የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ በከተማው በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የመንግስት ንግድ ቤቶችን በጨረታ አወዳድሮ በኪራይ ለማስተላለፍ የወጣውን የሁለተኛ ዙር ጨረታ ውጤት ይፋ አድርጓል።
ከመስከረም 22 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለተወዳዳሪዎች ክፍት የተደረገውና ከጥቅምት 18/2018 እስከ ጥቅምት 20/2018 ድረስ የተከፈተው ይህ ጨረታ፣ በተለይ እንደ አራዳ ክፍለ ከተማ ባሉ ማዕከላዊ አካባቢዎች ከፍተኛ ፉክክር ያስተናገደ ሲሆን፣ በ4 ኪሎ ጆሊ ባር አካባቢ የሚገኝ አንድ የንግድ ቤት በካሬ ሜትር 11 ሺህ 699 ብር ቀርቦ ከፍተኛውን ዋጋ አግኝቷል።
በተመሳሳይ የጆሊ ባር አካባቢ ለሌላ ንግድ ቤት 8 ሺህ 50 ብር እንዲሁም በቤልኤር የሚገኝ ንግድ ቤት 6 ሺህ 317 ብር ተመን ተሰጥቶታል።
የጨረታው ውጤት ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ ቢሮው አሸናፊዎች ከህዳር 04 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት 10 ተከታታይ የስራ ቀናት ንግድ ቤቱ በሚገኝበት ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ጽ/ቤት በአካል በመቅረብ ውል እንዲፈፅሙ ጠይቋል።
