በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት ሶስት ወራት በተኪ ምርት 1 ነጥብ 08 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማዳን መቻሉን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለፀ፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)÷ በሩብ ዓመቱ የአምራች ዘርፉን ውጤታማነት ይበልጥ ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል፡፡
ኢንዱስትሪዎች በተኪ ምርት ላይ በስፋት እንዲሳተፉ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ÷ አመርቂ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ በተለያዩ ዘርፎች በተኪ ምርት ላይ በተከናወኑ ሥራዎች 1 ነጥብ 08 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማዳን መቻሉን አብራርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም እና የሥራ እድል ፈጠራ ከማሳደግ አንጻር ተጨባጭ ውጤት ተገኝቷል ያሉት ሚኒስትሯ በሩብ ዓመቱ 37 አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን ጠቁመዋል፡፡
አክለውም የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሥራ ውጤታማነት እየተጠናከረ መሆኑን ገልፀው÷ ባለፉት ሶስት ወራት 10 ፋብሪካዎች ሥራ መጀመራቸውን አመልክተዋል፡፡
በፓርኮቹ 6 ዩኒየኖች እና 67 የህብረት ሥራ ማህበራትን ጨምሮ በአጠቃይ 272 ሺህ 635 አርሶ አደሮች በግብዓት ትስስር መፍጠራቸውንም አስረድተዋል፡፡
በአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተጨማሪ 31 ፋብሪካዎች በቅርቡ ሥራ ለመጀመር አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ከኢንዱስትሪ ፓርኮች በወጪ ንግድ 47 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን ÷ በሥራ እድል ፈጠራም የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል ሲሉ መግለጻቸውን የዘገበው ኤፍ ኤም ሲ ነው፡፡
