
ታሪኩ መኮንን (የፊልም ባለሙያ)
የዛሬው የኪነ ጥበብ ዓምዳችን እንግዳ ልዩ ልዩ የሙዚቃ ቪዲዮዎችን ከመሥራት አንስቶ በቅርቡ ደግሞ በበርካታ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አልፎም በትልልቅ ዓለም አቀፍ የሲኒማ መድረኮች ተወዳጅ እና ተወዳዳሪ ለመኾን የበቃውን ‹‹አፊኒ›› የተሰኘውን ሀገርኛ ፊልም ያዘጋጀው ታሪኩ መኮንን ነው፡፡ ታሪኩ ይኽ የፊልም ሥራው የመጀመሪያው ቢኾንም፣ ያልተነገረላቸውን የሀገራችንን ሕዝቦች ድንቅ ባሕሎችና ችግርን የመፍቻ ዘዴዎች በማራኪ ኪናዊ ለዛ ለተመልካች ተደራሽ በማድረግ ረገድ የተዋጣለት ሥራ መሥራት የቻለ ባለሙያ ነው፡፡ ከታሪኩ ጋር በፊልምና ኪነጥበባዊ ሕይወቱ ዙርያ አሁን ላይ ከሚገኝበት ሃገረ እንግሊዝ ከጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ጋር የሚከተለውን ቆይታ አድርጓል፡፡ መልካም ንባብ!
ግዮን፡- ራስህን ለአንባቢያን በማስተዋወቅ ብትጀምር?
ታሪኩ፡- ታሪኩ መኮንን ወይም ‹‹ዘካሪያስ›› እባላለሁ፡፡ በፊልም ሥራ ሙያ ውስጥ የምገኝ ባለሙያ ነኝ፡፡ ተወልጄ ያደኩት ሐዋሳ ነው፡፡
ግዮን፡- ወደ ፊልሙ ዓለም እንዴት ገባህ? ምን ያህል ጊዜስ ኾነህ?
ታሪኩ፡- ወደ ፊልሙ የገባሀት 2002 ዓ.ም ላይ ነው፡፡ አንድ ካሚል የሚባል የወልቂጤ ልጅ ጓደኛ ነበረኝ፡፡ ከእርሱ ጋር በመኾን አርባ ምንጭ ላይ ‹‹ሻራ›› የሚባል ፊልም ሠርተን አቀረብን፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በዚሁ ሙያ ውስጥ እገኛለሁ፡፡
ግዮን፡- ፊልም ውስጥ የምትሳተፈው እንዴት ባሉ ዘርፎች ነው?
ታረኩ፡- ፊልም ውስጥ የምሳተፈው በዝግጅት ነው፡፡ ክሊፕ ላይ ግን ሁሉንም ዳይሬክት አድርጌ ቀርጬ ኤዲት አድርጌ ነው የማስረክበው፡፡
ግዮን፡- ከፊልም ውጪ ምን ያህል የሙዚቃ ክሊፖችን ሠርተሃል?
ታሪኩ፡- ብዙ ሰርቻለሁ፡፡ ከታዋቂዎቹ ውስጥ የኢትዮጵያን አይዶል አዘጋጅ የኾነችው የሺ ደመላሽ ‹‹ዛሬ ልዩ ቀን ነው›› የተሰኘውን ሙዚቃ ቪዲዮ ክሊፕ ሰርቻለሁ፡፡ የአበበ ከፈኒንም እንዲሁ አንድ የኦሮምኛ ሙዚቃ ክሊፕ ሠርቻለሁ፡፡ ግጥምና ዜማ የሠራሁለት ደግሞ ሳሚ ጎ ነው፡፡ ለሳሚጎ ባለቤት ለነፃነት ሱልጣንና ከድር አጋዩ ለሚባል ኦሮምኛ ዘፋኝም እንዲሁ ዘመናዊ ክሊፕ ሠርቻለሁ፡፡ ለአስጌ ዴንዳሾም እንዲኹ አራት ሙዚቃዎች ሠርቻለሁ፡፡ ከመጀመሪያው እስከ ያደሴ ያለውን እኔ ነኝ የሠራሁለት፡፡ ታሪኩ ዲሽታ ጊናንም ከዲሽታ ጊና በፊት በነፃ ሠርቼለታለሁ፡፡ እዚያው አሪ ውስጥ ለታሪኩና ክፍሌ ወሰኔ ለሚባል ሰው ሠርቻለሁ፡፡ ቦዲ ለሚባለው ብሔረሰብም ሠርቻለሁ፡፡ ለቢና፣ ለዳነሰነች ፣ ለኒያንጋቶ፣ ለዲዚና መሰል ማኅበረሰቦችም ሠርቻለሁ፡፡ ወደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ስንመጣ ደግሞ ለሀዲያ፣ ለደንጋ ፣ ለከንባታ ፣ ለአላባ ፣ ለወላይታ ፣ ለዳውሮ ፣ ለኮንታ ፣ ለጋሞ ፣ ለዘይሴ ፣ ለኦይዳ ፣ ለኮንሶ እና ለሌሎችም ሠርቻለሁ፡፡ ለየም ብሔረሰብ፣ ለጌዲዮ ብሔረሰብ ፣ ለኮሬ ብሔረሰብ ፣ ለቡርጂ ብሔረሰብ ፣ ለአሌ ብሔረሰብ እና ለደራሼ ማኅበረሰብም ሠርቻለሁ፡፡
ግዮን፡- ከደቡቡ ክፍል ውጪ የሠራህባቸው ቦታዎች የት የት ናቸው?
ታሪኩ፡- ጎንደርም ሄጄ የጎንደር ሙዚቃ ሠርቻለሁ፡፡ ባህርዳር ሄጄም የጎጃም ሙዚቃ ሠርቻለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር አብዛኛውን የኢትዮጵያ ክፍል አካልየዋለሁ ማለት እችላለሁ፡፡
ግዮን፡- በጣም የምትወደውና ብዙ ትዝታ ያለህ የትኛው ሥራህ ነው?
ታሪኩ፡- ኢትዮጵያ የ86 ብሔረሰብ ውቅር ሀገር ናት፡፡ ከእነዚህ ውስጥም 46 የሚኾኑት ማኅበረሰቦች ደቡብ ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ ከ50 በላይ የሚኾኑ ብሔረሰብ ሥራዎችን በሚገባ አይቻለሁ፡፡ ሁሉም ብሔረሰብ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁሉም ብሔረሰብ ችግሮችን የሚፈቱበት መንገድ አላቸው፡፡ ሁሉም ጥንታዊ የኾነ ልምድ አላቸው፡፡ የመከባበር ባሕላቸውም ተመሳሳይ ነው፡፡ በተለይ ታላቅን ማክበር ላይ ሁሉም አንድ ዓይነት ናቸው፡፡ ሁሉም ሕዝብ የሞራል ሕዝብ ነው፡፡ አዛውንት ማክበር፣ ቤተሰብ ማክበር፣ እናት አባት ማክበር የኢትዮጵያውያን የጋራ ባሕሪ ነው፡፡ እኔ አብዛኛውን ጊዜ ትኩረት የማደርገው ባሕል ላይ ነው፡፡ ባሕላቸውን ካየሁ በኋላ ማኅበረሰቡ የሚገኝበት ቦታ እሄዳለሁ፡፡ ሕብረተሰቡ ማሳየት የሚፈልገውን ነገር ከቦታው በመገኘት እቀርፃለሁ፡፡ የመልከዓ ምድሩንም አቀማመጥ ለቱሪዚም ያለውን አመችነት ሳይ እጅግ እገረማለሁ፡፡ የዚህ አስተሳሰብ ውጤቴም ነው አፊኒን ፊልም ለመሥራት ያነሳሳኝ፡፡
ግዮን፡- በቅርቡ ለእይታ የቀረበው ፊልምህ “አፊኒ” ይባላል፡፡ ሥያሜው ምን ማለት ነው?
ታሪኩ፡- ‹‹አፊኒ›› ማለት የሲዳምኛ ቃል ሰኾን ትርጉሙም “ሰምታችኋል” ማለት ነው፡፡ የኾነ ሰው ችግር ወይም በደል ሲደርስበት ከ3ኛ ወገን ጀምሮ እስከ ሸንጎ ድረስ ጉዳዩን “ሰምታችኋል ወይ” እንደማለት ነው፡፡ ጉዳዩን ጉዳያቸው እንዳደረጉትና እነሱንም ጭምር እንደሚያሳስባቸው መጠየቂያ መንገድ ነው፡፡

ግዮን፡- ፊልሙ በምን ላይ ያጠነጥናል? ምን ያህል ደቂቃዎችንስ ይጨርሳል? እስከመቼስ በእይታ ይቆያል?
ታሪኩ፡- ፊልሙ 1 ሰዓት ከ43 ደቂቃ ይፈጃል፡፡ የፊልሙ ሀሳብ ይቅርታ ነው፡፡ የፊልሙ አጠቃላይ ጭብጥ ደግሞ እውነት ነው፡፡ የዚች ዓለም ወይም የሕዝብ ችግሮች እውነቱ እስከተጣራ ድረስ ምንም ዓይነት ግጭት ውስጥ አይገባም፡፡ የአንድ ሰው እውነት ሲጎድል ፍትሕ ይጓደላል፡፡ ፊልሙ ማስተላለፍ የፈለገው ይኼንን ነው፡፡ እውነትን በመመለስ ውስጥ ፍትሕን ማሰጠት ይቻላል የሚል መልዕክት ነው ማስተላለፍ የፈለግነው፡፡ የፍትሕ መሠረቱ የእውነት መጓደልን ማስተካከል ነው፡፡ አፊኒ ደግሞ ዋና ዓላማው እውነትን ማውጣት ነው፡፡ የሲዳማ አባቶች “እውነት ትውጣ ፍትሕ ትምጣ” ነው የሚሉት፡፡ እውነት በሁለት መንገድ ይገለፃል፡፡ የመጀመሪያው በሲዳምኛው አባባል “ሀዩ” ይባላል፡፡ በእንግሊዘኛው ‹‹ሎጂክ›› የሚባለው ዐይነት ነው፡፡ መረጃ በማቅረብ እውነትን ይፋ ማድረግ ማለት ነው፡፡
ለምሳሌ ፍርድ ቤት እውነት ሳይኾን የሚወጣው መረጃ ያለው ሰው ነው የሚያሸንፈው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የሲዳማ አባቶች “ሃላሌ” ይሉታል፡፡ ሃላሌ ማለት በእምነት የሚገለፅ እውነት ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ሰዎች ተበድለው በዳይ በመረጃ ሊያሳምን ይችላል፡፡ ይህ ሲኾን በሲዳማ አባቶች እውነቱ በእምነት የሚጣራበት መንገድ አለው፡፡ ይኼ የአውጫጭኝ መንገድ በእምነት እስከ ፈጣሪ ድረስ በመሄድ የሚደረስበት ነው፡፡ ስለዚህ የሲዳማ አባቶች እውነትን ለማግኘት አንድም በሎጂክ አንድም በእምነት ጥረት አድርገው ፍትሕን ያሰፍናሉ፡፡ የአፊኒ ፊልምም በእነዚህ ነገሮች ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡
ልጁ የተጋጨበት አባት ለልጁ ፍትሕ ያገኝ ዘንድ ይጥራል፡፡ የገጨችው አካል ደግሞ የእሱን ልጅ ለመግጨት ብላ አስባና አቅዳ ኾን ብላ ከቤቷ እንዳልወጣችና እንዳላደረገችው በእምነትም በሎጅክም ተከራክራ ለመታረቅ ትሞክራለች፡፡ ተበዳይ ግን ልጁን በእምነት ለማግኘት ይጥራል፡፡ በዚህም ተበዳይን ለመካስ ከተበዳይ ልጅ ወልዳለት ለመተካትና ፍትሕን ለማስፈን ይጣራል፡፡ ይሄ ፊልም የእኛን የገፅታ ግንባታ የሚሳይ ነው፡፡ ፊልሙ የሲዳማን ማኅበረሰብ በደንብ መግለጽ የሚችል ነው፡፡
ግዮን፡- የሲዳማን ባሕል በፊልም ለመሥራት ምን አነሳሳህ?
ታሪኩ፡- እኔ ተወልጄ ያደግሁት ሐዋሳ ነው፡፡ ስለዚህ ሲዳማ ማለት ከልጅነቴ ጀምሮ የማውቀው በደንብ ላወራለትና ልናገርለት የምፈልገው፣ በፊልም ልገልፀው የምሻው አንዱ ማኅበረሰብ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የክልሉ መንግሥት ይህን ፊልም እንድሠራ ልጃችን ነው ብሎ እስከ 7 ሚሊዮን ብር ድረስ ሰጥቶኛል፡፡ መንግሥት ይህን ነገር ያደረገልኝ የማኅበረሰቡን ባሕልና ማንነት ስለማውቅና እንደምሠራው ስለተማመነብኝ ነው፡፡ እኔም ፊልሙን ለመሥራት ያነሳሳኝ እነዚሁ ሁኔታዎች ናቸው፡፡
ግዮን፡- ፊልሙ መቼ ነው ለእይታ የበቃው? ምርቃቱስ መቼ ነበር?
ታሪኩ፡- ሚያዚያ 2016 ዓ.ም አካባቢ ላይ የሲዳማ ክልል መንግሥት ካቢኔዎች ባሉበት ተመርቋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ፕሬዝዳንት ደስታ ሌዳሞ በተገኙበት ነው ተመረቀው፡፡ ለተከታታይ 3 ቀናትም የክልሉ ሕዝብ እንዲያይ ተደርጓል፡፡ ሐምሌ 12/2016 ዓ.ም ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ በበርካታ ሲኒማ ቤቶች ታየ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዋናነት በዓለም ሲኒማ እስካሁን እየታየ ነው፡፡
ግዮን፡- በምርቃቱ ዕለት ምን ተሰማህ? ያገኘኸው አስተያየትስ ምን ነበር?
ታሪኩ፡- ፊልሙ የመጀመሪያው ሲዳምኛ ፊልም ነው፡፡ በሀገራችን አሉ የተባሉ አንጋፋ አርቲስቶች ግሩም ኤርሚያስና አማኑኤል ሀብታሙ የሠሩበት ፊልም ነው፡፡ ፊልሙን ሙሉ የሲዳማ ሕዝብ ሲወደው “ፈጣሪ ይመስገን፤ ልፋቴ በከንቱ አልቀረም” የሚል ከፍ ያለ ደስታ ነው የተሰማኝ፡፡ ምክንያቱም የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ያን ሁሉ ወጭ ያስወጣ እና እምነት ተጥሎብኝ የሠራሁት ሥራ ሲወደደልኝ “እግዚአብሔር ይመስገን ይኼ ያንተ ሥራ ነው” ነው ያልኩት፡፡
ግዮን፡- የተዋናይ ምርጫህ ምን ይመስላል? ምን ያህል ተዋናይስ ተሳትፈውበታል? የፊልሙ ቋንቋስ ሲዳምኛ ነው?
ታረኩ፡- መሪ ተዋናዩ ግሩም ኤርሚያስ ነው፡፡ ቋንቋው ደግሞ በሲዳምኛ ዘዬን የተላበሰ አማርኛ የሚነገርበት ነው፡፡ አማኑኤል ደግሞ ምንም አማርኛ የማይችል ኾኖ ሙሉ ለሙሉ ሲዳምኛ እያወራ ነው ፊልሙን የጨረሰው፡፡ በቋንቋ ረገድ ሁለቱን ቋንቋዎች ነው የተጠቀምነው፡፡ ተዋንያንን በተመለከተ ከመቶ በላይ ሰዎች ተሳትፈውበታል፡፡ በተለያዩ የፊልሙ ሁነቶች ላይም የማኅበረሰቡን አባላት ተሳትፈውበታል፡፡ ለምሳሌ የፋሮ ጭፈራ ላይ ፣ የቄጣላ ሥርዓት ላይ ፣ የሸንጎ ሥርዓት ላይ ማኅበረሰቡ ተሳትፏል፡፡
ግዮን፡- ፊልሙን ለመሥራት ምን ያህል ጊዜ ፈጀ?
ታሪኩ፡- ፊልሙን ሳንሠራ በመጀመሪያ ወደ 3ወር ለሚጠጋ ጊዜ የገጠሩን ማኅበረሰብ ጎብኝተናል፡፡ መሪ ተዋናዮቹ ፊልሙን ኾነው ነው የሚሠሩት ፤ ያን ለመኾን ደግሞ የተለያዩ ልምምዶችን ማድረግ ነበረባቸው፡፡ ለምሳሌ የፈረስ ልምምድ ነበረው፡፡ ፈረስ ተገዝቶ ነው ሲለማመዱ የነበረው፡፡ የሳይክልና የሞተር እንዲሁም የእግር መንገድ ልምምድም አድርገዋል፡፡ ማኅበረሰቡን ቋንቋ እንዲዋሐዱት ለ3 ወራት ከማኅበረሰቡ ጋር ቆይተዋል፡፡ ለአንድ ወር ደግሞ ስክሪፕቱን የማጥናት ሥራ ሠርተዋል፡፡ ቀረጻው ደግሞ 3 ወራትን ጨርሷል፡፡ ቀረፃው የሲዳማ ገጠራማ ቦታዎች ላይ የተከናወነ ነው፡፡ ለአንድ ወር ከገጠር ሳይወጡ ቀረፃው ተሠርቷል፡፡ በከተማዎች ደግሞ አንድ ወር ከግማሽ የቀረፃ ሥራው ተከናውኗል፡፡ የፕሮዳክሽን ሥራውም እንደዚሁ ሰፋ ያሉ ወራትን ጨርሷል፡፡ በአጠቃላይ ፊልሙን ሠርቶ ለማጠናቀቅ ከአንድ ዓመት በላይ ጨርሷል፡፡
ግዮን፡- ፊልሙን ማነው ያዘጋጀው? አንተ ለሲዳማ ቱሪዝም ቢሮ መሥራት እንደምትፈልግ ጠቁመህ ነው? ወይንስ ቢሮው እራሱ ጥያቄውን ይዞልህ ቀርቦ ነው?
ታሪኩ፡- ደራሲ እለፋቸው ብርሃኑ ይባላል፡፡ የሲዳማ ልጅ ነው፡፡ እሱ እስክሪፕቱን አምጥቶ ለእኔ ሰጠኝ፡፡ ፕሮፖዛል አዘጋጅተን ለሲዳማ ባሕልና ቱሪዘም ቢሮ አስገባን፡፡ የገንዘብ ምንጭ ለመጨመር ተፈልጎ ኮሚቴ ተዋቅሮ ከመንግሥት ጋር በመደጋገፍ ነው ፊልሙ የተሠራው፡፡ ፊልሙ አክቲቭ እስኪኾን ድረስ ለአራት ዓመታት እስክሪፕቱን በማስተካከል ቆይተናል፡፡ ይህ ማለት ሲዳማን በትክክል የሚወክል እንዲኾን፣ የአዲስ አበባም ሰው እንዲወደው ዘመናዊ ፊልም እንዲኾንና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታይ በሚል ወደ አራት ዓመት ብዙ ሥራ ተሠርቶበታል፡፡
ግዮን፡- ሌሎች ባለሙያዎችም በተለይም እንደሲዳማ ያሉ ሌሎች የማሕበረሰብ አባላትም ባሕቸውን በእንዲህ ዓይነት መንገድ ለማቅብ እንዲሠሩ ምን ትመክራለህ?
ታሪኩ፡- የእኔ ምክር ታላቁ የፊልም ሰው ኃይሌ ገሪማ እንዳሉት ነው፡፡ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ “ሁሉም ሰው የሚያውቀውን ይሥራ” ይላሉ፡፡ ሰው የሚያውቀውን ከሠራ ተጽዕኖ መፍጠር ይችላል፡፡ ኦሮሚያ ፣ አማራ ፣ ወላይታ ሁሉም አካባቢ ያለ ዳይሬክተር በደንብ ከሠራ የታለመለትን ግብ መምታት ይችላል፡፡ እኔ ለምሳሌ መጀመሪያ ላይ የአፊኒን ስክሪፕት የሚያዘጋጅ ልጅ ከአዲስ አበባ ነበር ያመጣሁት፡፡ ልጁ መጀመሪያ ላይ አፊኒን የተረዳበት መንገድ ልክ አልነበረም፡፡ አፊኒን ሲያስብ እንደ አንድ ቃል ብቻ ነበር እያሰበ የጻፈው፡፡ ይህን ሥራ ድጋሜ አፍርሼ ነው የሠራሁት፡፡ ይኼ የኾነው እኔ አፊኒን በማወቄ ነው፡፡ ሲዳማ አፊኒን የፈጠረው ከሁሉ ቀድሞ ነው፡፡ ሲዳማ በአፊኒ ምክንያት እውነትን አግኝቶ የተቀመጠ ማኅበረሰብ ነው፡፡ አፊኒ ትልቅ ፍልስፍና ነው፡፡ ይኼን ነገር ነው ፊልም ላይም ለማሳየት የሞከርኩት፡፡ እኔ በደንብ ስለገባኝ ተራቅቄበታለሁ፡፡ ስለዚህ ሁሉም በየአካባቢው ቢሞክር አርቲስቱ ለመሥራት ዝግጁ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አርቲስት ደስ ብሎት ነው የሚሠራው፡፡ በዘርፉ በቂ ባለሙያ አለ፡፡ ነገር ግን የመረዳትና የማመን ነገር እንቅፋት ይኾናል፡፡ ኢትዮጵያ በባሕል እጅግ የበለጸገች ሀገር ነች፡፡
ግዮን፡- አሁን የት ሀገር ነው ያለኸው? የሄድክበት ምክንያትስ ምንድነው?
ታሪኩ፡- አሁን ያለሁት እንግሊዝ ሀገር ለንደን ነው፡፡ የሄድኩት የኢትየጵያ ፊልም ፌስቲቫል ላይ ልሳተፍ ነው፡፡ ይህ የፊልም ፌስቲቫል ሲዘጋጅ ለ5ኛ ጊዜ ነው፡፡ እኔም የመጣሁት የአፊኒን ፊልም ሥራን ይዤ ነው፡፡ ለንደን ያለው ማኅበረሰብም ፊልሙን አይቶታል፡፡ በጣም እንደወደደውም ተረድተናል፡፡ ደስ የሚል ምላሽም አሳይቶናል፡፡ ተመሣሣይ ሥራዎችን በደንብ እንድሠራ አደራ ተሰጥቶኛል፡፡
ግዮን፡- አጠቃላይ ኹነቱስ ምን ይመስላል? ግብዣውስ ከየት ነው የመጣው? አመልክታችሁ ነው ወይስ ተጠርታችሁ?
ታሪኩ፡- ግብዣው ከአበሻ ቪው ኢንተርቴመንት የመጣ ነው፡፡ ይህ ድርጅት ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ለዛ ያላቸውን ፊልሞች በመምረጥ በተለያዩ ሀገራት በሚካሄዱ የፊልም ፌስቲቫሎች ላይ የሚያሳትፍ ነው፡፡ ሀገሩ ላይ ያሉ የፊልም አድናቂያን ፊልሙ ይቀርብላቸዋል፡፡ በእኛ ፊልም ላይ የከተማዋ ከንቲባ ጭምር ተሳትፈዋል ፤ እንዲሁም በርካታ ኢትዮጵያውያንና ብዙ ጥቁሮችም ታድመዋል፡፡ ብሪክሰን የምትባል ቦታ ላይ ነበር ፊልሙ የቀረበው፡፡ ልዩ ልዩ ባለሥልጣናት እና አርቲስቶችም በዚህ ፌስቲቫል ላይ ታድመዋል፡፡ አፊኒን ያዩ ሁሉ በጣም ተደምመዋል፡፡ በርካታ ኢትጵያውያን እንዲህ ዓይነት ባሕልም አለን ወይ ሲሉ ነበር፡፡
ግዮን፡- የፊልሙ ፌስቲቫል ለምን ያህል ጊዜ ነው የሚቆየው? ውድድርስ አለው?
ታሪኩ፡- ውድድር የለውም፡፡ ለ3 ቀን ነው የታየው፡፡ የመጀመሪያ ቀን ላምባዲና የተባለ ፈልም ታየ ፤ ከዚያ የኛ ፊልም ቀጥሎ ደግሞ ቲያትር ለእይታ ቀርቧል፡፡ ስለዚህ በጣም ጥሩ ነበር፡፡
ግዮን፡- የፊልሙ ፖስተር ምንን ለማመልከት ታስቦ የተነደፈ ነው?
ታሪኩ፡- በፖስተር ደረጃ ሁለት ተቃራኒዎች (አንታጎኒስትና ፔንታጎኒስት) ናቸው ፊልሙ ላይ ያሉት፡፡ የግሩምና የአማን ፎቶ ነው የሚታየው፡፡ የግሩም ሀላሌን ነው የሚወክለው፡፡ ሀላሌ ማለት እውነት ማለት ነው፡፡ እውነት ደግሞ እንከን የሌለው ነው፡፡ ስለዚህ ሲዳማን በአዎንታዊ ጎኑ ለመግለፅ የተስተካከለ ጀግና የነብር ቆዳና ሴና የለበሰ አክተር ከፊት ፈረስ እየጋለበ ነው የሚታየው፡፡ ከእሱ ጀርባ ደግሞ ጠላት የኾነው አካል ትክክል ባልኾነ አለባበስ ከእውነት ተደብቆ ይታያል፡፡ ፖስተሩ እንዲገልፅ የተደረገው ይኼን ነው፡፡
ግዮን፡- እንደ ሀገር ለፊልሙ ዘርፍ እድገት ለባለሙያዎቹ ምን ማለት ትፈልጋለህ?
ታሪኩ፡- ፊልምን ልንሠራ ስናስብ ትልቅ ምስል በልቦናችን ማስቀመጥ ይኖርብናል፡፡ እኔ የዛሬ አራት ዓመት ይህን ፊልም ስክሪፕት ስራ ሳስብ የነበረው እሳቤዬ ኔትፍሌክስ ላይ እንደማሳይ ነበር፡፡ ያሰብኩት ነገር ተሳክቶልኝ ዛሬ ለንደን ላይ እየታየልኝ ነው፡፡ በዚያ ላይ አሁን ‹‹ብላክ አፍሪካ ፒፕል ሂስትሪ ፊልምስ›› ለውድድር ተጠይቀናል፡፡ ማንቺስተር ላይም የኒው አፍሪካ ፊልም ፌስቲቫል ሥራ እንድንሳተፍ ተጠይቀናል፡፡ አሜሪካም የጥቁር አፍሪካ ፊልም ፌስቲቫል እንድንሳተፍ ተጠይቀናል፡፡ ስለዚህ ይኼ ሁሉ ግብዣ የመጣው እኔ ከዛሬ አራት ዓመት በፊት ይህን ፊልም ስሠራ ዓለም ላይ መታየት በምችልበት ደረጃ ልክ በመሥራቴ ነው፡፡ ከእኔ የተሸለ አቅም ያላቸው ባለሙያዎች በሀገራችን አሉ፡፡ እነርሱ ለትልቅ አስበው ከሠሩ ትልቅ ደረጃ መድረስ ይቻላል፡፡ ዓለም ላይ መታየት የሚችል ፊልም መሥራት ይችላሉ፡፡ ሀገራችን በቂ ባለሙያ አላት፡፡
ግዮን፡- በቀጣይ ምን ለመሥራት አስበሃል?
ታሪኩ፡- እኔ ከዚህ በኋላ የምሠራው ፊልም ዓለም አቀፋዊ እንዲኾን እፈልጋለሁ፡፡ በተለይ ደቡብ ላይ ያሉ በርካታ ባሕሎች ላይ ትኩረት እያደረኩ ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ ነው የምፈልገው፡፡ የኔ ሕልም ደቡብ ኢትዮጵያ ላይ ሠርቶ ዓለም ላይ መገለጥ ነው፡፡
ግዮን፡- በመጨረሻም ማስተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት ካለ?
ታሪኩ፡- ፊልም መሥራት እጅግ ከባድ ነገር ነው፡፡ ከዚያም የሚከብደው ደግሞ ፊልምን ሠርቶ ማሳየት ነው፡፡ ፊልምን የሚያይ ሰው ደግሞ ለሥራው ክብር የሚሠጥ ነው፡፡ በተለይ ሲኒማ ገብቶ ፊልም የሚያየው የአዲስ አበባ ሕዝብ እግዚአብሔር ያክብረው፡፡ የአዲስ አበባን ፊልም ተመልካች እጅግ በጣም አመሠግናለሁ፡፡ በጣም ጉልበት ኾነውኛል፡፡ ለንደን የታደሙ ኢትየጵያውያንንም በጣም ማመሰገን እፈልጋለሁ፡፡ እንግሊዝ ሀገር የእኛ ፊልም የታየው ቻርሊን ቻፕሊን የተወነበት መድረክ ላይ ነው፡፡ ቻርሊን ቻፕኒን የታየበት ቦታ ላይ የኔም ፊልም በመታየቱ ፈጣሪ ይመስገን፡፡ በዚህ ሥራ ላይ የረዱኝ የሲዳማ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አባላት ፣ የፊልም አሠሪ ኮሚቴ ካሊቱ ዱባለ ፣ ይርጋአለም ፣ አዜብ ፣ ልደትና ዘለቀን በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ይኼ ፊልም እውን እንዲኾን የገንዘብም የጉልበትም ዋጋ ከፍለዋልና እጅግ አመሰግናለሁ፡፡
ባለቤቴ ፍጹም ተስፋዬን በጣም ላመሰግናት እወዳለሁ፡፡ ይኼ ፊልም ከተጀመረ ሦስት ልጅ ወልደናል፡፡ በተለይ ሁለቱን ልጆቼን ዋጋ ከፍላ ነው እያሳደገች ያለችው ፤ ልጆቼን አላየኋቸውም፡፡ ምክንያቱም የሥራ ልምምድ ላይ ስለነበርኩ ነው፡፡ እርሷ ከአራስ ቤት ጀምሮ ስቃይዋን አይታ ነው ያሳለፈችው፡፡ ስለዚህ ሽልማቱ ለእርሷ ይገባል፡፡ ጓደኞቼም እነ ቴዎድሮስ፣ ሻሻሞ ዱከሌ፣ ኢሳያስ እና ያልጠራኋቸው ብዙ የለፉትን አመሰግናለሁ፡፡ ደራሲው እለፋቸው ብርሃኑም ይህን ነገር አንተ ሥራ ብሎ ሰለሰጠኝ እጅግ አመሰግነዋለሁ፡፡ ይኼን ቃለ ምልልስ ከግዮን መጽሔት ጋር እንዳደርግ እንዲሁም ፊልሙን በተመለከተ ምርጥ ዘገባ በማዘጋጀት ለተባበረኝ አለባቸው ደሳለኝ (ሐበሻ) እንዲሁም ፊልሙ በተለያዩ ሀገራት እንዲታይና የሲዳማ ባሕል እንዲተዋወቅ የራሳቸውን አበርክቶ የተወጡትን በዚህ አጋጣሚ ከፍ ያለ ምሥጋናዬን ላቀርብላቸው እወዳለሁ፡፡ በአጠቃላይ ይህን ፊልም ስሠራ ሁሉም ሰው ነው ያገዘኝ ፤ ሁሉንም ሰው አመሰግናለሁ፡፡
ግዮን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ሥም ከልብ እናመሠግናለን፡፡
———-
ቅጽ 6 ግዮን ቁጥር 217 ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ.ም