‹‹ሰላም ላይ ካልሠራን ቢዝነሱ ሊያንሰራራ አይችልም››

Date:

ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ

(የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት ዋና ፀሐፊ)

ከተቋቋመ በርከት ያሉ ዐሠርት ዓመታትን ያስቆጠረው፣ ‹‹የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት›› የኢትዮጵያን ንግድ በማዘመንና በማደራጀት ፤ ንግድና ኢንቨስትመንት ማስፋፋትን ዓቢይ ግቡ ያደረገ ነው፡፡ በሒደቱም የንግዱ ማኅበረሰብ ጥቅም እንዲጠበቅ በተለይም ደግሞ የመንግሥት ፖሊሲና መመሪያዎች የንግዱ ማኅብረሰብን ያማከሉ እንዲኾን በማድረግ ረገድ ትልቅ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ ምክር ቤቱ ባለፈው ዓመት ያካሔደውን የቦርድ አባላት ለውጥና ሌሎች ሪፎርሞች ተከትሎም እነኚህን የተቋቋመላቸውን ዓላማዎች ተፈጻሚ ለማድረግ በትጋት እየተንቀሳቀሰ መኾኑን፣ በዚሁ ለውጥ ወደ ምክር ቤቱ ፀሐፊነት የመጡት ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ ይናገራሉ፡፡ በዛሬው የግዮን ቆይታ ዓምዳችንም፣ ከእኚህ ወጣት ምሁርና የምክር ቤቱ አመራር ጋር በግል ሕይወታቸውና በንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤቱ እንቅስቃሴ ዙርያ የሚከተለውን ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ!  

ግዮን፡- በቅድሚያ ራስዎን ለአንባቢያን በማስተዋወቅ ቢጀምሩ?

ዶ/ር ቀነኒሳ፡- ቀነኒሳ ለሚ ደበላ እባላለሁ፡፡ የተወለድኩት ታህሳስ 13 ቀን 1978 በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጎንጎ በምትባል ትንሽዬ ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ እድሜዬ ለትምህርት እንደደረሰ ሰፈራችን በሚገኘው ጎንጎ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ድረስ ከተማርኩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜም ከእናቴ ተለይቼ ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ ጋሌሳ በሚባል ትምህርት ቤት ተማርኩ፡፡ 8ኛ ክፍል ሚኒስትሪ ጥሩ ውጤት አምጥቸ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ቡለን ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሬ በ1996 ዓ.ም ጅማ ዩኒቨርሲቲ ገባሁ፤ በ1998 ዓ.ም በአካውንቲንግ የመጀመሪያ ዲግሪዬን ያዝኩ፡፡

ከትምህርት ክፍሉም ከፍተኛ ውጤት በማምጣቴ በዩኒቨርሲቲው ረዳት ምሩቅ መምህር ሆኜ ተቀጠርኩ፡፡በዚህም ከ1999-2001 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው አገልግዬ በዚያው ዓመት በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቴን መማር ጀመርኩ፡፡ በ2002 ዓ.ም ትምህርቴን ጨርሼ እዚያው በዩኒቨርሲቲው ማገልገል ቀጠልኩ፡፡ ከሦስት ዓመት በኋላ በ2005 ዓ.ም ወደ ሕንድ ሀገር በመጓዝ በፑንጃቢ ዩኒቨርሲቲ በማኔጅመንት ጥናት የፒ ኤች ዲ ትምህርቴን በማጠናቀቅ በ2009 እዚያው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ማገለገል ቀጠልኩ፡፡ አዲስ አበባ እስከምመጣ ድረስም ጅማ ዩኒቨርሲቲ በአመራርነትም በአስተማሪነትም እያገለገልኩ ቆየሁ፡፡

የአንድ መምህር ኃላፊነት ማስተማር፣ የማህበረሰብ አገልግሎት መስጠትና መመራመር ነው፡፡ እኔ ግን ከዚያም በላይ በአስተዳደር ሥራ ላይ ነው በብዛት ያሳለፍኩት፡፡ ከተቀጠርኩ ከሁለት ወራት በኋላ ወደ አስተዳደር ሥራ ገባሁ፡፡ በዩኒቨርሲቲው በቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የክረምት ትምህርት ቢሮ ነበረች ፤ እሷን በመምራት ነው የአስተዳደር ስራን የጀመርኩ፡፡ከዚያም በኋላ ወደ ትምህርት ክፍል ኃላፊነት በመመደብ ማስተርስ ሳልሠራ የመጀመሪያ ዲግሪ አስተማሪዎቼን የመምራት እድል አገኘሁ፡፡ ሁለተኛ ዲግሪየን እንደያዝኩ ደግሞ የቢዝነስና ኢኮኖሚ ኮሌጅ የሥነ ምግባር መኮንን ሆኜ ተሾምኩ፡፡ አንድ ዓመት ሠርቼ ድጋሜ ሕንድ እስክሄድ ድረስ የዲፓርትመንት ኃላፊ ኾኜ ሠርቻለሁ። ከሕንድ ስመለስ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ምክትል ዲን ተደርጌ ተሾምኩ፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ሆኜ ለተከታታይ አራት ዓመታት አገልግያለሁ። በመቀጠልም የጅማ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች ጉዳይ ምክትል ፕሬዝደንት ሆኘ በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ ተሹሜ ለአራት አመታት አገለገልኩ። እዚህ እስክመጣ ድረስም በዚያው የኃላፊነት ሥራ ላይ ቆይቻለሁ፣

እንደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ የምንከተለው ፍልስፍና ‹‹የማህበረሰብ አቀፍ ትምህርት›› የሚባል ነው፡፡ በዚህ መሠረት የማኅበረሰብ አገለግሎት እና ምርምር ከአንድ መምህር የሚጠበቁ ሥራዎች ናቸው፡፡ ስለኾነም ጥናትና ምርምር ላይ ትኩረት አደርጋለሁ፡፡ በሰራኋቸዉም የምርምር ሥራዎች እና በሰጥኋቸው የማኅበረሰብ አገልግሎቶች በዩኒቨርሲቲው የእድገት እርከን መሠረት የዶክትሬት ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ በ4 ዓመት ማግኘት የነበረብኝን የተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ በአክሰሌሬትድ ፕሮሞሽን በ3 ዓመት ጊዜ ውስጥ ማሳካት ችያለሁ፡፡ በመቀጠልም በነበረኝ የማስተማር አበርክቶ፣ ባሳተምኳቸው ጥናቶች፣ ባበረከትኩት ማኅበራዊ አስተዋጽኦ እና በተቋማዊ አመራር ተሳትፎ መሠረት በጅማ ዩኒቨርሲቲ በኦርጋናይዜሽን ሊደርሺፕ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ጠይቄ እየተጠባበቅኩ እገኛለሁ፡፡

ግዮን፡- በጅማ ዩኒቨርሲቲ ከተማሪነት እስከ አመራርነት አልፎም ፕሮፌሰርነት ድረስ የነበርዎት ቆይታ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ቀነኒሳ፡- በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በጎ ነገር በቀናነት ማስተማር ነው፡፡ ጥሩ አስተማሪ መኾን አስፈላጊ ነው፡፡ እኔም ጥሩ አስተማሪ ነኝ ብዬ አስባለሁ፡፡ ከተማሪዎቼ ጋር የነበረኝ ቆይታ ድንቅ ነበር፡፡ በሕይወቴ በጣም ደስ የሚለኝ ክፍል ገብቼ አስተምሬ ስወጣ ነው። በዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልገሎት ውስጥ በጣም እሳተፋለሁ፡፡ በኋላ ባይቀጥልም ከተማሪዎቼ ጋር በመሆን ከቤት የሚጣል ደረቅ ቆሻሻ ወደ ማዳበሪያ የሚለወጥበትን መንገድ ሰርተናል። ይህም በሙዙምቤ ዓመታዊ መጽሔት ‹‹ምርጥ የቢዝነስ ሞዴል›› ተብሎ የተደነቀ ሥራ ለመስራት ችለን ነበር። ለወጣቶች ሥራ የሚፈጥሩ፣ የሥልጠናና ሌሎች ብዙ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን ሰርቻለሁ። ከዚህም በተጨማሪ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ፕሮጀክቶችን ለዩኒቨርሲቲው አበርክተናል። በርካታ ተማሪዎችን በማስተርስ እና ፒኤችዲ ውጭ ሀገር ልከን አስተምረናል፡፡ በተለይ ደግሞ ከኖርዌዩ ቢዝንስ ስኩል ጋር በመሆን ባሸነፍኩት ፕሮጀክት አሥር የሚሆኑ ተማሪዎችን ወደ ኖርዌይ ሀገር ሄደው የአጭር ጊዜ ሥልጠና እንዲወስዱ እንዲሁም የስታፍ አባላት ደግሞ የልምድ ልውውጥ እንዲወስዱ አድርጌያለሁ፡፡

አንድ ዩኒቨርሲቲ ‹‹ዩኒቨርሲቲ›› የሚባለው የሚሠራቸው ጥናቶችና ምርምሮች በዓለም አቀፍ ጆርናሎች መታተም ሲችሉ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የዩኒቨርሲቲውን ደረጃ ከፍ ያደርገዋል፡፡ እኔ  እስካሁን ከ60 በላይ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ አሳትሜያለሁ፡፡ በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ለማሳተም ክፍያ ስላለዉና ብዙ ጊዜ ስለሚጠይቅ በትምህርት ሚኒስቴር እውቅና ያለው የአገር ውስጥ ጆርናል ‹‹ሆርን ኦፍ አፍሪካ ጆርናል ኦፍ ቢዝንስ ኤንድ ኢኮኖሚክስ›› የሚባል ሐሳብ አቅርቤና አደራጅቼ በርካታ ጆርናሎች እንዲታተሙ አድርጌያለሁ፡፡ ሌላው አበርክቶዬ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ያገለገልኩበት የአስተዳደር ሥራ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ከሰባት በላይ በሚሆኑ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ አገልግያለሁ፡፡

ግዮን፡- ይህን ሁሉ አገልግሎት የሰጡበትን ተቋም ትተው ወደ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት ሲመጡ ሽኝትዎ እንዴት ነበር?

ዶ/ር ቀነኒሳ፡- በጅማ ዩኒቨርሲቲ ከተማሪነት እስከ ከፍተኛው ደረጃ አመራርነት ከ21 ዓመታት በላይ ቆይቻለሁ፡፡ ስለዚህ ከዚህ አከባቢ መራቅ በጣም ከባድ ነበር፡፡ ኾኖም ግን አሁንም ግንኙነቴ  አልተቋረጠም፡፡ በዩኒቨርሲቲ ሥርዓት ሰባት ዓመት ያገለገለ መምህር አንድ ዓመት እረፍት መውሰድ ይችላል፡፡ እኔም የመጣሁት በዚያ እረፍት ነው፡፡ ልጆቼና ባለቤቴ እዚያው ናቸው፡፡ የዶክትሬት ተማሪዎችም አሉኝ፡፡ ከ150 በላይ የማስተርስ ተማሪዎችን አማክሬ አስመርቄያለሁ፡፡ አሁን 15 ተማሪዎችን በዶክትሬት ደረጃ እያማከርኩ እገኛለሁ፡፡ ሦስቱን በዚህ ዓመት አስመርቄያለሁ፡፡ ዶክትሬት ካስመረኳቸዉ ተማሪዎቼ መካከል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አሉበት፡፡ ስለዚህ ግንኙነቴ አልተቋረጠም፡፡ ነገር ግን ጅማ ዩኒቨርሲቲ የሠራ ሰው ከዚያ ውጭ ለመሥራት የሚከብደው ነገር አለ፡፡ የጅማ ማኅበረሰብ ጥሩ የሆነ ማኅበረሰብ ነው፡፡ ፍቅር በተግባር የሚታይበት፣ የሚታመንና ሰላም ያለው ማኅበረሰብ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲም ውስጥ ያለው ማኅበረሰብ ሁሉ እንደ ቤተሰብ  ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ልዩ ፍቅርና መተሳሰብ ያለው ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን ከትምህርት ሥርዓቱ ውጭ ያለውን ዓለም መጋፈጥ አለብኝ ብዬ ወደዚህ መጥቻለሁ፡፡

ግዮን፡- ቤተሰቦችዎን ቢያስተዋውቁን ፤ በእርሶ ስኬት ዙሪያ ያላቸው እገዛስ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ቀነኒሳ፡- ባለትዳርና የሁለት ልጆች፡ አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት ልጅ አባት ነኝ። ባለቤቴ እዚያው ጅማ ዩኒቨርሲቲ የተማረች ነች። አብረን ነው የተመረቅነው፡፡ እሷም የሀይስኩል የኬሚስትሪ መምህር ነበረች፡፡ አሁን ቢዝነስ አጥንታ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በአካውንቲንግ እንዲሁም የማስተርስ ዲግሪዋን ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ተምራ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኛ ነች፡፡ ባለቤቴ በጣም ጎበዝ እና የተባረከች ሴት ነች፡፡ በጣም ታግዘኛለች፡፡ ለትምህርት ሕንድ በነበርኩበት ጊዜ ልጆቻችንንና በቤተሰቦቻችን ዙሪያ ኃላፊነት ወስዳ ስታስተዳድር ቆይታለች፡፡ በጣም ታታሪ ሠራተኛም ናት፡፡ የእሷ ጠንካራ መኾን ነው እኔን ለዚህ ያበቃኝ፡፡ እሷ ለእኔ እንደ እናቴ ነች፡፡ ብዙ ጊዜ በአካዳሚው ዓለም በመጻፍ ረጅም ጊዜ ያልፋል፡፡ እኔ እስከ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት የምጽፍ ከሆነ እሷም ሳትተኛ አብራኝ ትቆያለች፡፡ አሁን እዚህ ሆኜ እሷ የቤተሰቡን ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ ወስዳ እየመራች ነው፡፡ እሷ ለእናትና አባቷ የመጀመሪያ ልጅ ናት፡፡ እህትና ወንድሞቿን፣ የእኔን እህቶችና ወንድሞች፣ እንዲሁም እናትና አባቶቻችንን የመጠየቅና በሚያስፈልጋቸዉ ሁሉ የማገዝ ኃላፊነት እየተወጣች ትገኛለች፡፡ ለባለቤቴ ወ/ሮ በላይነሽ ፈየራ በጣም የተለየ አክብሮትና ምሥጋና አለኝ፡፡

ግዮን፡- በሕንድ የትምህርት ቆይታዎ ወቅት ለኢትዮጵያ ትምህርት ቢሆን ብለው የታዘቡት ነገር አለ?

ዶ/ር ቀነኒሳ፡- በሕንድ አገር በሦስት ዓመት ከግማሽ ነው ዶክትሬቴን ጨርሼ የመጣሁት ፤ በጣም ብዙ የቢዝነስ አሠራሮች አይቻለሁ፡፡ ተዟዙሬ የተለያዩ ከተማዎችንም ጎብኝቻለሁ፡፡ ሕንድ በጣም ብዝኃነት ያለባት ሀገር ነች፡፡ ብዙ ነገሮች የሚታዩባት ራሷ ዓለም ነች፡፡ የካፒታል ገበያ ሥርዓታቸው በጣም የተማርኩበት ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስለ ስቶክ ማርኬት ስንማር ክፍል ውስጥ እየገዙ  እና እየሸጡ ነው የሚያስተምሩን፡፡ ይሄ ማለት መምህራኑ የሚያስተምሩት በተግባር እየነገዱም ጭምር ነው፡፡ ተማሪውም ስቶክ ማርኬትን በንድፈ ሐሳብ ሳይኾን በተግባር ነው የሚማረው፡፡ በጣም የሚያስገርመኝ የነበራቸው የካፒታል ገበያ ሥርዓት ነው፡፡ የቢዝነስ ኦፕሬሽናቸው ዲጂታላይዝድ ነው፡፡ ብዙ ነገሮችን  በዲጂታል ነው የሚጠቀሙት ፤ ብዙ ውድድር ስላለ የግል ተቋማት ጠንካራ ናቸው፡፡

ለምሳሌ፦ በቴሌኮም ኢንዱስትሪ ውስጥ እነ ኤርቴል፣ ቮዳፎን እና ሌሎችም አሉ፡፡ የንግድ ሂደቱ ተወዳዳሪዎች በብቃት የሚመሩበት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አሁን የእኛ መንግሥት የጀመረው ነገር ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ድሮ እንደሚታወቀው ኢትዮ ቴሌኮም ብቻ ነበር፡፡ አሁን ግን ሳፋሪኮም በመግባቱ ኢትዮቴሌኮም በአገልገሎትም ይሁን በጥራት የተሻለ ሆኖ እንዲገኝ አድርጎታል፡፡ ይሄ አሠራር እኔ ሕንድ እያለሁ እዚህ ስላልነበረ እቆጭ ነበር፡፡

ግዮን፡- ወደ ኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በዋና ጸሐፊነት እንዴት መጡ?

ዶ/ር ቀነኒሳ፡- ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር እዚህ ከመጣሁ በኋላ አይደለም ግንኙነት ያለኝ፡፡ ጅማም እያለሁ ለጥናት ሥራዎች ወደ ማኅበረሰቡ ስወጣ ግንኙነት ነበረኝ፡፡ ለምሳሌ፦ በፒ ኤስ ዲ ስፖንሰር የተደረገና በኦሮሚያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት አማካኝነት በግሉ ዘርፍ ዙሪያ ጥናት አጥንቼ ነበር፡፡ የቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ዲን ኾኜ ተወዳድሬ ከባልደረቦቼ ጋር አሸንፌ የሰራሁት ጥናት ነው፡፡ ጥናቱ የሚያተኩረው የግሉ ዘርፍ ያለበት የታክስ ተግዳሮት ላይ ነበር፡፡ ጥናቱ በቦታ ደረጃ ጅማን ጨምሮ ወሊሶ፣ አምቦ፣ ነቀምትና ኢሊባቡር አካባቢ ትኩረት ያደረገ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ወደዚህ ምክር ቤት ስመጣ ያን ጥናታችንን አግኝቼዋለሁ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ከጅማ ቻምበር ጋር በደንብ እንሠራ ነበር፡፡ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የማኅበረሰብ  አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ለምሳሌ፦ የሕግ ትምህርት ቤት ነጻ የሕግ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የጤና እንስቲትዩትም ነጻ የጤና አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ስለዚህ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ኾኜ ነጻ የቢዝነስ ማማከር አገልግሎት እንዲሰጥ አደረኩ፡፡ በዚህም ከጅማ ቻምበር ጋር ስምምነት ተፈራረምን፡፡ ቢሮ እንዲከፈት በማድረግ እና ቢሮውን በማደራጀት መምህራንን አስመደቤ ነጻ የማማከር አገልግሎት እንዲሰጥ አደረኩ፡፡ ነገር ግን በኋላ አገልግሎቱ ተቋረጠ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው ከቻምበር ጋር አብሮ መሥራት እንደሚገባ ያስተዋልኩ፡፡ በኋላም አዲሱ የሥራ አመራር ቦርድ ወደ ሥራ ሲገባ በሰዎች ተጠቁሜ ወደዚህ እንድመጣ ተጋበዝኩ፣ ቃለ-መጠይቅም ሊያደርጉልኝ እንደሚሹ ነገሩኝ፡፡ ቃለ-መጠይቁን ተደርጌ ወደዚህ ሥራ መጣሁ፡፡ ከጅማ ቻምበርና ከኦሮሚያ ቻምበር ጋር መሥራቴ፣ የቻምበር ሲስተምን መከታተሌ እንዲሁም እንደ ቢዝነስ ተማሪና ተመራማሪነቴ ካነበብኳቸውም በመነሳት ተማርኬ ወደዚህ ሥራ ልመጣ ችያለሁ፡፡

ግዮን፡- ነጋዴውን ከዓለም አቀፍ የነጋዴ ማህበራት ጋር ለማገናኘት ምን ያህል ጥረት እያደረጋችሁ ነው?

ዶ/ር ቀነኒሳ፡- የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በ1939 ዓ.ም ሲቋቋም ትልቁ የተሰጠው ተልዕኮ የኢትዮጵያን ንግድ በማዘመንና በማደራጀት ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ማድረግ፣ እንዲሁም የንግዱ ማኅበረሰብ ጥቅም እንዲጠበቅ በተለይም ደግሞ የመንግሥት ፖሊሲና መመሪያዎች የንግዱ ማኅብረሰብን ያማከሉ እንዲኾኑ ማድረግ ነበር፡፡ ይህንን ዓላማ ይዞ የመጣው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የሚጠበቀውን ያህል ባይኾንም ብዙ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡

እኛ ከመጣን በኋላ ንግድና ኢንቨስትመንት ከማስፋፋት አኳያ ከውጭ ሀገር ኤምባሲዎች ጋር ለመሥራት እየሞከርን ነው፡፡ በጣም ብዙ ኤምባሲዎችም ጎብኝተውናል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት እራሱን ለዉጦ ነው የመጣው፡፡ ሐምሌ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ አዲስ ቦርድ በመሰየምና አዲስ ፕሬዝደንትና ምክትል ፕሬዝደንት በመምረጥ፣ አዲሱ ቦርድም እኔን በዋና ጸሐፊነት በመሰየም በአዲስ መንፈስና ተነሳሽነት ነው እየሠራ የሚገኘው፡፡ ስለዚህ በርካታ የዓለም አቀፍ ተቋማት ወደ እኛ እየመጡ ነው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ባዛሮችና ልዩ ልዩ ዝግጅቶች በተለያየ ጊዜ በተለያዩ ቦታዎች እንዲካሄዱ እያደረግን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሥር 21 አባላት አሉ፡፡ ሁሉም ክልሎች የእኛ አባሎች ናቸው፡፡ የሴክተር ዘርፎችም ወደ 6 የሚኾኑ አሉ፡፡ አንድ ብሔራዊ የዘርፍ ማኅበርም አለ፡፡ እነዚህ 21 አባላት በራሳቸው የመሄድ ሥልጣን አላቸው፡፡ እኛ ሁኔታዎች እንዲመቻቹላቸዉ እናግዛቸዋለን፡፡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመሆን ሁኔታዎችን ምቹ እናደርግላቸዋለን፡፡ በዚህ ረገድ ጥሩ የሄዱም ወደኋላ የቀሩም ክልሎች አሉ፡፡ ስለኾነም ድክመት የታየባቸውን በማቀናጀት አብረው እንዲሠሩና እንዲጠናከሩ እያደረግን ነው፡፡

ከልማት አጋሮቻችን ጋር በመኾንም የተለያዩ የሥልጠና መርሐ-ግብሮችን በማውጣት ሥልጠናዎችንም እየሠጠን ነው፡፡ አሁን እየገባንበት ያለው የንግድ ሥርዓት በጣም ውብስብና ብዙ እውቀትን የሚጠይቅ ነው፡፡ በእኛ ሀገር የንግዱ ሥራ በእውቀትና በሳይንስ ሲመራ ነበር ለማለት ያስቸግራል፡፡ አሁን ደግሞ የተለያዩ ዓለምአቀፋዊና አህጉራዊ ገበያዎች ውስጥ ገብተናል፡፡

ለምሳሌ፦ እንደ ሀገር የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ልንኾን ነው፡፡ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣናም አባል ነን፡፡ ይሄ ገበያም አፍሪካን የሚያስተሳስር ትልቅ ገበያ ነው፡፡ በዚህ ገበያ ውስጥ በእውቀት እና በሳይንስ መሪነት ካልገባን ገበያው ውስጥ ተዋናይ መሆን ከባድ ነው፣ ነጋዴውም ተወዳዳሪ ኾኖ ሊወጣ አይችልም፡፡ መንግሥት አሁን ላይ የካፒታል ገበያን አስጀምሯል፡፡ የካፒታል ገበያ በራሱ በጣም ትልቅ የኾነ ውስብስብ ገበያ ነው፡፡ ይህ ገበያ እውቀትን ይፈልጋል፡፡ የአደጋ ትንተና መኖር አለበት፡፡ ትክክለኛ ቦታ ላይ ገንዘቡን ዘርቶ ተገቢውን ዋጋ የማያገኝ ከኾነ በዚህ ገበያ ውስጥ ሊቀጥል አይችልም፡፡ ስለሆነም በዚህ ዙሪያ እየሰጠናቸው ያሉ ሥልጠናዎች አሉ፡፡ ወደፊትም ከልማት አጋሮቻችን የገንዘብና ሌሎች ድጋፎችን በማፈላለግ ቀጣይነት ያለው ሥልጠና ለመስጠት ፕሮጀክት አዘጋጅተን የማሣመን ሥራ እየሰራን ነው፡፡

ግዮን፡- ከኤምባሲዎችና ከተለያዩ የውጭ ተቋማት ጋር ያላችሁ ግንኙነት ያለው ተስፋ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ቀነኒሳ፡- ከተለያዩ ኤምባሲዎች ጋር እየተነጋገርን ነው፣ ወደፊትም ከሌሎች ጋር የመወያየት እቅድ አለን፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ ጥሩ ተስፋ አለ፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እራሱን እንደ አዲስ አደራጅቶ መምጣቱን ተከትሎ በእነርሱ በኩልም አብሮ ለመሥራት ከፍ ያለ ጉጉት አለ፡፡ አሁን የመጣው ቦርድ በእውቀትም ይሁን በሥራ ተነሳሽነቱ በእጅጉ የተሻለ ነው፡፡ ስለዚህ የልማት አጋሮቻችንም የተሻለ ለውጥ እንደምናመጣ ትልቅ ተስፋ አላቸው፡፡

ከሰሞኑ ከፈረንሳይ እና ከሌሎችም ሀገራት ከመጡ የልማት አጋሮቻችን ልዑካን ጋር ልዩ ውይይት አድርገናል፡፡ ከሁሉም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችም ጋር እየሰራን ነው። የንግድ ዘርፉ ላይ ጫና ሊያደርጉ በሚችሉ ለምሳሌ፦ ሰላም ላይ እየሠራን ነው፡፡ ከሰሞኑ ከሰላም ሚኒስቴር እና ከሰንቴር ፎር ኢንተርናሽናል ፕራይቬት ኢንተርፕራይዝ (CIPE) ጋር በመተባበር ባይነቱ ልዩ የሆነ ትልቅ ወርክሾፕ አካሂደናል፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ የሰላም ጉዳይ ስለሚያሳስበው እና ንግድ ያለሰላም ስለማይታሰብ ‹‹ቢዝነስ ለሰላም›› በሚል ልዩ ውይይት ነው ያደረግነው። አዲሱ ቦርድ ከማኔጅመንቱ ጋር ተቀራርቦ በመሥራቱ ትልቅ እምርታዎችን እንዲያመጣ እያደረገ ነው፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ መመሥረቱና እስካሁንም ለረጅም ዓመታት መንቀሳቀሱ እንደቀላል የሚታይ ባይሆንም መሥራት የሚጠበቅበትን ሰርቷል ብለን አናምንም፡፡ እናም አሁን ላይ በአዲሱ ቦርድና ማነጅመንት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ለልማት አጋሮቻችን ተስፋ የሰጡ ናቸው፡፡

ግዮን፡- የንግድ ማኅበረሰቡ ከመንግሥት የንግድ ፖሊስና መመሪያዎች ጋር በተያያዘ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች ለመፍታት እንዲሁም አዳዲስ ደንቦች ሲወጡ ከማሳወቅ አኳያ በእናንተ በኩል እየተሠራ ያለ ነገር ካለ፣ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ዶ/ር ቀነኒሳ፡- የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በግሉና በመንግሥት መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ በማገናኘት የተሳለጠ የአሠራር ስርዓት እንዲኖር እያገዘ ነው፡፡ ጥሩ የንግድ አካባቢ ተፈጥሮ የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚው መሪ እንዲኾን ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡ አሁን ላይ በተለይ ከጂዲፒ አንፃር በኢኮኖሚ  ውስጥ የግሉ ዘርፍ ድርሻ 15% አካባቢ ነው፡፡ መሪ ኾነ ማለት ደግሞ ጂዲፒ ውስጥ ቢያንስ ከ50% በላይ ሊኖረው ይገባል፡፡ አሁን ያለው የሚያሳየው ሥራ እንዳልሠራን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ቦርዱ ላይ ለውጥ የተደረገው፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው ቦርድ ያለ ምርጫ ሰባት ዓመት የቆየ ነው፡፡ ቦርዱ ሕጋዊ አይደለም የሚልም ትችት ይቀርብበት ነበር። እነዚህ ኹነቶች ናቸው ለአዲሱ ቦርድ መዋቀር ዋና ምክንያቶቹ፡፡

ስለዚህም ከመንግሥት ጋር ተቀራርበን ሰርተን የመንግሥት ፖሊሲ፣ ሕግና ደንቦች የግል ዘርፉን ያገናዘቡ እንዲኾኑ ለማድረግ እየሠራን ነው፡፡ ነገር ግን የንግድ ዘርፉም በበኩሉ ታማኝ ኾኖ መቅረብ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው የመንግሥት ፖሊሲ የግል ሴክተሩን ወደኋላ አድርጎ የመንግሥት ሴክተርን ያስቀደመ ነበር፡፡ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ትርክታችን እራሱ ልማታዊ መንግሥት ነው፡፡ ስለዚህ ልማቱን የሚመራው መንግሥት በመኾኑ የግል ዘርፉ ከኋላ ነው ያለው፡፡ አሁን ያ ነገር ተቀይሮ ለግል ዘርፉ የተሻለ ትኩረት ተሰጥቶት ይገኛል፡፡ እኛ ደግሞ በዚህ ላይ ጠንከር ብለን የሚወጡ ሕግና ደንቦች የግል ዘርፉን ማዕከል ያደረጉ እንዲሆኑ ለማድረግ እንጥራለን፡፡ የጀመርናቸው ሥራዎችም አሉ፡፡ የተለያዩ ውይይትና ንግግሮችን እያደረግን ነው፡፡ እዚህ ላይ በደንብ ሠርተን ካስቀጠልን መጪው ጊዜ የተሻለ ይኾናል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እንደስሙ ሆኖ እራሱን ችሎ መቆም ከቻለ መንግሥትም ይፈልገዋል፡፡ መንግሥት ራሱ እንደ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተለያዩ ደንብና ሕጎች ሲወጡ ተሳተፉ ብሎ ይጠራናል፡፡ ፈላጊ መሆናችን ቀርቶ ተፈላጊ እንሆናለን፡፡ እስከአሁን የነበረው የምክር ቤት የአሰራር ሥርዓት ግን ተፈላጊ እንዳንሆን አድርጎናል፡፡

ግዮን፡- የግል ንግዱ ዘርፍ ከመንግሥት ጋር የሚኖሩትን ቅሬታዎች ለመፍታት በእናንተ በኩል ያለው ዝግጁነት ምን ይመስላል?

ዶ/ር ቀነኒሳ፡- የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አንዱ ኃላፊነት የግሉ ዘርፍ ያለዉን ጥያቄ ወይም ቅሬታ ለመንግሥት ፊት ለፊት የሚያቀርብበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። ይህን ለማድረግ በመጀመሪያ የግል ዘርፉ የሚያቀርባቸውን ቅሬታዎች በጥናትና ምርምር እንለያለን፣ ከዚያም ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እንዲቀርቡ እናደርጋለን። ለምሳሌ፦ እስካሁን 119 ጥያቄዎች መኖራቸውንና መመዝገባቸውን ከሰነድ ላይ አይቻለሁ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 87 ጥያቄዎች በትክክል በፖሊሲና ደንብ መሠረት መንግሥት እንደመለሰ በክትትል ለይተናል፡፡ ያልተመለሱት ደግሞ ይለዩና እንዲመለሱ ምክር ቤታችን ጫና ያደርጋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተፅዕኖ ፈጣሪ ኾኖ ከወጣ የግሉ ዘርፍ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ያገኛሉ፡፡

ግዩን፡- በአሁኑ ወቅት የሚታየውን የገበያ አለመረጋጋት ለመቅረፍ በእናንተ በኩል ምን እያደረጋችሁ ነው?

ዶ/ር ቀነኒሳ፡- በሀገራችን ላለው ገበያ አለመረጋጋት ሁለት ሦስት ሁኔታዎችን ማየት አስፈላጊ ነው። የመጀመሪያው ዓለማቀፋዊ ቀውስ ነው፡፡ ለምሳሌ፦ የኮሮና ቫይረስ መምጣት የዓለም ገበያን አናግቶታል፡፡ የዚያ ውጤት ደግሞ እያደጉ ባሉ ሀገራት ላይ ያለው ጫና በጣም ከባድ ነው፡፡ ሁለተኛው ዓለም አሁን ባለችበት ሂደት ጦርነቶች በዓለም ደረጃ በዝተዋል፡፡ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት፣ የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት እንዲሁም እንደ ሀገር እኛ የነበርንበት ጦርነትም ተጠቃሽ ነው፡፡ ይኼ ሁኔታ ገበያው ላይ የራሱ ተፅዕኖ አለው፡፡ ግጭት ባለበት ኢኮኖሚ መረጋጋት አይችልም፡፡ ንግድና ኢንቨስትመንት ከግጭት ጋር አብረው አይሄዱም፡፡ ሰው በየአቅሙ የንግድ ልውውጥ ማድረግ አይችልም፡፡

ሰላም ከሌለ ሌብነትና ብልሹ አሠራር ይበረክታል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አንዱ ሥራ ይህን ያልተረጋጋውን የሸማቹ እንቅስቃሴ ማረጋጋት ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ያሰብነው ደግሞ ሰላም ላይ መሥራት ነው፡፡ ሰላም ሲጠፋ ሁላችንም እኩል እንጎዳለን፡፡ ለምሳሌ፦ ጦርነት ሲመጣ መንግሥትም ግለሰብም ሁሉም ይጎዳል፡፡ ሰላም የማምጣት ሥራን ደግሞ ሁልጊዜ ለመንግሥት መተው ተገቢ አይደለም። መንግሥት ሰላም ማውረድ አለበት እንላለን እንጂ እኔ ለሰላም የድርሻዬን ልወጣ አንልም፡፡

የሰላም ጉዳይ እንደገጠር ሳር ቤት ነው፡፡ የገጠር ሳርቤት ክዳን ሲሠራ ከአንዲት ዘለላ ሳር ጀምሮ ነው፡፡ ከአንድ ቤት ጣራ ክዳን ላይ አንድ ሳር እየተመዘዘ በተጣለ ቁጥር ቤቱ ዝናብ ማፍሰስ ይጀምራል፡፡ የሰላምም ጉዳይ እንደዚሁ ነው፡፡ አንድ ግለሰብ ሰላም ለማምጣት የራሱ ሚና አለው።

ሰዎች ተሰባስበው ለሰላም የሚሠሩ ከሆነ ሰላምን ማምጣት ይችላሉ፡፡ ሰላም ሲጠፋ በጋራ የምንጎዳ ከሆነ ሰላም ለማምጣትም በጋራ መቆም ይኖርብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ የንግድ ተቋማት ትልቁን ድርሻ መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም የግሉ ዘርፍ ሰላም ከጠፋ ቢዝነሱ በጣም ስለሚጎዳ ነው፡፡

አንዳንዴ በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ የግሉ ዘርፍ የግጭት ቀስቃሽ ኾኖ ይስተዋላል፡፡ ይህ ማለት የጦር መሳሪያን የሚሸጥ ተቋም ግጭት እንዲኖር ይፈልጋል፡፡ በዓለም ውስጥ ከ3 እስከ 4 በመቶ የሚሆነው ንግድ ከጦር መሣሪያ የሚገኝ ንግድ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተናጠል የግጭት መንስኤ የሆኑ አካላትም ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ በዘመናችን ትልቅ የግጭት መንስኤ የኾነው ማኅበራዊ ሚዲያ ነው፡፡ ሚዲያ ላይ ግለሰቦች በአፋቸው ይገድላሉ፣ ሌሎች ደግሞ ላይክ ያደርጉላቸዋል፡፡ ሁለቱ በጋራ ገንዘብ ይሠራሉ፡፡ ስለዚህ ይህን መሰል ሰላም ነሺ ነገሮችን በመከላከል ረገድ የግሉ ዘርፍ ትልቅ ሚና መጫወት ይችላል፡፡ ለዚህም ነው ሰሞኑን ከሰላም ሚኒስቴርና ከተለያዩ የልማት አጋሮቻችን እንዲሁም ከግሉ ዘርፍ አካላት ጋር ፍሬያማ ውይይቶችን ያደረግነው።

ከዚህም በተጨማሪ በሰላም ጋዜጠኝነት ላይ ሥልጠና እየሰጠን ነው፡፡ ጋዜጠኛው እንዴት ሰላምን ሰብኮ ቢዝነሱ ሊያንሰራራ ይችላል የሚለውን እያሠለጠንን ነው፡፡ በአጠቃላይ እንደ ፕሮጀክት የቀረፅነው የ5 ዓመት እቅድም ‹‹ቢዝነስ ለሰላም›› የሚል ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ተቀርፆ አልቋል፡፡ ሰላም ላይ ካልሠራን ቢዝነሱ ሊያንሰራራ አይችልም በሚል ነው እየሠራን ያለነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የሚጠበቅበትን ሁሉ ሰርቶ ጨርሷል ባልልም በርካታ ሙከራዎችን እያደረገ ነው፡፡

——-

ማስታወሻ፡- ውድ አንባቢያን ከዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ ጋር የነበረን ቆይታ በዚህ አልተጠናቀቀም፡፡ የመጨረሻውን ክፍል በሚቀጥለው ዕትም ይዘን የምንመለስ ይኾናል፡፡

ግዮን መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር 222 የካቲት 8 2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ኢትዮጵያ የ1 ቢሊዮን ዶላር የቦንድ ዕዳዋን ለማዋቀር ስታደርግ የነበረዉ ድርድር ያለ ስምምነት ተቋረጠ

የኢትዮጵያ መንግሥት በ2024 ዓ.ም. ዋናው ዕዳ የሚከፈልበት የአንድ ቢሊዮን...

የትግራይ ኃይል አባላት ሰልፍ ዛሬም በሌላ አቅጣጫ ቀጥለዋል

በመቐለና ዙሪያዋ የሚገኙ የትግራይ ኃይል አባላይ ትናንት ሰኞ ጥቅምት...

የምርመራ ኬዝ ስለሆነ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል

ተማሪ ሊዛ ደሳለ የተባለች ወጣት ሰሞኑን በደሴ ከተማ “...

ስቲሊ አር.ኤም.አይ ላለፉት አራት ዓመታት የፕላቲኒየም ሸልማት ተሸላሚው

የ2017 በጀት ዓመት 7ኛው የታማኝ ግብር ከፋዮች ዕውቅና እና...