“ለትውልዱ በረከተ መርገም የሆነው ቴክኖሎጂ ነው”

Date:

አቶ ጌታቸው በለጠ

አቶ ጌታቸው በለጠ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር የቀድሞ ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡ በበርካታ ሀገራዊ፣ ማኅበራዊና ታሪካዊ ጉዳዮች ዙሪያም ጥልቅና በሳል ሃሳቦችን በማስተላለፍ ይታወቃሉ፡፡ በዛሬው የ”ኢትዮጵያዊነት” ዓምዳችን ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አኳያ ለሰነዘርንላቸው 10 ጥያቄዎች የሚከተሉትን ምላሾች ሰጥተውናል፡፡                   

ግዮን፡- ኢትዮጵያዊነት በእርሶ እይታ እንዴት ይገለፃል?

ጌታቸው፡- ኢትዮጵያዊነት ነባር ኢትዮጵያዊ እሴቶችን መኖር ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያን “ኢትዮጵያ” ላሰኙ እሴቶች መኖር ማለት ነው፡፡ እነዛ እሴቶች ምንድን ናቸው? ነው ጥያቄው፡፡ ታላላቆቹ እሴቶች ረጅም ታሪክን ማክበር፣ ረጅም የአባቶች ተጋድሎና ሀገርን ለመጠበቅ የከፈሉትን መስዋዕትነት አክብሮ ብቻ ሳይሆን ኑሮም ማለፍ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከውጭ ጠላቶች ጋር በነበራት ውጥረትና ችግር ውስጥ በአሸናፊነት እንድትወጣ ቀደምት አባቶች በከፈሉት ዋጋና እሴቶች መኖር ነው፡፡  ከእሴቶቻችን መካከል ያልተፈለጉ ጉድፎች አልነበሩም ማለት አይደለም፡፡ እነዛን ጉድፎች ወይም ችግሮች አሊያም ሕጸጾች መቁጠር ዋጋ የለውም፡፡ እነሱ የታሪካችን አንድ ክፍል ናቸው፡፡ እንደ አረም ነው የምንቆጥራቸው፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያን “ኢትዮጵያ” ባሰኟት እሴቶች ዛሬ መኖር ነው ኢትዮጵያዊነት ማለት፡፡

ግዮን፡- ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችን ምን ምን ናቸው?

ጌታቸው፡- ከአወቅን ባይነት ጋር በተገናኘ ችግር እየተሸረሸረ ነው እንጂ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ስትሄድ የነበረ ነገር አለ፡፡ ቀደም ባሉትና “አድሏዊነት አለባቸው” በሚባሉ ሥርዓቶች እንኳን በየትም አካባቢ ብትንቀሳቀስ ማንህ? ከየት ነህ? ፀጉረ ልውጥ ነህ አይባልም፡፡ “የእግዚአብሔር እንግዳ” ተብለህ ተቀባይነት ታገኛለህ፡፡ ብሔርህ ምንድን ነው? አይባልም፡፡ ምን ቋንቋ ነው የምትናገረው? አይባልም፡፡ በነዛ ሥርዓቶች እንዲህ ያለ ነገር አለመኖሩን በብዙ መገለጫዎች ማሳየት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ፣ ከእምነት አንፃር ብናየው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአብነት ተማሪዎች አኗኗር በቂ ማሳያ ነው፡፡ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው እየተዘዋወሩ ለምነው ነው የሚኖሩት፡፡ ለምን መጣህ? ለስለላ ነው ወይ? አይባሉም ነበር፡፡

የእግዜአብሔር እንግዳ አሊያም ተማሪ ነው እየተባለ ማኅበረሰቡ እየመገበና እያለበሰ ያኖራቸው ነበር፡፡ የኃይማኖት አባቶችም ባዶ እጃቸውን ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ እንደየእምነቱ የኃይማኖት ተቋማትን ይተክሉ ነበር፡፡ ነጋዴውም እንደፈለገ ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ ድሃውም የፈለገበት ሄዶ ኢኮኖሚውን ማሳደግ ይችል ነበር፡፡ ይህ ነው እንግዳ ተቀባይነት፡፡ በኃይማኖት ምክንያት የመጡትን ስደተኞች በመቀበል ብቻ አይደለም፡፡ ይህ ባህል አሁንም አልሟሸሸም፡፡ በሌላ በኩል፣ የእድርና እቁብ እሴታችን በቀላሉ መታየት የለበትም፡፡ እድር ወይም እቁብ ውስጥ የሚገባ ሰው ማንነት አይጠየቅም፡፡ በተለያየ አጋጣሚ “የየት ሀገር ሰው ነህ” ተብሎ አስተዳደጉ የት እንደሆነ ሊጠየቅ ይችላል እንጂ፣ “የየትኛው ጎሳ ነህ” ተብሎ አይጠየቅም ነበር፡፡ የእነዚህ ድምር ውጤቶች ናቸው ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችን የምንላቸው፡፡

ግዮን፡- ይህ ትውልድና ኢትዮጵያዊነት ተራርቀዋል?

ጌታቸው፡-  ተሸረሸረ እንጂ አልተራራቁም፡፡ በእኛ እይታ አንዳችን ሌላኛችንን ስለምንመዝን ነው እንጂ አልተራራቀም፡፡ ኢትዮጵያዊነት የሚፈተነው ሀገር ውስጥ ሳይሆን ውጭ ሲኬድ ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን ውጭ ሀገር ያሉት ኢትዮጵያውያን ስሞት ሀገር ቤት ቅበሩኝ ይላሉ፡፡ ሌላው ሀገር የእኛን ያህል እትብቴ የተቀበረበት እኔንም ቅበሩኝ አይልም፡፡ እንደኢትዮጵያዊ በየበዓሉና በየአጋጣሚው ስለሀገሩ የሚብከነከን የለም፡፡ እዚህ ያለነው ባሕሩ ውስጥ ስላለን እርጥበቱ አይሰማንም፡፡ እኔ በተማርኩበትና ባየኋቸው ሀገሮች ውስጥ በብዛት ያለው ኢትዮጵያዊ ምግብ ቤቶች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ያህል ሌሎች ሀገሮች በአሜሪካና አውሮፓ ሬስቶራንት የላቸውም፡፡ ሌሎች ዜጎች ሌላን የማወቅ ጉጉት ስላላቸው ከራሳቸው ይልቅ የሌላን ባሕል ለመልመድ መሄድ ያዘወትራሉ፡፡ እኛ በሄድንበት ሁሉ መሠባሰብ ልማዳችን ነው፡፡ በእርግጥም መናቆሩ ሊኖር ቢችልም አብረን ነን፡፡ እዚህም ቢሆን እየተሸረሸረ ቢሆንም ኢትዮጵያዊነቱ አልጠፋም፡፡ አይበለውና አንድ ችግር ቢመጣ “ሆ” ብለን በመነሳታችን መኖሩን ማየት ይቻላል፡፡  በሰላም ጊዜ ነው መስማማት ያጣነው እንጂ በችግር ጊዜ አንድ ነን፡፡

ግዮን፡- በዚህ ትውልድ ውስጥ የኢትዮጵያዊነት ተግዳሮቶቹ ምን ምን ናቸው?

ጌታቸው፡- ከኢትዮጵያዊነት ተግዳሮቶች ዋነኛው ቴክኖሎጂ ነው፡፡ እኛ ማኅበረሰብ ውስጥ ንባብን ሳናጎለብት የሀሳብ ልዕልናን ሳናከብር ነው እዚህ ደረስነው፡፡ “ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል”፣ “የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች” ዓይነት አባባሎች በምሳሌ እንድናድግ አድርገውናል፡፡ የሆነውንም ያልሆነውንም እየተነገረን ነው ያደግነው፡፡ በንባብ ሳንፈትሸው ዝም ብለን ቴክኖሎጂ ላይ ደረስን፡፡ ቴክኖሎጂው በጣም ስለሄደ ግራ አጋባን፡፡ ተደብቆ ማማትና መሳደብ ይቻላል ለካ? ተደብቆ መበደልና ኃጢያት መፈፀም ይቻላል? የሚሉ መጥፎ ጽንሠ ሃሳቦች ውስጣችን ስለዳበሩ ችግር አመጣ፡፡ ይህ ነገር ከቅርብ ሰዎቻችን አልፎ እንደ ሀገር መሣለቂያ ያደረገን ነገር ነው፡፡ ለትውልዱ በረከተ መርገም የሆነው ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ሁለተኛ የፖለቲካ ሥርዓቱ ነው፡፡ ፖለቲከኞች ለራሳቸው ሕልውና እንዲመቻቸው ብለው ክፉ ጽንሠ ሃሳብ አእምሯችን ውስጥ ስለጠቀጠቁ ላለፉት በርካታ ዓመታት የኢትዮጵያዊነት አብሮ መኖር እሴታችን ተሸርሽሯል፡፡

ግዮን፡- ይህ ትውልድ ከብሔርተኝነት መንፈስ ተላቅቆ ኢትዮጵያዊነትን መቀበል ይችላል?

ጌታቸው፡- በጣም ይቻላል፡፡ ብሔርተኝነት የእኛ ብቻ ችግር አይደለም፡፡ ሠለጠኑ በሚባሉ አሜሪካንን በመሳሰሉ ሀገሮችም ያለ ነው፡፡ ግዛቶቻቸውን የተከፋፈሉት በአውሮፓውያን  ቅኝ ገዢዎች መሠረት ነው፡፡ ዘርና ጎሳን መሠረት እያደረጉ ነው ተፈላልገው የሠፈሩት፡፡ ብሔርተኝነት በራሱ ክፋት አልነበረውም፡፡ የራስን ወገን መውደድ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ሌላውን መጥላቱ ነው ችግሩ፡፡ አንዳንዶች ይህን ራስን የመውደድ እውነታን መርዝ ቀብተው አደሉት፡፡ ለምሳሌ መድኃኒት እንዳይመር በስኳር እንደሚቀባው ወይም የኮሶ መድኃኒት መተሬ በገንፎ ወይም በሙዝ ተጠቅልሎ እንደሚሠጠው ማለት ነው፡፡ ክፉን ነገር በበጎ ጠቅልለው ወደ ማኅበረሰቡ የሚያቀርቡ ናቸው ችግር የፈጠሩት፡፡ ይህ በሕዝብ መካከል ጥላቻ ዘርቷል፡፡ አሁን የምናየውና በየጊዜው ወጀብ የሚያስነሳው ዕድሜው ብዙም አይደለም፡፡ ጎርፍ ቢሆንብንም ያልፋል፡፡ ቶሎ ወደ ሕሊናችን ስንመለስ መንቃትና መባነን እንጀምራለን፡፡

ግዮን፡- ኢትዮጵያዊነት ስሜት ነው ግብር ?

ጌታቸው፡- ሁለቱም ነው፡፡ ስሜት መሆኑ ቀረርቶና ስለኢትዮጵያ ዘፈን ስንሰማ ልባችን የሚናወጠው ነገር ነው፡፡ ስለኢትዮጵያ ታሪክ ስንሰማም ሆነ ስናነብ የሚሠማን ስሜት ነው፡፡ በሌላ በኩል የተሰማንን ስሜት መኖር ስንጀምርና ታሪኩን ስናስቀጥል ግብር ይሆናል፡፡

ግዮን፡- ማህበራዊ ድረገፆች ለኢትዮጵያዊነት ያላቸው ሚና ምንድነው?

ጌታቸው፡- የጥፋትና የልማትም መሣሪያ ናቸው፡፡ የጥፋቱ ግን እየበዛ መጥቷል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎሉ ያሉትን ያህል የሚያኮስሱም አሉ፡፡

ግዮን፡- ወጣቱ ትውልድ ኢትዮጵያዊነት ይዞ እንዲቀጥል ምን መልዕክት ያስተላልፋሉ?

ጌታቸው፡- ኢትዮጵያዊነታችን በጥልቅ መሠረት ላይ እንዲቆም የሚያደርገው አንዱ የትምህርት ሥርዓታችን ነው፡፡ ለምሳሌ በቀድሞ ጊዜ የሚሠጠው የሞራል ትምህርት የትም ሀገር ይሰጣል፡፡ አሁን ሲቪክ የሚባል መጥቷል፡፡ በአጋጣሚ የዚህን ትምህርት መጽሐፍ ካዘጋጁት አንዱ እኔ ነኝ፡፡ ትምህርቱን ከማዘጋጀታችን በፊት መንግሥትን አንድ ጥያቄ ጠይቀን ነበር፡፡ ልጆቹ መብትና ግዴታቸውን እኩል በኩል እንዲያውቁ ሚዛኑ መጠበቅ አለበት? ስንል የተሰጠን መልስ “መብታቸውን አሳውቋቸው፣ ለግዴታቸው ይደርሱበታል” የሚል ነው፡፡ የተሳሳተ ቲዎሪ ተደርጎ መጽሐፏ ተዘጋጀ፤ ያ ትውልድ ዛሬ “ሀገር ይጥፋ” የሚል ሆኗል፡፡ ከ30 እና 40 ዓመት በላይ የሆነው ቢያስበው እንኳን አፉን ሞልቶ አገሬ ትጥፋ አይልም፡፡ የአሁኑ እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል የሚል ትውልድ ስለሆነ በትምህርት ብዙ መሠራት አለበት፡፡ የነበረንን መልካም እሴት ትውልዱ እየሸረሸረው ስለሄደ ቢያንስ መልስን ለመጀመር የትምህርት ሥርዓቱ ወሳኝ ነው፡፡ እነዚህ የምናያቸው ከሰብዓዊነት ያፈነገጡ ደርጊቶች ሁሉ በትምህርት ወደ በጎ ሊመለሱ ይችላሉ፡፡

ግዮን፡- ኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶችን በዓለም ለማስተዋወቅና ቅርሶችን ከነክብራቸው ለመጠበቅ ምን ይደረግ ይላሉ? ሓላፊነቱንስ የማን ነው?

ጌታቸው፡- ታሪካዊ ቅርሶች ላይ የተሰራ የፖለቲካ ጨዋታ አለ፡፡ ባለፉት ዘመናት ስንማር የኖርነው አክሱምና ላሊበላን የመሳሰሉ ቅርሶች የሁላችንም እንደሆኑ ነው፡፡ ያለፈውን ሥርዓት የመሩት ሰው ያሉት ግን ከዚህ የተለየ ነበር፡፡ “አክሱም ለወላይታ ምኑ ነው?” ብለው በአደባባይ ተናግረው ነበር፡፡ ይህ የናደውና ያደረሰው ጥፋት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በየትም ቦታ ያለው ቅርሳችን አባቶቻችን በጋራ የሠሩት የእነሱ ውጤት ነው፡፡ ወደ ነበርንበት መመለስ አለብን፡፡ ቅርስ ከሌለ ሀገር የለም፡፡ በቱሪዝም መስክ ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊም ሆኑ የግል ተቋማት በዚህ ጉዳይ ላይ በሠፊው ትምህርት መስጠት አለባቸው፡፡

ግዮን፡- አባቶቻችን ለዚህ አገር በክብር መቆየት የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለው ለተከታዩ ትውልድ አስተላልፈዋል፡፡ ይህ ትውልድስ ለቀጣዩ የማስተላለፍ ምን ይጠበቅበታል? ምን ያድርግ? ጌታቸው፡- በትውልዱ ውስጥ አደራ በልነት መኖሩ ይታወቃል፡፡ ትልቁ ነገር ይህን መተው ነው፡፡ በማይጨው ጦርነት ለምን ጦሩ ተፈታ በሚል የተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ የጦርነት ታሪኮቻችንን ስንመለከት ስሜት ያርዳል፡፡ የአባቶቻችን አወዳደቅ ስሜትን ይይዛል፡፡ ለምን ዓላማ ሞቱ? ብንል ለእኛ ብለው ነው፡፡ የትናንትን ኢትዮጵያ አይተው ለመጪው ብለው ነው በመርዝ ጋዝ የተቃጠሉት፡፡ በእኛ ጊዜ ሀገራችን እየደማች ያለችው ከውጭ በመጣ ወራሪ አይደለም፡፡ ከውስጧ አፍራሾች ሲነሱባት እምቢ ብሎ የሚነሳ ትውልድ ለምን አልኖረም ማለት አለብን፡፡ የመኖራችንን ምክንያትና ዓላማ ማወቅ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ይህን ሕዝቡ እንዲረዳ ትልቅ ሚና መጫወት የሚችለው ሚዲያው ነው፡፡ ጭፈራና የውጭ ባሕልን ማስተዋወቅ ሳይሆን አባታዊ ምክሮችን ትውልዱ እንዲሰማ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የደራሲያንም ሆነ የሁላችንንም ደርሻ ትውልዱን ማነጽ ነው፡፡ ከመንግሥት ይልቅ የኪነ ጥበቡና የሚዲያው ኃላፊነት የበለጠ የጎላ ነው፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የህወሓት የቃላት ጦርነት ንሯል።ይዋጉ ይሆን?

ሶስቱም ኃይላት የጦር ኃይላቸዉን እያጠናከሩ፣ አዳዲስ ተዋጊ እየመለመሉ መሆናቸዉ...

የሐማስ ታጣቂዎች ከእስራኤል ጋር በመተባበር የተከሰሱ ሰባት ሰዎችን ገደሉ

ሰኞ እለት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተዘዋወረ ያለ ቪዲዮ እንደሚያሳየው...