የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከአራት ቀናት በፊት ሥልጣን የለቀቁትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዳግመኛ ሾሙ።
የፈረንሳዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰባስሽን ሌኮርኑ አንድ ወር ሳይሞላቸው ሥልጣን መልቀቃቸው ይታወሳል።
“ሥራውን አልፈልገውም፤ ኃላፊነቴን ጨርሻለሁ” ብለው ከሥልጣን የለቀቁት ሰባስሽን ሌኮርኑ ወደ ሥልጣን መመለሳቸው አነጋጋሪ ሆኗል።
በድጋሚ የተሾሙት ጠቅላይ ሚኒስትር እስከ ሰኞ ድረስ የቀጣዩን ዓመት በጀት ለፓርላማ ማቅረብ አለባቸው።
የ39 ዓመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከማክሮን ዋነኛ ደጋፊዎች አንዱ ናቸው።
በኤክስ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት “ፕሬዝዳንቱ በሰጡኝ ኃላፊነት መሠረት የፈረንሳይን በጀት ከማቅረብ ባሻገር ፈረንሳውያን ለሚገጥሟቸው ችግሮች መፍትሔ አበጃለሁ” ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት “ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኜ ለመቀጠል የሚያስችል ሁኔታ አልተሟላም” ሲሉ ለሥልጣናቸው መልቀቅ ምክንያት የሆናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።