ማኅበራዊ ተሳትፏችን ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል!

Date:

ኢትዮጵያውያን ለረጅም ጊዜያት ከምንታወቅበት በርካታ የወል ማንነት ውስጥ አንዱ እርስ በእርሳችን ያለን ማኅበራዊ መተጋገዝና ተሳትፏችን ነው፡፡ የምንታወቅበት የራሳችን የኾነ ማኅበራዊ ማንነት ያለን ሕዝቦች ነን፡፡ የዳበረ እሴትን ካካበቱ ሀገራት መካከልም ግንባር ቀደም ከሚባሉት ውስጥ ነን፡፡ የመረዳዳት፣ የመተሳሰብ፣ የመተጋገዝ፣ ሰው አክባሪነት፣ ሩሕሩሕነትና አዛኝነትም ከመገለጫዎቻችን ውስጥ ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡ በእምነት እሴትም የበለጸግን ሕዝቦች ነን፡፡ ሀገራችን ለዘመናት ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ ራሱን የቻለ ማኅበራዊ ስሪትም አላት፡፡ በተለይ እሴቶቿ በአንድ በኩል ሀገር ሲገነቡ በሌላ በኩል የሕዝቡን ሥነ ልቦናዊ ውቅር አንፀዋል፡፡ ማኅበራዊ ስሪታችን ኢትዮጵያዊ ሥነ ምግባር ከዓለም በተለየ መልኩ እንዲገነባም ከፍተኛ ሚናን ተጫውቷል፡፡ ይሉኝታና ነግ-በኔን የመሳሰሉ እራስን በሌላው ቦታ አስቀምጦ የማየት አስተሳሰቦች የኢትዮጵያውያን ስብዕና እንዲኾኑ አስችሏል፡፡ እንግዳ ተቀባይነት፣ እርዳታ የሚያሻቸው ሰዎችን ያለ ጥርጥር በቀናነት መርዳትም አንዱ በዘመናት በተገነባው እሴታችን ምክንያት የመጣ የማንነታችን መገለጫ ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ይህ ማንነታችን እየተሸረሸረ የመጣ ይመስላል፡፡ እንደሕዝብ ፖለቲካዊ የጥላቻ ሰንኮፎቻችን ወደ ማኅበራዊና ማንነታዊ ስብዕናችን ተሸጋግረው እየረበሹን ሳይመጡ አልቀረም፡፡ በመኾኑም ለዚህ ማኅበራዊ ልሽቀት እየዳረገን የመጣው ምንድነው የሚለውን ቆም ብሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ የእምነት ተቋማትና ልዩ ልዩ ሀገር በቀል ትውፊታዊ ማኅበራትም በዚህ ዙሪያ በጥልቀት መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይም በዓመት ከአምስት ጊዜ በላይ የምናከብራቸው ሃይማኖታዊ በዓላት የማኅበራዊ መስተጋብሮቻችን መገለጫዎቻችን ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ማኅበራዊ ተሳትፎ ዕለት በዕለት የሚገለጽ ሂደት ቢኾንም ሃይማኖታዊ እና ሀገራዊ በዓላት ደግሞ ተሳትፎዎቻችን ይበልጥ የሚገለጡበት ነው፡፡ ጎረቤት ከጎረቤቱ ዘመድ ከዘመዱ የሚደጋገፍበት ነው፡፡ መጪው አዲስ ዓመትም ይህ ማኅበራዊ አንድነታችን የሚታይበት ነው፡፡ ያለው ለሌለው የሚያካፍልበት እርስ በእርስ ተደጋግፎ ያለፈውን ዘመን ሸኝቶ ለአዲሱ ዘመን እራሱን በመልካም ምኞት አንጾ የሚገለጽበት ነው፡፡ በቅርቡ በተለያዩ አካባቢዎች የታዩትን ድንገቴ አደጋዎች ተከትሎ የታየው ማኅበራዊ መረባረብ በሁሉም ዘርፍ ላይ የተሳትፎ አድማሱን አስፍቶ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአንጋፋውን ጋዜጠኛ ድምጽ እንደገና እንስማ

ኑ ጥቂት ድጋፍ አድርገን ተስፋ እናለምልም ‼️ ባለ ወርቃማ ድምጹ...

ግዮን መጽሔት ዛሬ ቅዳሜ መስከረም 9 2019 ዓ.ም ገበያ ላይ ውሏል !!!

-የግዮን እንግዳ አምዳችን :- ‹‹ምንጩና ጸሐፊው በማይታወቅ መረጃ መመራት አደገኛ...

ሸኽ መሃመድ አል አሙዲ ተጨማሪ 40 ሺህ ሠራተኞች እንዲቀጠሩ አቅጣጫ ሰጡ

የMIDROC Investment Group ሊቀመንበር ሼክ መሃመድ ሁሴን አል...

የወርቅ ማዕድን ሠራተኛው ከመገደላቸው በፊት ቤተሰባቸው ከታጣቂዎች ጋር ያደረገው የመጨረሻው የስልክ ምልልስ

ማስጠንቀቂያ፡ ቀጥሎ የሚያነብቡት ታሪክ ሊረብሽዎት ይችላል በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ...