
በታደሰ ብሩ ኬርስሞ (ዶ/ር)
በግጭት በሚታመስ ማኅበረሰብ ውስጥ ወንዶችን እና ወጣቶችን የግጭት ጠማቂዎች፣ ልጃገረዶችን እና ወጣት ሴቶችን ደግሞ ሰለባዎች አድርጎ መመልከት ተለምዷዊ እውነታ ነው። ይህ እምነት በተጨባጭ ማሳያዎች ሳይቀር ሊደገፍ የሚችል ነው። ምንም እንኳን አስተማማኝ የስታቲስቲክስ መረጃ ማግኘት ቀላል ባይሆንም የኢትዮጵያ ወጣቶች [በተፈጠሩትና እየተፈጠሩ ባሉት] ግጭቶች ተጎጂ ከኾኑት የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል ግንባር ቀደም እንደኾኑ መገመት ይቻላል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በአንድ በኩል መደበኛ እና መደበኛ ባልሆኑ አደረጃጀቶች ወጣት ወንዶችን ለእኩይ ዓላማ የማሰለፍ ጉዳይ በመኖሩ ነው። በሕዳር 2020 በማይካድራ “ሳምሪ” በመባል በሚታወቁ ወጣቶች የተፈጸመው ፍጅት ለዚህ ጉልህ ማሳያ ይኾናል። ወደኋላ አለፍ ካልንም ከዓመት በፊት በሻሸመኔ ከተማ የደረሰው ጥፋት በተመሳሳይ መልኩ በወጣት ወንዶች የተፈጸመ እንደነበር ማስታወስ ይቻላል።
በሌላ በኩል ስንመለከተው ደግሞ፣ ልጃገረዶች እና ወጣት ሴቶች በእነኚህ ግጭቶችና ጥፋቶች በመቶኛ ሲሰላ ከፍተኛውን የሰለባነት ደረጃ እንደያዙ መገንዘብ እንችላለን። በኢትዮጵያ የተፈናቃዮች ቁጥር አብዛኞቹ ወጣቶችና ሕፃናት መኾናቸው፣ በመንግሥት እና በአብዛኛዎቹ የሲቪክ ድርጅቶች ዘንድ በድህረ ግጭቶቹ ሰብዓዊ ተግባራት ላይ የተረባረቡበትን አመክንዮ ግልጽ ያደርገዋል። “በርካታ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት ከኾነ የዜጎችን ደህንነት በማረጋገጥ ረገድ ወጣቱ የሰላም ግንባታ ሂደት ተሳታፊ እንዲኾን የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት መሠራት አለበት”፡፡
ኢትዮጵያ ሰፊ የወጣት ሕብረተሰብ ክፍል ያላት ሀገር ናት። ከ15 እስከ 29 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘውን የሕብረተሰብ ክፍል “ወጣት” አድርገን የምንይዘው ከሆነ 28.4 በመቶ ገደማ የሚሆነው ሕዝብ ወይም በግምት 32 ሚሊዮን የሚኾኑ ዜጎች ወጣት ኾነው እናገኛቸዋለን። አብዛኛው የኢትዮጵያ ወጣት (81.4 በመቶ ገደማው) በገጠር የሚኖር ሲሆን ቀሪው 18.6 በመቶው ደግሞ የከተማ ነዋሪ ነው። በመቶኛ ሲታይ በአንጻራዊነት አነስተኛ ቢመስልም፣ የኢትዮጵያ የከተማ ወጣቶች በተለይም ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሀገሪቱን ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ለውጥ (dynamics) በመቅረፅ ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል። የኢትዮጵያ ተማሪዎች ከ1960 ዎቹ መጀመሪያ አንስቶም በኢትዮጵያ የማይናቅ የፖለቲካ ኃይል ነበሩ።
በንጉሠ ነገሥቱ፣ በወታደራዊ አስተዳደር እና በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥታት ሥር ነቀል የፖለቲካ ለውጦችን ለማድረግም ወጣቶች ፈር ቀዳጅ ነበሩ። የዘመናችን ወጣቶችም ኢሕአዴግ በግማሽ የጋገረውን “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ከምጣዱ እንዲያነሳ በማስገደድ ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል። እነኚህ መደበኛ ያልሆኑ የወጣቶች እንቅስቃሴዎች (ቄሮ፣ ፋኖ፣ ኤጄቶ፣ ዘርማ…) ከ2015 – 2018 በኢሕአዴግ መንግሥት ላይ ለዘለቀው ተቃውሞ እና ሕዝባዊ እምቢተኝነት ወሳኝ ኃይል ኾነው በመውጣታቸው የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሊመጡ ችለዋል።
እዚህ ጋር የፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ ወጣት ወንዶችና ሴቶች መኾናቸውን ማወቅ ጠቃሚ ነው። ምናልባትም ይኽ የወጣቶች ጣምራ ሚና የኢትዮጵያ መንግሥት ወጣቶችን የመንግሥት ደህንነት ሥጋትም ዋስትናም አድርጎ እንዲመለከት ምክንያት ኾኖት ሊሆን ይችላል። ይህ ጣምራ ባለሚናነት ሰፋ ያለ አንድምታ እንዳለው የ2004ቱ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ብሔራዊ የወጣቶች ፖሊሲ እና የእርግዝና ቁጥጥር አዋጅ (VCP) (384/2004) የፖሊሲ ሰነዶች ማሳያ ሊኾኑ ይችላሉ።
ብዝኃ ወጣት (Youth Bulge)
“ብዝኃ ወጣት” (Youth Bulge) በሕዝብ ምጣኔ ፒራሚድ ውስጥ ከፍተኛ የወጣት መቶኛ ቁጥርን የሚወክል ንባበቃል ነው። ሶሲዮሎጂስት ጉናር ሄይንሶን የወጣቶች መበራከት ፣ በተለይም የወጣት ጎልማሳ ወንዶች ቁጥር ከመጠን በላይ መብዛት ወደ ማህበራዊ አለመረጋጋት፣ ጦርነት እና ሽብርተኝነት ሊያመራ ይችላል ብሎ ይከራከራል። እንደ ሂንሶን ፣ ጋሪ ፉለር እና ጃክ ኤ ጎልድስቶን ፣ ሊዮኔል ቢነር እና ሌሎች ማኅበራዊ የሥነ ሰብዕ (አንትሮፖሎጂ) ባለሙያዎች ዕምነት ደግሞ በፍጥነት እያደጉ ያሉ ወጣት ሕዝቦች ያሏቸው ሀገሮች ሥራ አጥ የሚኾኑበት ዕድል ከሰፋ ወደ አመፅ አልያም ለአሸባሪ ቡድኖች ምልምል የመኾን ዕድላቸው ሰፊ ነው። የ1930ዎቹ ታላቁ የኢኮኖሚ ድቀት፣ የ2000ዎቹ የምጣኔ ሃብት ውድቀት፣ የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ፋሺዝም፣ የ2010ሩ የዐረቡ ዓለም አብዮቶች እና ሌሎችም እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች እና ሽብርተኝነቶች ከወጣቶች ቁጥር መብዛት ጋር የተቆራኙ ናቸው ብለው ይከራከራሉ። ደካማ የፖለቲካ ተቋማት ያሏቸው አገሮች፣ ከወጣቶች ጋር ተያይዞ ለሚመጣ አመጽ እና ማኅበራዊ አለመረጋጋት በጣም ተጋላጭ ናቸው ሲሉም ያስጠነቅቃሉ።
ሆኖም ከላይ የተጠቀሱት የማኅበራዊ ሳይንስ ምሑራን የወጣት ሕብረተሰብ ቁጥር መብዛት በመጥፎ ገጽታው ብቻ የሚገለጽ አለመሆኑንም ያስረዳሉ። ለወጣቶች ተስማሚ ፖሊሲዎች እና አሰራሮች ተግባራዊ ከሆኑ ከወጣት ቁጥር መብዛት ጋር ተያይዞ የሚመጣው ሥጋት ወደ “ሥነ ሕዝብ ምጥጥን” (demographic dividend) ዕድልነት ሊለወጥ ይችላል። በፍጥነት በማደግ ላይ ባሉ የምሥራቅ እስያ አገሮች ውስጥ እንደታየው በርካታ በሥነ ምግባር ተገርቶ እና በሙያ ሰልጥኖ በኢኮኖሚው መስክ የሚሳተፍ የማኅበረሰብ ክፍል የሀገሪቱን ምጣኔ ሃብት ሊያሳድግ ይችላል። የኢትዮጵያ ወጣቶች መበራከትም የተቀናጀ ጥረት ቢደረግ ከችግር ይልቅ ወደ ዕድሉ የሚያመዝነው ለዚህ ነው። ለወጣቶች ተስማሚ በሆኑ ቴክኖሎጂዎች ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ፣ የተለያዩ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር፣ የቤተሰብ ዕቅድ ትግበራዎች ተደራሽነትን ማሻሻል እንዲሁም የሕፃናትን ሞት መጠን መቀነስ ደግሞ ለዚህ መሠረታዊ የፖሊሲ ማዕቀፎች ናቸው።
ከላይ የተጠቀሰው ማሳሰቢያ እንዳለ ኾኖ፣ የ“ብዝኃ ወጣት” (youth bulge) ጽንሠ ሀሳብ ወጣቱን በአንድ በኩል እንደ አሉታዊ ኃይል በሌላ በኩል ደግሞ “በዕድሜ ከፍ ባለው ክፍል መመራት ያለበት” የማኅበረሰብ ክፍል አድርጎ ከማቅረቡ የተነሳ ወጣቱ ሕዝብን (ሀገርን) በሚመለከቱ ጥቅል ጉዳዮች በንቃት የመሳተፍ መብቱን አያበረታታም።
ወጣት፣ ሰላም እና ደህንነት
ወጣቱን ሰላም ፈላጊ አድርጎ ከማሰብ ይልቅ ችግር ፈጣሪ አድርጎ የመቁጠር ዕሳቤ መኖሩ በዕድሜ ከፍ ያሉት የሕብረተሰብ ክፍሎች (elders) የሰላም ግንባታ ሂደቱን እንዲንዲመሩ ምክንያት ኾኗል። ሆኖም የሰላሙ ባለቤትና ዋና ተዋናይ የኾነው ወጣቱ ትርጉም ባለው መንገድ ተሳታፊ እስካልኾነ ድረስ በአዛውንቶች ጥረት ብቻ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ሰላም መፍጠር አይቻልም። ለዚህ ደግሞ በተለምዶ ሸኔ ተብሎ ከሚጠራው የኦሮሚያ ነፃ አውጪ ጦር (OLA) ጋር በአባገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች የተደረጉት በርካታ ያልተሳኩ ድርድሮች በምሳሌነት ሊነሱ ይችላሉ። በትግራይ ባለው ሁኔታም ያለ ወጣቶች ንቁ ተሳትፎ ክልሉን ማረጋጋት በጣም ከባድ ነው። በኢትዮጵያ ለወጣቶች ያለውን አሉታዊ አመለካከት በመለወጥ እና በሁሉም የሰላም ግንባታ እና የዜጎች ደህንነት ማረጋገጫ ሂደቶች በንቃት የማሳተፊያው ጊዜ አሁን መኾን ያለበትም ለዚህ ነው።
ወጣትን ለሰላምና ደህንነት የማሳተፍ ዕሳቤ ለአካዳሚው ዓለም፣ ለተባበሩት መንግሥታት እና ለሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አዲስ አይደለም። የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በታህሳስ 2015 ውሳኔ ቁጥር 2250 ግጭትን በመከላከል እና ደህንነትን በማረጋገጥ ረገድ የወጣቱ አቅም ትልቅ እንደኾነ በማያሻማ ሁኔታ ገልጹዋል። ይኽ የተመድ ውሳኔ እንደተለመደው ወጣት ወንዶችን “በጠመንጃ ነካሽነት” ሴቶችን ደግሞ “በሰለባነት” ጠቅሰው የተቹትን ባያጣም ወጣቶች ግጭቶችን በመፍታት እና በመከላከል ረገድ ያላቸውን አቅም ግን በሚገባ አስተዋውቋል። የውሳኔ ሃሳቡ አባል አገራት እና ሲቪክ አደረጃጀቶች ወጣቶች በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ የሚጫወቱትን ወሳኝ ሚና እውቅና ሰጥተው እንዲደግፉም አሳስቧል።
መደረግ ያለበት
የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ 2250፣ የወጣቶችን የሰላምና ደህንነት ተሳትፎ ለማሳደግ ምን መደረግ እንዳለበት መመሪያ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ሃሳብ አስቀምጧል። በዚህ መሠረትም የፌዴራል፣ የክልል መንግሥታት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሚከተሉትን ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው ፡-
- ግጭቶችን እና ጽንፈኝነቶችን ለመከላከል እና የሰላም ግንባታን ለማሳለጥ ወጣቶች በአካባቢያዊ አስተዳደሮች፣ በክልል እና በፌዴራል የሥልጣን እርከኖች የውሳኔ ሰጪነት ተሳትፏቸውን ማሳደግ፣
- ግጭት ባለባቸው እና ግጭት በተፈጸመባቸው ቦታዎች የወጣቶችን እና የንጹሐንን ሕይወት ጥበቃ ማረጋገጥ ፤ በተጨማሪም በዘውግ፣ በሃይማኖት፣ በአመለካከት፣ በቆዳ ቀለም፣ በጾታ፣ በጤና ወይም በአካል ጉዳት ላይ የተመሠረቱ ማናቸውንም የመድልዎ ዓይነቶች ማስወገድ ፤
- ወጣቶች በራሳቸው ሁከትና ነውጥን ለመከላከል እንዲሁም የሰላም ግንባታ እንቅስቃሴዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር መደገፍ ፤
- ጽንፈኝነትን በመከላከል እና በማኅበራዊ ትስስሮች ውስጥ በቅንጅት በማሳተፍ ከሚመለከታቸው ሌሎች ተዋናዮች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር ፣ እንዲሁም
- የሥራ ዕድሎችንና ትምህርትን በመፍጠር፣ የአቅም ግንባታን ሥልጠናን በመሥጠት የወጣቶችን ሕልምና ርዕይ ለመደገፍ የሚቻለውን ሁሉ በማድረግ ከአመጻ ተግባራት እንዲርቁ ማድረግ ናቸው።
ሰላምን እና ደህንነትን በሚመለከት በወጣቶች ላይ የአመለካከት እና የአሠራር ለውጥ ማምጣት፣ የኢትዮጵያን የሰላም ግንባታ ሂደት ላይ ቀልጣፋ፣ ውጤታማ እና ዘላቂነት በማድረግ ረገድ ሰፊ አዎንታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ለዚህ ደግሞ ወጣቱ በሁሉም የሰላም ግንባታ ሂደቶች እና የዜጎችን ደህንነት በሚያረጋግጡ እንቅስቃሴዎች በንቃት መሳተፍ አለበት ፤ ከግጭቶች እና ከጽንፈኝነት ተግባራት መጠበቅ አለበት። የኢትዮጵያን ወጣቶች በሰላምና ደህንነት ውስጥ ያላቸውን ሚና በማጠናከር ረገድ ደግሞ ሁሉም የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በትብብር መሥራት ይኖርባቸዋል። ለዚህ እንዲረዳም ወጣቶችን ከአመፅ ተግባራት ለማራቅ ሥልጠናዎች ከመሥጠት ጀምሮ የሲቪክ ተሳትፎ መርሃ ግብሮችን መተግበር አስፈላጊ ነው።
————–
ታደሰ ብሩ ኬርስሞ (ዶ/ር) በወጣቶችና ባሕል ልማት ፋውንዴሽን (YCDF) የሰላምና የግጭት ጥናቶች ባለሙያ ናቸው። ሀሳብና አስተያየቶን በ ycdfoundationethiopia@gmail.com ወይም tkersmo@yahoo.com ሊያደርሷቸው ይችላሉ፡፡ዩዝ ኤንድ ደቨሎፕመንት ፋውንዴሽን (YCDF) ግጭትን ለመከላከል፣ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ ኢኮኖሚን ለማሳደግ፣ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት እና ሰብአዊ ክብርን ለማጎልበት እ.ኤ.አ በ2013 የተቋቋመ በወጣቶች ላይ ያተኮረ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ነው።