(ጥናት የገለጣቸው እውነቶች)
በዳንኤል መኮንን ይልማ
መግቢያ
የትግራይ ክልል ትምህርት ዘርፍ ለሁለት አመታት በተካሄደው አውዳሚ ጦርነትና የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ባስከተሉት ጥምር ጉዳት በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ በመዳከር ላይ ይገኛል፡፡ የትምህርት ስርአቱ በተራዘመው ጦርነት ምክንያት ጭርሱኑ የመንኮታኮት አደጋ ተጋርጦበት ነበር፡፡ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም የተፈረመው የፕሪቶሪያ ስምምነት በትግራይ የትምህርት ዘርፉን ቀውስ ለመፍታትና ዘርፉን መልሶ ለማቋቋም መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡ የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመም በኋላም ግን የክልሉን ትምህርት አገልግሎት ወደ ቀድሞው ሁኔታ ለመመለሰ በርካታ ጉዳዮች እንቅፋት ሆነዋል፡፡
የዚህ ፖሊሲ መግለጫ አላማ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ስላለው የትምህርት ዘርፍና አገልግሎት የተሟላ ትንተና በማቅረብ በተለይም ጦርነቱና ወረርሽኙ ያስከተሉትን ጉዳቶች በማጉላት በክልልና በፌዴራል ደረጃ በትምህርት ዘርፍ የሚሰሩ የብዙሀን ማህበራት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ አህጉራዊና አለም አቀፍ ድርጅቶችና ሀላፊዎች ግንዛቤ ኖሯቸው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ነው፡፡
ስለዚህም በዳሰሳ ጥናቱ መሰረት መረጃዎች እንደሚያሳዩት በክልሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በርካታ ትምህርት ቤቶች ክፉኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን የተቀሩት ሌሎች ትምህርት ቤቶች ደግሞ ከቀያቸው በተፈናቀሉ ሰዎች ተይዘዋል፡፡
በመጨረሻም የዳሰሳ ጥናቱ ምክረ አሳቦችን የሚያስቀምጥ ሲሆን ምክረ ሀሳቡም የትምህርት ስርአቱን መልሶ ለማቋቋምና ለማሻሻል ያለመ ነው፡፡ የምክረ ሀሳቦቹ ትኩረቶች የትምህርት መሰረተ ልማቶችን መልሶ ማቋቋም፣ የትምህረት መርጃ መሳሪያዎችን ማሟላት፣ ለተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራም ድጋፍ መስጠት፣ ሰላምና ደህንንትን ማስጠበቅና የትምህርት ዘርፉን የሰው ሀይል ማጠናከር የሚሉ ናቸው፡፡
ቁልፍ ነጥቦች
ጽኑ የትምህርት ዘርፍ መታወክ፡- በኮቪድ 19 ወረርሽኝና ለሁለት አመታት በተካሄደው አውዳሚ ጦርነት የትግራይ ክልል የትምህርት ስርአት ክፉኛ በመታወኩ በትምህርት ዘርፉ መሰረተ ልማቶች ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት ከማስከተሉም በላይ በርካታ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጪ አድርጓቸዋል፡፡
ዝቅተኛ የተማሪዎች ተሳትፎ፡- በክልሉ በ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ይመዘገባሉ ተብለው ከተገመተው የተማሪዎች ቁጥር 40 በመቶ ብቻ የተመዘገቡ ሲሆን 729,267 ሴት ተማሪዎችን ጨምሮ 1,487,600 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል፡፡ በክልሉ የማዕከላዊና የሰሜን ምዕራብ ዞኖች በከፍተኛ ሁኔታ ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ተማሪዎች የተመዘገቡባቸው ዞኖች ሆነዋል፡፡
መጠነ ሰፊ የመሰረተ ልማት ጉዳት፡- ጦርነቱ በክልሉ መጠነ ሰፊ የመሰረተ ልማት ጉዳት ያስከተለ ሲሆን በዚህም 74.9 በመቶ ትምህርት ቤቶች ከፊል ጉዳት፣ 19.1 በመቶ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፡፡ ስለዚህም በርካታ ተማሪዎች እውቀት የመቅሰም እድላቸውን ክፉኛ በሚያቀጭጭ መልኩ በጊዚያዊ መጠለያና ለደህንነታቸው ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ለመማር ተገደዋል፡፡
የመምህራንና የሰው ሀይል እጥረት፡- ክልሉ ከፍተኛ የመምህራን እጥረት የገጠመው ሲሆን አሁን ካሉት 16.1% (2,434) ተጨማሪ መምህራን ያስፈልጋሉ፡፡ በጦርነቱ ምክንያት መምህራን ለተራዘመ ጊዚያት ደሞዝ ስላልተከፈላቸው ሞራላቸው በመውደቁ የትምህርት ስርአቱን ለከፋ ቀውስ ዳርጎታል፡፡
ስነልቦናዊ ቀውስ፡- ጦርነቱ በክልሉ ተማሪዎችና መምህራን ላይ ስር የሰደደ ሥነ ልቦናዊ ቀውስና የመንፈስ መረበሽን ፈጥሯል፡፡ ሥነ ልቦናዊ ቀውሱ የመማር ማስተማር ሂደቱን ከመጉዳቱም በላይ መምህራንና ተማሪዎችን ጭንቀት ለሚያስከትለው የአዕምሮ መረበሽ ዳርጓቸዋል፡፡
የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም እንደ መፍትሄ፡- የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም የድርቅና ርሀብ ተጽዕኖን በመቋቋም፣ የተማሪዎችን ትምህርት የመከታተል ችሎታ በማሳደግ፣ የተማሪዎችን ጤናና ትኩረት በማሻሻል፣ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለሚልኩ ወላጆች ማበረታቻ በመሆን ወሳኝ መፍትሄ መሆኑ ተለይቷል፡፡
የብዙሀን ገንዘብ የማሰባሰብ ስልት እንደ ስትራቴጂያዊ የፖሊሲ አማራጭ፡- የብዙሀን ገንዘብ የማሰባሰብ ስልት መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከህጉራዊና አለም አቀፍ መንግስታት፣ ከግሉ ዘርፍና በውጭ ከሚኖሩ ዜጎች ለትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራሞች ገንዘብ በማሰባሰብ ፕሮግራሞቹ እንዲስፋፉና ዘላቂ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑ በአማራጭ ስልትነት ቀርቧል፡፡
የበለጠ ትኩረት ለሴት ተማሪዎች፡- የትምህርት ዘርፉ ቀውስ ባልተመጣጠነ ሁኔታ በሴት ተማሪዎች ላይ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር በተለይም ከጦርነት በኋላ የሴት ተማሪዎችን ልዩ ፍላጎትና ፈታኝ ሁኔታዎችን ለይቶ መፍትሄ መስጠትን የግድ ይላል፡፡
ሁል አቀፍ የስነልቦና ማህበራዊ ድጋፍ አስፈላጊነት፡- በትግራይ የትምህርት ዘርፉን መልሶ ለማቋቋምና ለማጠናከር ለተማሪዎችና ለመምህራን መጠነ ሰፊ ጭንቀትና የአዕምሮ መረበሽ ችግሮች፣ የመማር ማስተማር ቀውስ፣ ለአዕምሮ ደህንነት ችግሮች መፍትሄ የሚሰጥ ሁል አቀፍ የስነልቦና ማህበራዊ ድጋፍ ነው፡፡
የትብብር ጥረት ጥሪ፡- በትግራይ የትምህርት ስርአቱን መልሶ ለመገንባትና ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ የመንግስትን፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ የአለም አቀፍ ድርጅቶችንና የግሉን ዘርፍ ጨምሮ የፖሊሲ መግለጫው የተለያዩ ባለደርሻዎች ትብብር አስፈላጊነት ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡
- የርዕሰ ጉዳዩ ዳራና ወቅታዊ ሁኔታ
ሰባት ዞኖችን ያቀፈው የትግራይ ክልል የትምህርት ዘርፍ በኮቪድ 19 ወረርሽኝና ወረርሽኙን ተከትሎት በመጣው ጦርነት ምክንያት ክፉኛ ታውኳል፡፡ በወረርሽኙ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የትምህርት አገልግሎት ተከትሎት የመጣው ጦርነት የትምህርት መሰረተ ልማቶችን በማውደም የትምህርት ዘርፉ እንዲናጋ በማድረግ ለከፋ ጉዳት ዳርጎታል፡፡
በጥቅምት/ 2015 ዓ.ም በፕሪቶሪያ የተደረገው የሰላም ስምምነት በእጅጉ የታወከውን የክልሉን የትምህርት ዘርፍ መፍትሄ ለመስጠት ምቹና ሰላማዊ ሁኔታ የፈጠረ ቢሆንም የትምህርት አገልግሎቱን መልሶ ለማቋቋምን ለማጠናከር የተደረገው ጥረት አዝጋሚ በመሆኑ የክልሉ ትምህረት ዘርፍ አሁንም በችግር አረንቋ ውስጥ እንደተዘፈቀ ነው፡፡ በመሆኑም የክልሉ የትምህርት ስርአት ጦርነቱ ባስከተለው ክፉ ጠባሳ እየተፈተነ ይገኛል፡፡ አሁንም በርካታ የክልሉ ትምህርት ቤቶች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ተጠልለውባቸዋል፣ መጠነ ሰፊ የትምህርት መሰረተ ልማቶች ፈራርሰዋል እንዲሁም ከፍተኛ የትምህርት መርጃ መሳሪዎችና የመምህራን እጥረት ተከስቷል፡፡
ጦርነቱ በክልሉ የትምህርት መሰረተ ልማትና በተማሪዎችና በመምህራን ስነልቦናዊ ደህንነት ላይ ጉዳት በማድረስ ዛላቂ ጠባሳ ትቶ አልፏል፡፡ በትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ መረጃ መሰረት በክልሉ ከሚገኙ 2492 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 105ቱ (4.2 በመቶ) የሚሆኑት ከቀያቸው በተፈናቀሉ ዜጎች በመያዛቸው ተማሪዎች በአንድ የመማሪያ ክፍል ብዙ ሆነው ተጨናንቀው እንዲማሩና ለመማር ምቹ ያልሆነ ከባቢያዊ ሁኔታ ውስጥ እንዲቆዩ ዳርጓቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ ተማሪዎች በጊዚያዊ መጠለያዎችና በፈራረሱ ትምህርት ቤቶች እንዲማሩ በመገደዳቸው እውቀት የመገብየት እድላቸው እንዲቀጭጭ ሆኗል፡፡ በተጨማሪም ትምህርት ቤቶች ከቀያቸው በተፈናቀሉ ዜጎች በመያዛቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤቶች እንዳይልኩ እንቅፋት ከመፈጠሩም በላይ ቢልኩም አንኳ እጅግ በተጨናነቀ ሁኔታ ስለሚማሩ በትምህረት ጥራት ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል፡፡
- በትምህርት ዘርፉ ላይ የደረሰ ተጽዕኖና ወቅታዊ አሀዞች
ከትግራይ ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ጦርነቱ በተማሪዎች ትምህርት ገበታ ላይ መገኘትና በወቅቱ ተገኝተው እውቀት መቅሰም ላይ የከፋ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ በክልሉ በ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን 2,481,969 ተማሪዎችን ለመመዝገብ ሰፋ ያለ እቅድ ቢያዝም መመዝግብ የተቻለው ግን 40 በመቶ ማለትም 994,369 ብቻ ነበር፡፡ ስለዚህም 60 በመቶ ተማሪዎች ማለትም 1,487,600 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሲሆኑ ከነዚህም ውስጥ 729,267 ሴት ተማሪዎች ናቸው፡፡
የትግራይ ክልል ማዕከላዊና ሰሜን ምዕራብ ዞኖች በእጅጉ ተጽዕኖ የደረሰባቸው ሲሆኑ 40.7 በመቶ ከማዕከላዊ፣ 65.8 በመቶ ተማሪዎች ከሰሜን ምዕራብ ዞኖች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል፡፡ ይህ ሁኔታ በትምህርት ተደራሽነት ላይ ትልቅ ክፍተት የፈጠረ ሲሆን ከሁለቱ ዞኖች 74,225 ልጃገረዶችን ከትምህርት ውጪ በማድረግ በተለይ በሴት ተማሪዎች ላይ ተጽዕኖው የከፋ ነው፡፡ ለተማሪዎቹ ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆን ርዕሰ መምህራንና አስተማሪዎች በርካታ ጉዳዮችን በምክንያትነት ገልጸዋል፡፡
- አበይት ፈተናዎች
የትግራይ ክልል የትምህርት ስርአትን የገጠመው ፈተና ዘርፈ ብዙ በመሆኑ ሁል አቀፍ ምላሽና መፍትሄ ያስፈልገዋል፡፡
የትምህርት መሰረተ ልማት ጉዳት፡- ኪሮስ በተባሉ ተመራማሪ ጥናት መሰረት ከጦርነቱ በፊት በትግራይ ክልል 2,500 ትምህርት ቤቶች፣ 40,000 መማሪያ ክፍሎች፣ 2 የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆች፣ ኮምፒተሮች ፕሪንተሮች ፕላዝማ ቲቪዎች ከባድ ፎቶ ኮፒዎችን ጨምሮ 30,000 የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎችና 300,000 የላቦራቶሪ መገልገያዎችና የትምህረት መርጃ መሳሪያዎች ነበሩ፡፡ እነደአለመታደል ሆኖ አብዛኞቹ ከላይ የተቀሱት የትምህርት መሰረተ ልማቶችና መገልገያ መሳሪዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ተሰረቅዋል ወይም ወድመዋል፡፡
ጉዳቱ ስርቆትን፣ መሰባባርንና ቃጠሎን ያካተተ ሲሆን 96.5 በመቶ የተማሪዎች ዴስኮች፣ 95.9 በመቶ ጥቁር ሰሌዳ፣ 63.5 በመቶ የተማሪዎች መማሪያ መጻህፍት፣ 85.1 በመቶ ኮምፒውተሮች፣ 79.9 በመቶ ፕላዝማ ቲቪዎች፣ 84.5 በመቶ የሳይንስ ላቦራቶሪ መሳሪያወች፣ 92.5 በመቶ የትምህረት መርጃ ሞዴሎችና 48 በመቶ መጸዳጃ ቤቶች የጉዳት ሰለባ ሆነዋል፡፡ ይህ መጠነ ሰፊ የትምህርት መሰረተ ልማት ጉዳት በክልሉ የመማር ማስተማሩን ምህዳር ክፉኛ ተጽዕኖ አሳድሮበታል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴርና በትግራይ ክልል ጊዚያዊ መስተዳድር ትምህርት ቢሮ በ22 የክልሉ ወረዳዎች በተደረገ የዳሰሳ ጥናት 74.9 በመቶ ማለትም 595 ትምህርት ቤቶች በከፊል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን 19.1 በመቶ ማለትም 152 ትምህርት ቤቶች የመማሪያ ክፍሎቻቸውና የትምህርት መገልገያ መሳሪያዎቻቸው ሙሉ በሙሉ ውድመት ደርሶባቸዋል፡፡ ስለዚህም ተማሪዎች በጊዚያዊ የመማሪያ ክፍሎችና ጉዳት በደረሰባቸው የመማሪያ ክፍሎች በድንጋይ ላይ ተቀምጠው ትምህርታቸውን ለመከታተል ተገደዋል፡፡ በተጨማሪም 61 ትምህርት ቤቶች (7.03 በመቶ) ትምህርት ቤቶች በድርቅና ርሀብ ምክንያት ተዘግተዋል፡፡
በትግራይ ትምህርት ቢሮ ግርድፍ ስሌት መሰረት ከ1ኛ አስከ 8ኛ ክፍል ባለው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያልተጎዱ የመማሪያ ክፍሎች ከተማሪዎች ጋር ያላቸው ጥምረታ 1:434 መሆኑን ያሳያል፡፡ አሚ በተባሉ አጥጪ መሰረት ደግሞ በክልሉ በትምህርት መሰረተ ልማት ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጓኛም 2,146 የትምህርቱ ዘርፍ ማህበረሰብ አባላት የተገደሉ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 1,911 ተማሪዎች ናቸው፡፡ ከተገደሉት ተማሪዎችም ውስጥ 84 በመቶ ሴት ተማሪዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡
የሰው ሀይል እጥረት፡- ጦርነቱ የመምህራንና የሌሎች የትምህርቱን ዘርፍ የሰው ሀይል እጥረት አስከትሏል፡፡ በጦርነቱ ምክንያት በርካታ መምህራን አካላዊ ጉዳትና መፈናቀል ደርሶባቸዋል፡፡ በትግራይ ትምህርት ቢሮ የዳሰሳ ጥናት በተደረገባቸው ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ለመከታተል በማይቻልበትና አሉታዊ ተጽዕኖ በሚያስከትል ሁኔታ አንድ መምህር በርካታ ክፍሎችን እንዲሸፍን በሚያስገድድ መልኩ ከፍተኛ የስራ ጫና ተከስቶ ታይቷል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት አሁን ካለው 2,434 ተጨማሪ መምህራን ወይም 16.1 በመቶ ተጨማሪ መምህራን ያስፈልጋሉ፡፡ በኢኒሺየቲቪ አፍሪካ አዘጋጅነት የተካሄደው አውደ ጥናት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ርእሰ መምሀራንና መመህራን ለ17 ወራት ደሞዝ ስላተከፈላቸው ተነሳሽነታቸው በእጅጉ ተመናምኗል፡፡
የስነ ልቦናዊና ማህበራዊ ድጋፍ፡- የስነ ልቦናዊና ማህበራዊ ድጋፍ እጥረት የትምህርቱን ዘርፍ መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት አዝጋሚ እንዲሆን አድረጎታል፡፡ ትምህርት ቤቶች ከተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ባገኙት ድጋፍ ለተማሪዎቻቸው የስነልቦናና ማህበራ ድጋፍ ቢያደርጉም ትምህርት ቤቶቹና የወረዳ ትምህርት ቢሮ ጽህፈት ቤቶች መረጃዎቸን አጠናቅረው አልያዙም፡፡ ይህ ሁኔታ በጉዳዩ ላይ ማጠናከሪያ ስልጠና መስጠት እንደሚያስፈልግ ያመለክታል፡፡
ድርቅና ርሀብ፡- ኪሮስ በተባሉት አጥኚ መሰረት በጦርነቱ ምክንያት 90 በመቶ የሚሆነው የትግራይ ህዝብ ለረሀብና ከረሀብ ለሚስተካከል ሁኔታ የተዳረገ ሲሆን ይህም የትምህርቱን ዘርፍ ለከፋ ቀውስ ዳርጎታል፡፡ እንደ ተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ የጃንዋሪ 2024 ሪፖርት መሰረት በትግራይ ክልል በድርቅ ምክንያት 1.4 ሚሊዮን ዜጎች ያስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ይህም በ40 አመታት ታሪክ የከፋው ድርቅ ነው፡፡ ድርቁ በተመሳሳይ መልኩ በተማሪዎችና በአስተማሪዎችም ዘንድ በምግብ እጥረት እንዲሰቃዩ ያደረገ ሲሆን ይህም ተመማሪዎች ትምህርታቸውን በመደበኛነት እንዳይከታተሉ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡
የጦርነቱ ስነልቦናዊ ተጽዕኖ፡- መፈናቀልን፣ ቤተሰብን ማጣትንና ስነልቦናዊ ጭንቀትን ጨምሮ ጦርነቱ በተማሪዎችና መምህራን ላይ መጠነ ሰፊ የመንፈስ መታወክን አስከትሏል፡፡ እ.ኤ.አ በ2023 በሉሚኒየስ ፈንድ በክልሉ በመማር ማስተማር ላይ የደረሰው ኪሳራ፣ የደረሰው የመንፈስ መታወክ፣ የተማሪዎች፣ የመምህራንና የዋላጆች በችግሮች ውስጥ በጽናት የማለፍ ደረጃ ተጠንቶ ነበር፡፡ ጥናቱ እንዳመለከተው ጦርነቱ በመማር ማስተማር ስርአቱ ላይ ጉልህ ኪሳራ እንዳደረሰና መጠነ ሰፊ ስነልቦናዊ የመንፈስ መታወክ እንዳስከተለ አመልክቷል፡፡
በጥናቱ መሰረት 44 በመቶ የክልሉ ተማሪዎች የሞተ ሰው አስከሬን አይተዋል፣ 29 በመቶ ተማሪዎች ሰው ሲገደል አይተዋል እነዲሁም 62 በመቶ ተማሪዎች እራሳቸው እንገደላለን ብለው ይጠብቁ ነበር፡፡ በተጨማሪም ከአምስት አስተማሪዎች አራቱ ጭንቀት የሚያስከትለው የመንፈስ መታወክ ደርሶባቸው በችግሩ ውስጥ አልፈዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ትኩረት ሰጥተው የመከታተል ችሎታቸውን ክፉኛ ጎድቶታል፡፡ በርካታ ተማሪዎች ገና በለጋ እድሚያቸው የጭካኔ ተግባር ሲፈጸም በማየታቸው ባጠቃለይ የትምህርት ቤት ማህበረሰቡ ለህሊና መታወክ ተዳርጓል፡፡
የትምህርት መርጃ ማሳሪያዎች እጥረት፡- የመማሪያ መጻህፍትን፣ ዴስኮችና ሌሎች የትምህረት መርጃ መሳሪያዎችን ጨምሮ በክልሉ ከፍተኛ ወሳኝ የትምህርት መርጃ መሳሪዎች እጥረት አለ፡፡ ተማሪዎች አብዛኛውን ጊዜ እየተማሩ ያሉት ለውጤታማ ትምህርት አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች ሳይሟሉላቸው ነው፡፡ በክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ መሰረት በ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከ340,709 ተማሪዎች ውስጥ 88,998 ተማሪዎች ማለትም 26.5 በመቶ ብቻ የትምህርት መገልገያ ቁሳቁሶች አግኝተዋል፡፡
የደህንነት ስጋት፡- በትምህርት ቤቶች አካባቢ ያልፈነዱ ፈንጂዎችና ሌሎች የጦር መሳሪያዎች መኖር በተማሪዎችና መምህራን ላይ የደህንነት ስጋት ደቅኗል፡፡ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች በአቅራቢያቸው የታጠቁ ቡድኖች ያሉ በመሆናቸው ህጻናት በአግባቡ ትምህርታቸውን እዳይከታተሉ ተጨማሪ የደህንነት ስጋት ተፈጥሮባቸዋል፡፡
ስደትና መፈናቀል፡- ሲካሄድ የቆው መፈናቀልና ስደት የተማሪዎችን የመማር ሂደት ክፉኛ አውኮታል፡፡ በርካታ ህጻናት ከቀያቸው በመፈናቀላቸውና ወደ ሌላ ስፍራ በመሰደዳቸው የትምህርት ተሳትፏቸውን በእጅጉ ገድቦታል፡፡
በተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራም ተግባራዊነት ላይ የታየ ክፍተት፡- የጦርነቱን ማብቃት ተከትሎ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ለ4 አመታት የተቋረጠውን ትምህርት ለማካካስ የተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራም ተግባራዊ አድርጓል፡፡ በመሆኑም የተፋጠነ ትምህርት ፕሮግራም እጥር ምጥን ያለ ካሪኩለምና ተግባራዊ መመሪያ ተዘጋጅቶ ለትምህርት ቤቶችና ለወረዳ ትምህርት ጽ/ቤቶች ተሰራጭቷል፡፡ ፕሮግራሙ በስልጠናም ተደግፎ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በማላለ ፈንድ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በክልሉ ትምህርት ቢሮ በተደረገ የዳሰሳ ጥናትና በኢኒሺየቲቪ አፍሪካ በተካሄደው አውደ ጥናት በተገኘው መረጃ መሰረት ፕሮግራሙን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ ሰፊ ክፍተት ተስተውሏል፡፡ በርካታ ተማሪዎችም በመማሪያ መጻኀህፍት እጥረት ትምህርታቸውን በአግባቡ መከተተል እንዳልቻሉ ተረጋግጧል፡፡
ከክልሉ ማዕከላዊና ሰሜን ምእራብ ዞኖች ከተመረጡ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ርእሰ መምህራን እነዳመለከቱትም የተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራም ተግባረዊ በማድረግ ሂደት በትምህርት ቤት መሪዎችና አስተማሪዎች መካከል ግዙፍ የክህሎት ክፍተት አለ፡፡ በጦርነት በተጎዱት ትምህርት ቤቶች ከ9ኛ አስከ 12ኛ ባሉ ክፍሎች ካሪኩለምን እንደ ተጨባጩ ሁኔታ በሚያመች መልኩ ተግባራዊ ያለማድረግና የተፋጠነ ትምህርት ፕሮግራም ካሪኩለም እጥረት ዋንኞቹ ፈተናች ነበሩ፡፡
(ይቀጥላል…)
——-
ምሥጋና፡- ይህ የፖሊሲ መግለጫ ከማላላ ፈንድ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በኢኒሺየቲቭ አፍሪካ የተዘጋጀ ነው፡፡ ኢኒሺየቲቭ አፍሪካ ከማላላ ፈንድ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በትግራይ የተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራም ፕሮጀክትን ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይህ ፕሮጀክት በትግራይ ክልል በተለይም በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች መልሰው እንዲያገግሙና የተማሪዎች አንገብጋቢ ችግሮች እንዲቀረፉ ለማገዝ ያለመ ነው፡፡
———-
ቅጽ 6 ግዮን ቁጥር 218 ሕዳር 14 ቀን 2017 ዓ.ም