ቀውስ የወለደው የኢትዮጵያውያን ስደት!

Date:

‹‹ስደት›› በተለምዶ ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ መፍለስ ማለት ነው። ሰዎች ከቤታቸው፣ ከትውልድ አካባቢያቸው በምስጢር ወይም በገሀድ ለቀው ወደ ሌላ ሥፍራ የሚያደርጉት ፍልሰት ነው። ስደት ዓለማቀፋዊ ነው፡፡ በዓለማችን የመጀመሪያው ስደት፣ በታላቁ መጽሐፍ ተሰንዶ የምናገኘው የያዕቆብ ልጆች ስደት ነው፡፡ ለያዕቆብ ልጆች ስደት ዐቢይ ምክንያት ተደርጎ የቀረበው ደግሞ የድርቅ መከሰት ነው፡፡ ስለኾነም ስደት በልዩ ልዩ ምክንያቶች ይከሰታል ማለት ነው፡፡ እንደ ጦርነት፣ ድርቅ፣ አለመረጋጋት፣ ፖለቲካዊ መገለልና የኑሮ ግሽበትና ሥራአጥነትን መሠረት ያደረጉ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የስደት ዋነኛ መንስኤዎች ናቸው፡፡ ስደተኞች አብዛኛውን ጊዜ የሚፈልሱት የተሻለ ሕይወት ወይም ደህንነት እናገኝበታለን ብለው ወደሚያስቡበት ሀገር ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ስደት በተለይ በዘመናዊው ዓለም ውስጥ ትልቅ ጉዳይ እየኾነ መጥቷል፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በተለይም እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓይነት ተቋማት ስደተኝነትን ለመግታት ከፍ ሲልም ስደተኞችን ለመርዳት በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውኑ ይታያል፡፡

ስደት ሁለት ዓይነት መንገዶች አሉት፡፡ አንደኛው ሕጋዊ ስደት የሚባለው ሲኾን ሁለተኛው ደግሞ ሕገወጥ ስደት ነው፡፡ ዜጎች ከአንድ ሀገር ወደሌላ ሀገር በሕጋዊ መንገድ ሲጓዙ ደኅንነታቸው የተጠበቀና መንግሥታዊ እውቅና ያለው ሲኾን በአንጻሩ በተለያየ ምክንያት በባሕርና በየብስ ከሀገር ወደ ሀገር ሽግግር ሲያደርጉ ደግሞ ለበርካታ መጉላላትና ሕይወትን ለማጣት ጭምር ይዳረጋሉ፡፡ አሁን ላይ አስቸጋሪ እየኾነ የመጣውም የስደት ዓይነት ይኸው ዓይነት መኾኑ በብዙ መልኩ ይነገራል፡፡ ይህን የስደት ዓይነት ለመግታትም ከፍ ሲል እንደተገለጸው በተለይ ያደጉ ሀገራትና ትላልቅ ተቋሞቻቸው በርካታ ሥራዎች ሲያከናውኑ ይታያል፡፡

ኢትዮጵያም ከፍተኛ ተሰዳጆች ካሉባት ሀገራት ውስጥ ግንባር ቀደሟ ነች፡፡ ኢትዮጵያውያን ሕገወጥ ስደተኞች በየጊዜው ለእንግልትና ሞት ሲዳረጉባት መስማት የተለመደ ነው፡፡ በተለይም ያለፉትን ስድስት ዓመታት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በበርካታ የዓለም ሀገራት ቀድሞ ከነበረው በእጥፍ እየጨመረ መምጣቱ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ ትልቁ ፈተና ደግሞ በሕገ-ወጥ መንገድ ተሰደው ከተመለሱ በኋላ ለዳግም ሕገወጥ ስደት መዳረጋቸው ነው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር የወጡና ፈቃድ ያላቸው እንዲሁም ያለፈቃድ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ከአረብ ሀገራት ወደ ሀገር የመመለስ ሥራ ቢሰራም፤ ድጋሚ በሕገ-ወጥ መንገድ መሰደዳቸው ተግዳሮት እንደኾነበት የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር በመሰደድ ወደ ዐረብ ሀገራት ያቀኑ ዜጎች ለእስር፣ ለእንግልት እና ለተለያዩ ችግሮች በመጋለጣቸው በርካቶችን ወደ ሀገር ቤት መመለስ ቢቻልም፣ በገፊ ምክንያቶች ዳግም ለስደት እየተዳረጉ እንደሚገኙ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሕገ-ወጥ ሰዎች ዝውውር መከላከልና የተመላሽ ዜጎች ድጋፍና ክትትል መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጄ ተግይበሉ በወቅቱ ለሚዲያዎች ማብራሪያ ሰጥተው ነበር፡፡ የእነዚህ ገፊ የስደት ምክንያቶች ምንድናቸው ከተባለ ሰሞኑን የወጣ አንድ ጥናት እንደሚያመላክተው ሥራ አጥነት ዋናው ምክንያት ነው፡፡ በዚህ ጥናት ውስጥ በኢትዮጵያ 65 በመቶ የሚኾኑ ተመራቂዎች ሥራ ማግኘት አዳጋች ኾኖባቸዋል፡፡

በአፍሪካ አመራር ዩኒቨርሲቲ የተደረገው ይህ ጥናት እንደሚያሳየው ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ወደ ሥራ ገበታ ሲገቡ የሚገጥሟቸው ዋና ዋና ሥጋቶችን የዘረዘረ ሲኾን የሥራ ዕድል እጥረት (65%)፣ ምቹ ያልኾነ የኢኮኖሚ ሁኔታ (37%) እና በቂ የሥራ ልምድ አለመኖር (29%) ናቸው። ከዚህ አኳያ በርካታ ወጣት ኃይል ለሕገወጥ ስደት ይዳረጋል፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ የትግራይ ክልል የወጣቶች ጉዳይ ቢሮ እንደገለጸው፣ በሥራ አጥነት ሳቢያ ከክልሉ በአማካይ በወር 32 ሺሕ ወጣቶች በሕገጥ መንገድ እንየተሰደዱ መኾኑን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል። በሕገወጥ መንገድ ከተሰደዱት ወጣቶች መካከል የተወሰኑት ቤተሰቦች፣ ልጆቻቸው ባኹኑ ወቅት በሊቢያ በሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ተይዘው በአሰቃቂ ኹኔታ ውስጥ እንደሚገኙ መግለጣቸውን ዘገባው ጠቅሷል።

በሌላ በኩል የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥራ አስፈጻሚው አቶ ደረጄ  እንዳሉት ከስደት ተመላሾች ሥራ አለማግኘታቸው በተለይም በክልሎች ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ክፍተት መኖሩ ዳግም ለሕገ-ወጥ ስደት እንዲዳረጉ ምክንያት እየኾነ እንደሚገኝ አብራርተዋል። ከሥራ አጥነቱ በተጨማሪም በሁሉም አካባቢዎች በሚባል ደረጃ የሚታዩ አለመግባባቶች፤ ከስደት ተመላሾች ወደየ አካባቢያቸው ለመመለስ ለቀጣይ ሕይወታቸው የተስፋ ጭላንጭል አለማየታቸው አስቸጋሪ መኾኑን ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል፡፡ ከፍ ሲል እንደተነሳው ከሥራ አጥነት ጋር ተያይዞ በሥራ ቅጥር ሽፋን በሕገ-ወጥ ዓለም አቀፍ የሰው አዘዋዋሪዎች ወደተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚሰደዱ ዜጎች ቀጥር በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል፡፡ ምንም እንኳን መንግሥት ከተሰደዱ በኋላ ችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ለመታደግ እያደረጋቸው ያሉ ጥረቶች የቀጠሉ ቢኾንም ችግሩን በዘላቂነት መቅረፍ አልቻለም፡፡

በቅርቡ ማይናማር ውስጥ ከነበሩበት አስቸጋሪ ሁኔታ አምልጠው ወደ ታይላንድ የገቡ 38 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በመንግሥት ጥረት ወደሀገር መመለሳቸው አይዘነጋም፡፡ ከሰሞኑም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በርካታ ዜጎች በዚሁም በማይናማር በስቃይ የሚገኙ ዜጎች ከአዲስ አበባ እስከ ታይዋን በተዘረጋ ሰንሰለት ሰለባ የሆኑ ናቸው ሲል አስታውቋል፡፡ በሚኒቴሩ የቆንስላ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አምበሳደር ሲራጅ ረሺድ፤ “በማይናማር በከፍተኛ ሁኔታ ስቃይ ውስጥ የነበሩ ዜጎችን ለማስመለስ ከማይናማር መንግሥት እና ሌሎች አጋሮች ጋር ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ” ብለዋል፡፡ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በበኩላቸው በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ሙሉ ለሙሉ ለማስወጣት ችግሮች እንዳሉ የገለጹ ሲኾን፤ ጃፓን በሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ዜጎቹን ወደ ታይላንድ በማሻገር ወደ አገራቸው ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ሰሞኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም የኢትዮጵያ መንግሥት በሦስት ዓመት ውስጥ ብቻ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የነበሩ ከ450 ሺሕ በላይ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ በዚህ ዓመትም ወደተለያዩ ሀገራት በሕገ-ወጥ መንገዶች ወጥተው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ፤ 27 ሺሕ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማደረጉንም ገልጿል፡፡ በጥቅሉ ግን መንግሥት የወጡ ዜጎችን ከማስመለስ ባሻገር ስደትን ለመቀነሥ የሚሠሩ ተግባራት ላይ ጥረት ቢያደርግ የተሸለ ውጤት ማግኘት ይቻላል፡፡

አሁን ላይ ዓለማችን ሕገወጥ ስደተኛ ቀርቶ ሕጋዊ ስደተኞችንም መጸየፍ ጀምራለች፡፡ ስደተኛ ጠልነት እየገነገነ መጥቷል፡፡ ለምሳሌ ከሰሞኑ በጀርመን ሀገር የዉጭ ዜጎችን ተቃውመው የሁለት ቀናት አድማ መተዋል፡፡ ጀርመናውያን የተቃወሙት ሕገወጥ ስደተኞችን ብቻ ሳይኾን የጀርመን ዜጋ የኾኑትን ነገር ግን የዘር ሐረጋቸው ከጀርመን ዉጭ የኾኑትንም ጭምር ነው፡፡ እንደምሳሌ ጀርመን ተነሳች እንጅ ሁሉም ያደጉ ሀገራት ስደተኛ እንደማይሹ ግልጽ ነው፡፡ አሜሪካም በቅርቡ ከስምንት ሺህ በላይ ስደተኞችን ለማባረር ማቀዷን ይፋ ማድረጓ አይዘነጋም፡፡ ስደተኞችን ይረዱ የነበሩ ዓለም አቀፍ ተቋማትም እጃቸውን በመሰብሰብ ላይ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ በጥቅሉ ኢትዮጵያውያንን በዋናነት ከሕገወጥ ስደት መታደግ የመንግሥት ፈጣኑ ኃላፊነት ነው፡፡

ግዮን መጽሔት ቅጽ 7 ቁጥር 224 የካቲት 29 2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የስደትና መፈናቀል ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል

በተባበሩት መንግሥታት የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) ኢትዮጵያ ውስጥ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት...

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እና ፕሬዚዳንት አልሲሲ ፊት ለፊት ሊገናኙ?

አብይ አህመድ እና አበዱልፈታህ አልሲሲ ፊትለፊት እንዲገናኙ እንደምትፈልግ አሜሪካ...

በትግራይ ጦርነትን ከማስቀረት ሰሞኑን እየተካሄዱ ያሉት ሰልፎች መበረታት አለባቸው

ላለፉት ተከታታይ ቀናት በርካታ ጥያቄዎችን ያነገቡ የቀድሞ ተዋጊዎች በትግራይ...

ግብፅ እና ሱዳን በዓባይ ውኃ እና በሱዳን ቀውስ ዙሪያ ተወያዩ

የግብፁ ፕሬዝደንት ዐብደል ፋታህ ኤል-ሲሲ የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር...