ በኢትዮጵያ የታሪክና የፖለቲካ አየር ላይ ዘመናትን ያስቆጠሩትና አሁንም ድረስ የሀገሪቱን እጣ ፈንታ በመቅረጽ ላይ ያሉት ሁለቱ ተቃራኒ የታሪክ መስመሮች (ማለትም የአማራና የትግራይ አንብሮዎች) ያካሄዱት የከረረ ፍልሚያ ነው፡፡ ፀሐፊው የነዚህን ሁለት የፖለቲካ አመለካከቶች መሠረታዊ ልዩነት ሲያብራራ፣ የ‹አማራ አንብሮ› ማዕከላዊነትን፣ ወጥ ብሔራዊ ቋንቋንና ጠንካራ አንድነት ያለው ሀገርን የሚያቀነቅን ሲሆን፤ የ‹ትግራይ አንብሮ› ደግሞ ሰፊ በሆነ የኢትዮጵያዊነት ማንነት ማዕቀፍ ውስጥ የአካባቢያዊ ራስ-ገዝነትን እና ታሪካዊ ፌደራሊዝምን የሚያጎላ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ይህ ንፅፅር እንደሚያመላክተው በትግራይ መሪዎችና በማዕከላዊው አገዛዝ መካከል የተከሰቱት አለመግባባቶች የሀገር መፍረስ ወይም የመገንጠል ጥያቄዎች ሳይሆኑ፣ ኢትዮጵያ በምን ዓይነት የፖለቲካና የአስተዳደር መዋቅር ላይ መገንባት አለባት በሚለው መሠረታዊ የፍልስፍና ልዩነት ላይ የተመሠረቱ ነበሩ፡፡
ኤርሊክ እንደሚለው የአማራ ንድፈ-ሐሳብ ሀገራዊ አንድነትንና ዘላቂ ሕልውናን ለማረጋገጥ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት፣ ወጥ ቢሮክራሲና አንድ የጋራ ባሕላዊና ቋንቋዊ መስተጋብር ያስፈልጋል ብሎ ያምናል (ገጽ 8)፡፡ ይህ መስመር ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ከዳግማዊ አጼ ምኒልክ የሥልጣን ዘመን አንስቶ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥታዊ ማዕከላዊነትና በኋላም በደርግ ወታደራዊ አገዛዝ በይፋ ተግባራዊ የተደረገ ዋና የሀገር ግንባታ ሞዴል ነበር፡፡
በተቃራኒው የትግራይ ንድፈ-ሐሳብ የኢትዮጵያን ታሪካዊና ማኅበራዊ እውነታ የሚረዳው ባልተማከለ ወይም ፌደራላዊ መሰል የሥልጣን ክፍፍል መርኅ ላይ ነው፡፡ በአጼ ዮሐንስ አራተኛ ዘመን ጉልህ ማሳያ ያገኘው ይህ መስመር፣ ንጉሠ ነገሥቱ የሀገሪቱን ውጫዊ ድንበርና የበላይነትን እየጠበቁ፣ የየአካባቢው ገዥዎች ግን በራሳቸው ግዛት ሙሉ ራስ-ገዝነት እንዲኖራቸው የሚፈቅድ የፖለቲካ ባሕል ነበር (ገጽ 29)፡፡ ይህ ንድፈ-ሐሳብ ኢትዮጵያ አክሱማዊና ሰሎሞናዊ መሠረት ያላትና ብዝኃ ባሕል ሀገር በመሆኗ፣ የማዕከላዊው መንግሥት ጫናና መገፋት ሲበዛ ይበልጥ አመጽንና የውስጥ ክፍፍልን ይጋብዛል እንጂ አንድነትን አያመጣም የሚል ጽኑ እምነት አለው፡፡
በእነዚህ ሁለቱ አንብሮዎች/ንድፈ-ሐሳቦች መካከል የነበረው ፍልሚያ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የታሪክ ሂደት ውስጥ እጅግ መራራ ዋጋ ያስከፈሉ ግጭቶችን ወልዷል፡፡ የሥልጣን ማዕከሉ ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ ሲዛወርና የሸዋው ማዕከላዊነት ሲነግሥ፣ የትግራይ መሪዎች የነበራቸውን ታሪካዊ ራስ-ገዝነት በማጣታቸው የገጠማቸው መገለል የቀዳማይ ወያኔ አመጽ እንዲፈነዳ ምክንያት ሆኗል (ገጽ 116)፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በ1960ዎቹና በ1970ዎቹ የአጼ ኃይለ ሥላሴና የደርግ ማዕከላዊ ጫና ይበልጥ ሲበረታ፣ የትግራይ አብዮታዊ ወጣቶች የትግራይን ታሪካዊ ንድፈ-ሐሳብ በማርክሲስታዊና በብሔር ፌደራሊዝም ርዕዮተ-ዓለም አድሰው ህወሓትን በመመሥረት ለ17 ዓመታት የትጥቅ ትግል እንዲያካሂዱ አድርጓቸዋል፡፡
በመጨረሻም የደርግ መውደቅን ተከትሎ ህወሓት አዲስ አበባን ሲቆጣጠር፣ ለዘመናት ተገፍቶ የነበረው የትግራይ ንድፈ-ሐሳብ በብሔር ፌደራሊዝምና በሕገ-መንግሥቱ አማካኝነት መጋረጃው ተገፎ እንዲነግሥ ተደረገ (ገጽ 155)፡፡ ሆኖም ኤርሊክ እንደሚሞግተው፣ የትኛውም መስመር የበላይነቱን በሚይዝበት ወቅት የሌላኛውን አመለካከት ሙሉ በሙሉ ለማጥፋትና የታሪክ ሚዛኑን ወደ አንዱ ወገን ብቻ ለማዘነበል በሚያደርገው ጥረት ምክንያት፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ውጥረት ዑደት ሳይቋጭ ከአንዱ ዘመን ወደ ሌላው ምዕራፍ እየተሸጋገረ ለመቀጠል በቃ፡፡
‹‹ምስጢራዊው ስበት›› – ትግራይን ከኢትዮጵያ የሚያስተሳስራት ረቂቅ ገመድ
የሐጋይ ኤርሊክ መጽሐፍ እጅግ በጥብቅ የሚያተኩርበትና የመጽሐፉ ማዕከላዊ ዓምድ የሆነው ሐሳብ ትግራይ ምንም እንኳን የታሪክ ውጣ ውረዶችን፣ የሥልጣን መገፋትንና የመገለል አጋጣሚዎችን ብታስተናግድም፣ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ሕልውናና ታሪካዊ መዋቅር ተነጥላ መኖር የማትችልበት ‹‹ምስጢራዊ ሀገራዊ ስበት›› (Mysterious Magnetism) እንዳላት የሚያስረዳው ክፍል ነው፡፡ ፀሐፊው ይህንን ረቂቅና የማይበጠስ የታሪክ ገመድ ሲያብራራ ከፍተኛ የማግለል፣ የውስጥ ግጭትና የውጭ ኃይሎች ሤራ በነበረባቸው የታሪክ አጋጣሚዎች ሳይቀር፣ የትግራይ መሪዎችና ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ከመበጠስ/ከመቆረጥ ከከለከላቸው ዘላቂ ‹ምስጢራዊ ስበት› ጋር—ከሰሎሞናዊው እሴትና ከሰፊው የኢትዮጵያ የታሪክ አደራ ጋር በጥብቅ የተሳሰሩ ሆነው መቅረታቸውን ያመላክታል (ገጽ 12-13)፡፡
ኤርሊክ እንደሚያብራራው፣ የትግርኛ ተናጋሪው ማኅበረሰብ ለኢትዮጵያ ሃገረ-መንግሥት መሠረት፣ ለቤተ-ክህነቱ ሥልጣኔ፣ ለግእዝ ቋንቋና ለሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥት ንድፈ-ሐሳብ ዋና ምንጭ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያዊነትን እንደ ውጫዊ አገዛዝ ወይም እንደ እንግዳ ማንነት አያየውም (ገጽ 10)፡፡ ይልቁንም ትግራውያን ሀገሪቱንና ታሪኳን የራሳቸው ጥንታዊ ቅርስና የእጃቸው ሥራ ውጤት አድርገው ስለሚቆጥሩ፣ በማዕከላዊው መንግሥት ላይ የሚያነሱት ተቃውሞ ሀገርን የመካድ ጥያቄ ሳይሆን የባለቤትነትና የፍትሐዊ ድርሻ ጥያቄ ነው፡፡ በሌላ አባባል፣ ለትግራውያን ኢትዮጵያ በላያቸው ላይ የተጫነች እንግዳ ፍጥረት ሳትሆን የራሳቸው ታሪካዊ የእጅ ሥራ ናት፤ ስለዚህ የፖለቲካ ትግላቸው በታሪክ ሂደት በነበረው የሥልጣን ማዕከሉ ባሕሪ ላይ እንጂ የኢትዮጵያዊነትን ማዕቀፍ ሙሉ በሙሉ በመተው ላይ አልነበረም፡፡
ይህ ‹ምስጢራዊ ስበት› ይበልጥ ጎልቶ የወጣው ሀገሪቱ በውጫዊ ወራሪዎችና የቅኝ ግዛት ሥጋቶች በተፈተነችባቸው የታሪክ አጋጣሚዎች ወቅት ነው፡፡ ለምሳሌ በ16ኛው ክፍለዘመን ግራኝ አሕመድ ማዕከላዊውንና ደቡባዊውን ኢትዮጵያ ተቆጣጥሮ የሰሎሞናዊውን መንግሥት ለውድቀት ባቀረበበት ወቅት፣ ባሕረ ነጋሽ ይስሐቅ የውጪውን በር ክፍት በማድረግ ከፖርቱጋል መንግሥት የተላኩትን 400 ወታደሮችና ዘመናዊ የጦር መሣርያዎች በምጽዋ በኩል ተቀብሎና የገዛ ሰራዊቱንም ቀላቅሎ የክርስቲያኑ መንግሥት ከውድቀት እንዲድን የሞት ሽረት ተጋድሎ አድርጓል (ገጽ 15)፡፡
በዓድዋ ጦርነት ዋዜማም እንዲሁ በትግራይ መሳፍንት (እንደ ራስ መንገሻ ዮሐንስ) እና በሸዋው ንጉሥ አጼ ምኒልክ መካከል የከረረ የሥልጣን ሽኩቻ የነበረ ቢሆንም፣ የኢጣሊያ ወረራ አደጋ ሲደቀን ግን የትግራይ መሪዎችና ሕዝብ ውስጣዊ ቅሬታቸውን ወደ ጎን በመተው ለመላው ሀገር ሕልውና ሲሉ በግንባር ቀደምነት ተሰልፈው መስዋዕትነት ከፍለዋል (ገጽ 66)፡፡ የኢጣሊያ ቅኝ ግዛት የሀገር ሕልውናን የመፈታተን አደጋ በደቀነበት ወቅት፣ የውስጥ የሥልጣን ፉክክሮች ከኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ጥሪ ፊት ከሰሙ፤ ይህም ታሪካዊው ስበት ከአካባቢያዊ ቅራኔዎች የበለጠ ጠንካራ መሆኑን አስመስክሯል፡፡
በተጨማሪም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ፋሺስት ኢጣሊያና በኋላም የብሪታንያ ወታደራዊ አስተዳደር ኤርትራንና ትግራይን በመቀላቀል የ‹‹ታላቋ ትግራይ›› ፕሮጀክት በመቅረጽ ሰሜኑን ክፍል ከኢትዮጵያ ማዕከል የመነጠል የጂኦ-ፖለቲካዊ ሤራ ሲሸርቡ፣ ይህ ምስጢራዊ ስበት የውጭ ኃይሎችን እቅድ ማክሸፉን ፀሐፊው ያወሳል (ገጽ 61)፡፡ የውጭ ኃይሎች ትግራይ ከአዲስ አበባ ጋር የነበራትን የፖለቲካ ቅሬታ በቀላሉ ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ወደ መካድ መቀየር ይቻላል ብለው በማሰባቸው ‹‹ሁልጊዜም የታሪክ ስሕተት ይፈጽሙ ነበር›› ይላል ኤርሊክ በትንታኔው፡፡
በዘመናዊው የታሪክ ምዕራፍም ቢሆን፣ ከተካሄዱት የድንበር ግጭቶች ጀምሮ እስከ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ድረስ ባሉት ሂደቶች የትግራይ መሪዎችና ሕዝብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አህጉራዊ ታላቅነት ለማስከበር ያሳዩት ተሳትፎ የዚሁ ረቂቅ ስበት ዘመናዊ ማሳያ መሆኑን ኤርሊክ ያብራራል፡፡ የፖለቲካ ክፍፍሉና የብሔር ፌደራሊዝሙ ቢበረታም፣ ‹‹ኢትዮጵያዊነት አይቀሬ የጋራ ማደሪያ ነው›› የሚለው ነባር እሳቤ በትግራይ የፖለቲካ ንቃተ-ሕሊና ላይ የነበረው ረቂቅ ግን ደግሞ ጽኑ ማግኔታዊ ስበት አልተሸረሸረም፡፡
የውጭ ኃይሎች ሤራ፣ ኤርትራና የ‹‹ታላቋ ትግራይ›› ድንበር
የሐጋይ ኤርሊክ መጽሐፍ በጥልቀት ከሚዳስሳቸው የታሪክ ዐውዶች መካከል አንዱ የውጭ ኃይሎች (በዋናነት ፋሺስት ኢጣሊያና የብሪታንያ ወታደራዊ አስተዳደር) በሰሜን ኢትዮጵያና በቀይ ባሕር አካባቢ ያካሄዱት ጂኦ-ፖለቲካዊ ሤራና የ‹‹ታላቋ ትግራይ›› (Greater Tigray) ጽንሰ-ሐሳብ አመጣጥ ነው፡፡
ኤርሊክ እንደሚተነትነው፣ የውጭ አገዛዞች የሰሜኑን ትግርኛ ተናጋሪ ማኅበረሰብ (የኤርትራን ደጋማ ክፍልና የትግራይን) ከአዲስ አበባ ማዕከላዊ አገዛዝ በመነጠል የራሳቸውን የቅኝ ግዛትና የወታደራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ስትራቴጂያዊ እርምጃዎችን ወስደዋል (ገጽ 96 እና 97)፡፡ በአሥመራ አስተዳደር ሥር የሚሆን የ‹ታላቋ ትግራይ›ን ጽንሰ-ሐሳብ በመጠቀም የሰሜኑን ትግርኛ ተናጋሪዎች ከኢትዮጵያ ማዕከል ለመነጠል የተወጠኑት እነኚህ የኢጣሊያና የብሪታንያ እቅዶች፣ በስተመጨረሻ ከኢትዮጵያዊነት የታሪክ ንቃተ-ሕሊና ግንብ ጋር ተጋጭተው ተንኮታኩተዋል፡፡
በ1930ዎቹ መጀመሪያ ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረች በኋላ፣ በመሠረተችው አዲስ አስተዳደራዊ መዋቅር ትግራይን ከአዲስ አበባ ቁጥጥር ነጥላ በአስመራ አስተዳደር ሥር እንዲጠቃለል አደረገች፡፡ ጣሊያኖች በትግራይና በኤርትራ ትግርኛ ቋንቋን፣ ባሕልንና የአካባቢ ማንነትን በማጎልበት የቋንቋው ተናጋሪዎችን ከኢትዮጵያ ማዕከላዊ ማንነት ለመነጠል የሞከሩ ሲሆን፣ ይህም በውጭ ኃይሎች የተቀረጸ የመጀመሪያው የ‹‹ታላቋ ትግራይ›› ፕሮጀክት ነበር፡፡ ፋሺስት ኢጣሊያ ትግራይን ከኤርትራ ጋር በማቀላቀል የትግራይን አካባቢያዊ ማንነት ለራሱ ዓላማ ለመጠቀም የሞከረበት ዋና ምክንያት፣ በአሥመራ ሥር የሚመራ አንድ የትግርኛ ተናጋሪ አካል መፍጠር ከኢትዮጵያን ንጉሠ ነገሥታዊ መንግሥት ጋር የነበረውን ታሪካዊ አንድነት መስበር ይቻላል በሚል እምነት ነበር፡፡
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ኢጣሊያ ስትሸነፍ፣ ኤርትራን በጊዜያዊነት የተቆጣጠረው የብሪታንያ ወታደራዊ አስተዳደርም ተመሳሳይ የጂኦ-ፖለቲካዊ ካርታ ለመሳል ሞክሮ ነበር (ገጽ 100)፡፡ የብሪታንያ መኮንኖች የኤርትራን ደጋማ ክፍልና የትግራይን ክፍለ ሀገር በማቀላቀል በብሪታንያ ሞግዚትነት የምትመራ ‹‹ታላቋ ትግራይ›› የመመስረት ሐሳብ በይፋ ያቀረቡ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ የትግራይ መሪዎችም (እንደ ራስ ሥዩም መንገሻ ያሉት) ይህን መደራደሪያ የትግራይን ታሪካዊ ራስ-ገዝነት ለማስመለስ እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ሞክረው ነበር (ገጽ 104)፡፡ የብሪታንያ መኮንኖች የኤርትራን ጥያቄ ለመፍታት የ‹ትግራውያን ሕብረት› በሚለው ሐሳብ ላይ ተዋሥዖ ቢከፍቱም፣ ትግራይን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር አጣብቀው የያዙትን ጥልቅ መዋቅራዊ ትስስሮች በወጉ መገንዘብ ግን አልቻሉም ነበር፡፡
በዚህም ሳቢያ፣ ብዙ የተለፋበትና የውጭ ኃይሎች ውጥን የኾነው የ‹‹ታላቋ ትግራይ›› ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ የከሸፈ ሲሆን፣ ውጤቱ እንዲያውም ትግራይን ከማጣት ሥጋት ተሻግሮ በቅኝ ግዛት የተነጠለችው መላዋ ኤርትራንም በፌደሬሽን ወደ ኢትዮጵያ እንድትመለስ አደረገ፡፡ ሆኖም ኤርሊክ እንደሚያሰምርበት፣ ኤርትራ በቅኝ ግዛት የታሪክ ዳራዋ ምክንያት ራሷን የመነጠል መንገድ መከተሏና በኋላም ነፃ ሀገር ሆና መውጣቷ፣ ትግራይ ደግሞ ከባሕር በር ተቆርጣ የብስ ላይ ተቆልፋ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀር መደረጉ በትግርኛ ተናጋሪ ማኅበረሰብ ዘንድ ዘላቂ የሆነ የታሪክ ቁስልና የፖለቲካ ፍጥጫ ጥሎ አልፏል፡፡ ምንም እንኳን የውጭ ኃይሎች የ‹ታላቋ ትግራይ› ፕሮጀክት ወደ ሉዓላዊ ሀገርነት ባይቀየርም፣ በተቃራኒው የትግርኛ ተናጋሪውን ማኅበረሰብ የመከፋፈሉ ፖለቲካዊና ሥነ-ልቦናዊ ውጤት ግን በምስራቅ አፍሪካ ጂኦ-ፖለቲካ ላይ ዘላቂ አሻራውን አስቀምጦ አልፏል፡፡
ከቀዳማይ ወያኔ እስከ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ
የሐጋይ ኤርሊክ መጽሐፍ የትግራይንና የኢትዮጵያን ዘመናዊ የታሪክ ሂደት ሲተነትን፣ ከ1930ዎቹ መገባደጃና 1940ዎቹ የቀዳማይ ወያኔ አመጽ ጀምሮ እስከ 21ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎቹ ዐሠርት ዓመታትና እስከ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ያሉትን ቁልፍ ምዕራፎች በስፋት ይዳስሳል፡፡ ፀሐፊው እንደሚሞግተው፣ በ1936 ዓ.ም የተከሰተው የቀዳማይ ወያኔ አመጽ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥታዊ ማዕከላዊነትና የግብር ጭቆና ላይ የተነሳ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ነበር፡፡ ይሁንና ይህ አመጽ በማዕከላዊው መንግሥትና በብሪታንያ የአየር ኃይል ድጋፍ በቦምብ ድብደባ ከከሸፈ በኋላ፣ የትግራይ ማኅበረሰብ ለበርካታ ዐሠርት ዓመታት በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ገለልተኝነት ውስጥ እንዲቆይ ተደረገ (ገጽ 110)፡፡ የቀዳማይ ወያኔ አመጽ መክሸፍ የአዲስ አበባን ማዕከላዊነት ያጠናከረ ቢሆንም፣ ከበርካታ ዐሠርት ዓመታት በኋላ ይበልጥ በጠነከረ የፖለቲካና ወታደራዊ መዋቅር ተመልሶ የሚመጣውን የዳግማይ ወያኔ ንቅናቄ እርሾ ትቶ ነበር፡፡
በ1966 ዓ.ም የንጉሠ ነገሥቱ ሥርዓት መውደቅና የወታደራዊው ደርግ ወደ ሥልጣን መምጣት፣ በትግራይ አብዮታዊ ወጣቶች ዘንድ አዲስ የትግል ምዕራፍ እንዲከፈት ምክንያት ሆነ (ገጽ 137)፡፡ በ1967 ዓ.ም የተመሠረተው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ግንባር (ህወሓት)፣ የቀዳማይ ወያኔን ታሪካዊ ቅሬታ በማርክሲስታዊ-ሌኒኒስታዊ የአደረጃጀት ስልትና በብሔር ፌደራሊዝም ርዕዮተ-ዓለም በማጠናከር መራራ የ17 ዓመታት የትጥቅ ትግል አካሄደ፡፡ ህወሓት በ1983 ዓ.ም በደርግ ላይ የተቀዳጀው ድል ወታደራዊ የበላይነት ብቻ አልነበረም፤ ይልቁንም ነባሩ የትግራይ ንድፈ-ሐሳብ/አንብሮ እውን መሆን ማለትም ኢትዮጵያን ከማዕከላዊ ንጉሠ ነገሥትነት ወደ ብሔሮች ፌደሬሽን የመቀየር የታሪክ ሂደት ነበር፡፡ ህወሓት መራሹ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ፣ በ1987ቱ ሕገ-መንግሥት አማካኝነት የብሔር ፌደራሊዝም ሥርዓት በመዘርጋት የትግራይ የፖለቲካ መስመር በሀገራዊ ደረጃ የበላይነቱን እንዲይዝ አደረገ (ገጽ 155)፡፡
በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የተከሰተው የኢትዮ-ኤርትራ የባድመ ጦርነት በትግራይ መሪዎችና በኤርትራ መንግሥት መካከል የነበረውን የታሪክና የፖለቲካ ቁስል በግልጽ ያወጣ አጋጣሚ ነበር፡፡ ኤርሊክ እንደሚገልጸው፣ ይህ ጦርነት የትግራይ መሪዎች ከኤርትራ ነፃ መውጣት በኋላ ከኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ጋር የነበራቸውን ትስስር ይበልጥ ያጠናከሩበትና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት የመጠበቅ ታሪካዊ አደራቸውን በይፋ ያረጋገጡበት አጋጣሚ ሆኗል፡፡ የድንበር ጦርነቱ በህወሓትና በሕዝባዊ ግንባር መካከል የነበረውን ወንድማማችነት በጥብቅ የበጠሰ ሲሆን፣ የትግራይ ልሂቃን የጂኦ-ፖለቲካ ማንነታቸውን ከኢትዮጵያ መንግሥት ሕልውናና መከላከል ጋር ሙሉ በሙሉ እንዲያዋሕዱም ያስገደደ ነበር፡፡
ከባድመ ጦርነት ማብቃት በኋላ፣ የትግራይ መሪዎች የሀገሪቱን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተሐድሶ ለመምራት ያደረጉት ጥረት ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግዙፍ የሃይድሮ-ኤሌክትሪክ ፕሮጀክት ብቻ ሆኖ ሳይሆን የተከሰተው፣ በብሔር የተከፋፈለችን ሀገር በጋራ የታሪክ ታላቅነት ዙሪያ በመሰብሰብ የትግራውያን ምስጢራዊ ኢትዮጵያዊ ስበት የዘመናዊው ታሪክ የመጨረሻ ማሳያ ሆኖ በመውጣቱ ነው (ገጽ 175)፡፡
በኤርሊክ ትንታኔ፣ የሕዳሴው ግድብ ግንባታ፣ ትግራይ በኢትዮጵያ ሃገረ-መንግሥት ግንባታና በዓባይ ውሃ ሉዓላዊነት ላይ ያሳረፈችው ታላቅ ዘመናዊ አሻራን የሚያሳይ ነው፡፡ ግድቡ በብሔር ፖለቲካ ተከፋፍላ የነበረችውን ሀገር በአንድ የጋራ የልማትና የሉዓላዊነት ርዕይ ሥር እንዲሰባሰቡ በማድረግ፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ማግኔትና ታሪካዊ ሕልውና በ21ኛው ክፍለ ዘመንም ቢሆን በአዲስ መንገድ ለመገለጥ መቻሉን የሚያስረዳ ኾኖ አገልግሏል፡፡
የመጽሐፉ ፍጻሜ
ሐጋይ ኤርሊክ መጽሐፉን የሚያጠናቅቀው ‹‹Non-conclusion›› (ያልተቋጨ) ባለው ምዕራፍ ነው፡፡ ይህም የኢትዮጵያና የትግራይ የታሪክ ጉዞ ገና ያልተጠናቀቀ፣ ወደፊትም የሚቀጥልና ሕያው ሀገራዊና አህጉራዊ እውነታ መሆኑን የሚያወሳ ነው፡፡ በዚህ ያልተጠናቀቀ የታሪክ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያ በሁለት ተቃራኒ ኃይሎች መካከል ባለው ቀጭንና ረቂቅ ሚዛን ላይ ትጓዛለች ይለናል፡፡ በአንድ በኩል በብሔር ፖለቲካ፣ በልሂቃን ፍጥጫና መከፋፈል የሚገለጸው ሀገሪቱን ወደ ፍርሰት ሊወስድ የሚችለው ‹የብተና ንድፈ-ሐሳብ› ሥጋት ሲደቀን፤ በሌላ በኩል ደግሞ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ፣ በታሪካዊ የጋራ አደራና በጠንካራው ሀገራዊ ማንነት በተወከለው ‹ምስጢራዊ ስበት (ማግኔት)› መካከል ያለው ፍልሚያ ቀጣይ ሕልውናዋን ይወስነዋል ሲል ያስቀምጣል፡፡
ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 237 ጥቅምት 2019 ዓ.ም
