ሲፒጄ በሶማሌው ጋዜጠኛ ላይ የተላለፈው እስራት “እንዳሳዘነው” ገለጸ

Date:

ዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄ የጅግጅጋ ቴሌቪዥን ኔትወርክ መስራች ጋዜጠኛ አህመድ አውጋ “ባልጻፈው የፌስቡክ ጽሁፍ” ምክንያት የሁለት ዓመት እስራት በመፈረዱ ማዘኑን ገለጸ።

ሲፒጄ ትናንት ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ አህመድ በ2012 ዓ/ም የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ በመተላለፍ ወንጀል ግንቦት 14 ቀን 2017 ዓ.ም በጅግጅጋ በሚገኘው የፋፈን ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብሏል።

እንደ ሲፒጄ ገለጻ፤ አህመድ ከዚህ ቀደም ልጃቸው የፖሊስ ድብደባ ደርሶበት ህይወቱ ማለፉን ከገለፁ ግለሰብ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ እንዲሁም በፌስቡክ ገጽ ላይ ከወጣ “አስተያየት” ጋር ተያያዥነት እንዳላቸው በተገለጹ ክሶች ምክንያት ከሚያዚያ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ ቆይቷል።

ጋዜጠኛ አህመድ አውጋ መጀመሪያ ላይ የወንጀል ድርጊቶችን በመቀስቀስ ተከሶ የነበረ ቢሆንም፣ ሲፔጄ በኋላ ላይ በተመለከተው የክስ መዝገብ ላይ ክሱ “ሀሰትኛ መረጃዎችን ማሰራጨት እና ህዝብን ማነሳሳት” ወደሚል መቀየሩ ተመላክቷል።

አህመድ ሚያዝያ 9 ቀን 2017 ዓ.ም በፌስቡክ ድረ-ገጹ ላይ “የክልሉን ምርጫ የውሸት ምርጫ በማለት ጠቅሷል”፣ “የክልሉ መንግስት ባለስልጣናት ህዝቡን በግዞት ይዘዋል” እንዲሁም “የተወሰኑ ወረዳዎች በጥቂት ግለሰቦች ቁጥጥር ስር ተይዘዋል” ሲል መጻፉን በክስ መዝገቡ ላይ ሰፍሯል ተብሏል።

“ግድያ እና ሞት እንጂ ፍትሕ የለም” በማለት ህዝብን አነሳስቷል ተብሎም ተከሷል።

ሆኖም እንደ ሲፒጄ ገለጻ፣ አህመድ ጥፋተኛ ተብሎ የተገኘበት ምክንያት በዋነኝነት ሚያዝያ 12 ቀን 2017 ዓ.ም የተለጠፈ ጽሁፍ ላይ የተመሰረተ ሲሆን፤ ልጥፉ ደግሞ “በግልጽ ከሌላ የፌስቡክ ገጽ የመጣ” እና አህመድ ታግ የተደረገው ወይም ስሙ የተጠቀሰው በዚያ ጽሁፍ ላይ ብቻ እንደሆነ ተጠቁሟል።

አህመድ ሚያዝያ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ከጻፋቸው ጽሁፎች ውስጥ አንዳቸውም በክስ መዝገቡ ላይ የተዘረዘሩትን መግለጫዎች የሚያመለክቱ አለመሆናቸውን የገለጸው ሲፒጄ ማስረጃዎቹን ሲገመግም የኦንላይን ሚዲያ የሆነው ቮስ ቴቪ (VOSS TV) ባካሄደው ትንተና ላይ ተደግፎ መሆኑን ገልጿል።

የዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (ሲፒጄ) የአፍሪካ ፕሮግራም ዳይሬክተር አንጄላ ኩዊንታል፣ በአህመድ ላይ የተላለፈው ቅጣት “ኢትዮጵያ በፕሬስ ነጻነት ላይ የምታደርገው ጥቃት መጨመሩን ያሳያል” ብለዋል። አክለውም፣ “ይህ እሱ ባልጻፈው ጽሑፍ የተላለፈ ፍርድ ነው” ያሉ ሲሆን፣ ባለሥልጣናት “ተቃዋሚ ድምጾችን ለማፈን የሕግ ስርዓቱን ከመጠቀም እንዲታቀቡ” ጥሪ አቅርበዋል።

ሲፒጄ የአህመድን ጉዳይ በኢትዮጵያ በመገናኛ ብዙኃን ላይ እየደረሰ ካለው “ሰፊ አፈና” ጋር አያይዞታል። ድርጅቱ “ቢያንስ ስድስት ሌሎች ጋዜጠኞች” በሚያዝያ ወር ብቻ መታሰራቸውን ገልጾ፤ ባለሥልጣናትም በሀገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ተቆጣጣሪ በሆነው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን (EMA) ላይ ቁጥጥራቸውን እያጠናከሩ ነው ሲል ተናግሯል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ መሃመድ በበኩላቸው ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም ከቢቢሲ ሶማሊ አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ሰዎች በኦንላይን በጻፉት ጽሁፍ ብቻ እየታሰሩ መሆናቸውን አስተባብለዋል።

አክለውም አንድ ጋዜጠኛ፣ አንድ የቀድሞ ባለሥልጣን እና ሁለት አክቲቪስቶች በአጠቃላይ አራት ግለሰቦች “የጸጥታ አካላትን ስም በማጥፋት”፣ “ስለ እስር ቤት ሁኔታ የሐሰት መረጃ በማሰራጨት” እና “የእስረኞችን ሞት ተጠቅመው ሕዝብን በማነሳሳት” ወንጀል ተጠርጥረው መታሰራቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በሶማሌ ክልል ያለው የፍትህ ስርዓት “ነጻ እና ገለልተኛ” እንደሆነ ገልጸዋል።

ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪ (RSF) በጎርጎሮሳውያኑ 2025 የዓለም የፕሬስ ነጻነት መረጃ ጠቋሚው ኢትዮጵያን ከ180 ሀገራት ውስጥ 145ኛ ደረጃ ላይ በማስቀመጥ ለመጀመሪያ ጊዜ “በጣም አሳሳቢ” በሚለው ምድብ ውስጥ አካቷታል።

ይህም እየጨመረ በመጣው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት፣ በተገደበው የፕሬስ ነጻነት እና በተዳከመው የሚዲያ ኢኮኖሚ ምክንያት እንደሆነ ገልጿል።

የጋዜጠኞች ጥበቃ ኮሚቴ (CPJ) ከዚህ ቀደም ይፋ ባደረገው የ2024 የጋዜጠኞች እስር ሪፖርት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጋዜጠኞችን በከፋ ሁኔታ ከሚያስሩ ሀገሮች መካከል መካተቷንና በእስር ላይ ካሉ ስድስት ጋዜጠኞች መካከል አምስቱ የሞት ቅጣት ሊያስከትል የሚችል የ”ሽብርተኝነት” ክስ ተመስርቶባቸዋል ሲል ማስታወቁ አይዘነጋም።

አስ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የህወሓት የቃላት ጦርነት ንሯል።ይዋጉ ይሆን?

ሶስቱም ኃይላት የጦር ኃይላቸዉን እያጠናከሩ፣ አዳዲስ ተዋጊ እየመለመሉ መሆናቸዉ...

የሐማስ ታጣቂዎች ከእስራኤል ጋር በመተባበር የተከሰሱ ሰባት ሰዎችን ገደሉ

ሰኞ እለት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተዘዋወረ ያለ ቪዲዮ እንደሚያሳየው...