የ2018 ዓ.ም የመስቀል በዓል በሀገረ ስብከቱ በልዩ ሁኔታ እንደሚከበር ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ዜና ማርቅስ መንፈሳዊ ኮሌጅ መሥራችና የበላይ ኃላፊ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ሰብሳቢና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል አስታወቁ።
የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለሀገረ ስብከቱ፣ ለመንበረ ጵጵስና፣ ለወረዳ ቤተ ክህንት የሥራ ኃላፊዎችና በወልቂጤ ከተማ ላሉ አድባራት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ጸሐፊዎች በመስቀል በዓል አከባበር ዙሪያ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
የመስቀል በዓል በጉራጌ ሀገረ ስብከት በሃይማኖታዊ በዓልነት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን የሕዝቡ ባህል የሆነ ታላቅ በዓል ነው፡፡ የዘንድሮ የመስቀል በዓል አከባበር ወጉንና ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ በታላቅ ድምቀት ይከበራል፤ ቤ/ክ በአደባባይ ከምታከብራቸው በዓላት መካከል አንዱ የመስቀል በዓል ነው፤ ኦርቶዶክሳውያን ምዕመናን ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም በአብሮነት የሚያከብሩት፤ የዓለማችን ሀብት ሆኖ የተመዘገበው ይህ በዓል በሀገረ ስብከታችን በልዩ ሁኔታ መከበር አለበት ብለዋል።
ከሀገረ ስብከት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ድረስ ቅንጅት ተደርጎ ወጣቶችን በማስተባበርና በማሥተሳሰር ከመንግስት አካላት ጋር በመናበብ ለማክበር ከወዲሁ ሥራው መጀመር ይገባዋል ሲሉ ብፁ ሊቀጳጳሱ መመርያ መስተጠታቸው ተገልፆል፡፡