ተቀዳሚ ሐጂ ሙፍቲ ዑመር ኢድሪስ በማረፍ ከፍተኛ ሀዘን አልተሰማኝም ። ሀዘን ከተሰማኝም ለሀገር እና ለሀገሬዎቹ ነው ። ምልክታቸውን አጥተዋል ። ፍቅርና ሰላምን ከቦታው ላይ አጥተናል ።
ሙፍቲ ምን ጎደለባቸውና ያሳዝኑኛል ? ብዙዎቻችን መሆን ፈልገን ያቃቸን እሳቸውን ማከል ነው ። ፍቅርን ሰብከዋል ፤ ኖረውታልም ። ለሰው ልጅ ያላቸው ክብር በአንደበት ብቻ ሳይሆን በሕይወት ኑረው ያሳዩት ነው ። የእስልምና ብቻ ሳይሆን የሀይማኖት መሪ ምልክት ነበሩ ።
በክርስትና እምነት ስር የሚገኙ ሀይማኖት ተከታዮች ብዙዎቹ ከየትኛውም የክርስትና መምህር በላይ በተቀዳሚ ሐጂ ሙፍቲ ዑመር ኢድሪስ ላይተመሳሳይ የመውደድና በህልፈታቸው የማዘን ስሜት አሳይተዋል ።
ከተሳሳትኩ አርሙኝ እንጂ ይህ ካሁን ቀደም በማንም የሀይማኖት አባት አልታየም ፤ ወደፊትም እንጃ ። ሐጂ ክርስቶስን አልሰበኩም ፣ ከብዙ ክርስቶሳውያን በላይ ግን እንደ ክርስቶስ ያለ ፍቅርና ሰላምን ኑረው አሳይተዋል ። በቅድስና ተመላልሰዋል ። የሀይማኖትን ድንበር አልፈው ብዙ ሀይማኖታዊ ልዩነት ባላቸው ሰዎች ዘንድ ፍቅር ሆነው ተገኝተዋል ።
ጋሽ ስብሐት ገ/እግዚአብሔርን በአንድ ወቅት ቃለመጠይቅ ሳደርግለት ” እኔ ገላዬን ወንድ ነክቶኝ አያውቅም ። ሀይለመለኮት መዋዕል ነው ማጀቴ ወስዶኝ ወንዝ ወስዶ ገላዬን ያጠበኝ ። እሱ ብቻ ነው ገላዬን ነክቶኝ የሚያውቀው ወንድ ” አለኝ ።
” ጋሽ ስብሐት ጋሽ ሀይለመለኮትን እንዴት ለመድከው ? ” አልኩት ።
” እኔ ለምጄው አይደለም ። እሱ አልምዶኝ ነው ። ” የሚል ውብ እና የማይረሳ መልስ ሰጠኝ ።
ተቀዳሚ ሐጂ ሙፍቲ ዑመር ኢድሪስን የወደድናቸው እኛ ሰው ለመውደድ ስንባዝን አግኝተናቸው አይደለም ። እሳቸው ፍቅር ይዘው ፣ ፍቅር ሆነው አግኝተውን ነው ።
በፍቅር ነክተውን ነው ። ፍቅርን ሆነው ነው ። ኢየሱስ ክርስቶስ የሰበከውን ፍቅር በሙስሊሙ ፣ ያውም ተቀዳሚ ሐጂ ሙፍቲ ላይ አግኝተነው ይሆናል ። የሚገርመው ፣ አጅግ የሚገርመው ከአንዳንድ ሙስሊሞች በላይ በክርስቲያኖች ይወደዳሉ ።
ፌስቡኩን ብታዩት በእረፍታቸው ሀዘኑን ከገለጸው ሙስሊም የክርስቲያኑ ቁጥር ሳይበልጥ አይቀርም ። ለምን እንደሆነ አላውቅም ። ግን ይሄ እጅግ እጅግ መታደል ነው ። የሀይማኖት ሰባኪ ( አባትነት ) ነት ካጓጓኝ እንደ ተቀዳሚ ሐጂ ሙፍቲ ዑመር ኢድሪስ ሆኜ መገኘት አለብኝ ። የሌላ ሀይማኖት ተከታይም እኔን አለመውደድ እንዳይችል ማድረግ አለብኝ ። የእኔን ተከታይ ብቻ መስበክ አይበቃኝም ።
የእኔ ሀይማኖት ብቻውን ይጠበኛል ። የራስ ብቻ መሆንማ ተራና ቀላሉ መንገድ ነው ። የራስን መንጋ ብቻ መንዳት ብርቱ እረኛ አያደርግም ። የሀይማኖት ሰባኪ ( መሪ ) ከሆንኩኝ ለሁሉም ብርሐን መሆን አለብኝ ። ተቀዳሚ ሐጂ ሙፍቲ ዑመር ኢድሪስ በብዙዎቻችን ልብ ውስጥ መብራት ችለዋል ።
የአንድ መንጋ መሪ ብቻ አልነበሩም ። በልጅነታችን የራሳችን አባት እያለ የምንወዳቸው የሌሎች ጓደኞቻችን አባቶች የሉም ? መልካም አባት የሁሉም ነው ፤ የወለደውን የሚያሳድግ ብቻ አይደለም ። አባታችን እንደዚያ ነበሩ ። የቱም ክርስቲያን ሲወዳቸው ሙስሊምነታቸውን አክብሮ ነው ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሀይማኖት ተከታዮች ፣ ወንጌላውያን ፣ ካቶሊኮች በጋራ እኩል የሚወዱት የሀይማኖት ሰባኪ ( አባት ) የላቸውም ። ሦስቱም በጋራ የሚወዷቸውና የሚያከብሯቸው ተቀዳሚ ሐጂ ሙፍቲ ዑመር ኢድሪስ የተባሉ ሙስሊም ግን ነበሯቸው ። አሁን ግን ማንም ምንም የለውም ።
ተቀዳሚ ሐጂ ሙፍቲ ዑመር ኢድሪስ አንድ ሀይማኖተኛም የሀይማኖት መሪ በምድር ሊኖረው የሚገባውን ሕይወት ኖረውታል ። በኮቪድ 19 ወረርሺኝ ወቅት የጋራ ጸሎት ሲደረግ እናት ተቀዳሚ ሐጂ ሙፍቲ ዑመር ኢድሪስ ሲናገሩ ሰምታ ” እስላም ( በእሷ አነጋገር ” ናቸው እኚህ ሰውዬ ? ” አለቺኝ ። ” አዎ ” አልኳት ። ” ከአንደበታቸው እንዴት ያለ ማር ይዘንባል ? አነጋገራቸው ልብ ጋ ይደርሳል ። እግዚአብሔር እድሜ ይስጣቸው ። ” አለቺኝ ። ይሄ ተሰርቶ የሚገኝ ሳይሆን በጸጋ የሚሰጥ ነው ።
የሁላችንም የሰላምና የፍቅር አባት ተቀዳሚ ሐጂ ሙፍቲ ዑመር ኢድሪስ ነፍስዎ በሰላም ትረፍ ።
ከቴዎድሮስ ተ/አረጋይ
