የኢትዮጵያ የአጥንት ሕክምና ሐኪሞች ማኅበር 19ኛውን ዓመታዊ ጉባኤ እና የሁለት ቀናት አውደ ርዕይ ዛሬ ሕዳር 13 ቀን 2019 ዓ.ም. አጠናቋል። ጉባኤው የአጥንት ቀዶ ሕክምናን ማዘመንና በጤናው ዘርፍ ያለውን ትብብር ማጠናከር በሚል መሪ ሐሳብ ተካሂዷል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ ለረጅም ዓመታት በዘርፉ አገልግሎት ለሰጡ ሁለት ሐኪሞችና አንድ ተቋም እውቅና ተሰጥቷል። በደሴና አካባቢው ለ35 ዓመታት ብቸኛ የአጥንት ሐኪም ሆነው ያገለገሉት ዶክተር ዘላለም ታምራት፣ በምሥራቅ ሐረርጌ ለረጅም ጊዜ ያገለገሉትና በአካባቢው ቋንቋ የአጥንት ሕክምና መጽሐፍ ያዘጋጁት ዶክተር ማንያዘዋል ደሴ ተሸልመዋል። በየዓመቱ ከ3 ሺህ በላይ ሕፃናትን በነጻ የሚያክመው ኪዩር ኢትዮጵያ የሕፃናት ሆስፒታልም እውቅና አግኝቷል።
የማኅበሩ አመራሮች እንዳሉት፣ ከ10 እና 11 ዓመታት በፊት የአጥንት ሕክምና ማሠልጠኛ ተቋም ጥቁር አንበሳ ብቻ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ቁጥራቸው 13 ደርሷል። በወቅቱ 50 ያህል የነበሩ የአጥንትና መገጣጠሚያ ሐኪሞችም ከ600 እስከ 700 ደርሰዋል። በየዓመቱ ከ100 በላይ ሠልጣኞች ወደ ስፔሻላይዜሽን የሚገቡ ቢሆንም፣ ከ132 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ላላት ኢትዮጵያ ይህ ቁጥር በቂ አለመሆኑን ገልጸዋል።
ባለሙያዎችን ከማሠልጠን በተጨማሪ በሀገር ውስጥ ማቆየት ትልቅ ፈተና መሆኑን ጠቁመዋል። የሥራ ቦታ፣ የበጀትና ማራኪ የሥራ ሁኔታዎች እጥረት ሐኪሞች ወደ ውጭ ሀገራት እንዲሄዱ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ናቸው። የሕክምና መሣሪያዎችን ከውጭ ማስገባትና የጤና መድን የአጥንት ቀዶ ሕክምናዎችን በበቂ ሁኔታ አለመሸፈንም ተጨማሪ ተግዳሮቶች ናቸው።
ማኅበሩ የባህላዊ አጥንት ሕክምና ባለሙያዎችን ከሥራ ማስወጣት ዓላማው እንዳልሆነ ገልጾ፣ በሕክምናው ሊያስከትላቸው በሚችሉ ጉዳቶች ላይ ጥናትና ሥልጠና እየሰጠ መሆኑን አስታውቋል። የወጌሻዎችን የሥራ ወሰን ለመለየትና የቁጥጥር ሥርዓት ለማበጀትም ከጤና ሚኒስቴር ጋር እየተወያየ ነው።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የውጭ ሀገራት ዜጎችን በአጥንት ሕክምና ማሠልጠኗ የዲፕሎማሲ ስኬት መሆኑን ገልጿል። በደቡብ ሱዳን ከሚገኙ 11 ያህል የአጥንት ሐኪሞች ሦስቱ በኢትዮጵያ የሰለጠኑ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት 13 ሩዋንዳውያን ሠልጣኞችም ተቀብላለች።
